በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ክፍል 3

ችግሮችን መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው?

ችግሮችን መፍታት የሚቻለው እንዴት ነው?

“ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።”—1 ጴጥሮስ 4:8

ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር አብራችሁ መኖር ስትጀምሩ የተለያዩ ችግሮች ያጋጥሟችኋል። ይህ የሚሆነው የሁለታችሁ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ስለ ሕይወት ያላችሁ አመለካከት ስለሚለያይ ሊሆን ይችላል። አለዚያም ለችግሮቹ ምክንያት የሚሆኑት ሌሎች ነገሮች ወይም ያልተጠበቁ ክስተቶች ይሆናሉ።

ችግሮች ሲያጋጥሙ እውነታውን ለመሸሽ እንፈተን ይሆናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚመክረን ግን ችግሮቻችንን ተጋፍጠን እንድንፈታቸው ነው። (ማቴዎስ 5:23, 24) የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች በሥራ ላይ ብታውሉ ለችግሮቻችሁ የተሻሉ መፍትሔዎች ታገኛላችሁ።

1 ችግሩን ተወያዩበት

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? ‘ለመናገር ጊዜ አለው።’ (መክብብ 3:1, 7) ስለተፈጠረው ችግር ጊዜ ወስዳችሁ ተነጋገሩ። ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚሰማችሁና ምን እንደምታስቡ ለትዳር ጓደኛችሁ በሐቀኝነት አሳውቁ። ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ምንጊዜም “እውነትን ተነጋገሩ።” (ኤፌሶን 4:25) ስሜታችሁን መቆጣጠር ከባድ በሚሆንባችሁ ጊዜም እንኳ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ ላለመግባት ጥረት አድርጉ። በተረጋጋ መንፈስ መልስ መስጠት፣ ቀላል የሆነው ጉዳይ ተጋግሎ ወደ ጠብ እንዳያመራ ያደርጋል።—ምሳሌ 15:4፤ 26:20

በውይይቱ ላይ የሐሳብ ልዩነት በሚኖራችሁ ጊዜም ጭምር አነጋገራችሁ ደግነት የሚንጸባረቅበት ይሁን፤ ለትዳር ጓደኛችሁ ፍቅርና አክብሮት ማሳየት እንዳለባችሁ ፈጽሞ አትርሱ። (ቆላስይስ 4:6) ችግሩን በተቻለ ፍጥነት ለመፍታት ጥረት አድርጉ፤ ደግሞም አትኮራረፉ።—ኤፌሶን 4:26

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • በችግሩ ላይ ለመወያየት ተስማሚ የሆነ ጊዜ መድቡ

  • የትዳር ጓደኛህ ስትናገር ሳታቋርጣት አዳምጥ። አንተም ተራህ ሲደርስ ትናገራለህ

2 አዳምጡ እንዲሁም አስተውሉ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:10) የምታዳምጡበት መንገድ ትልቅ ልዩነት ያመጣል። የትዳር ጓደኛችሁን አመለካከት ለመረዳት ጣሩ፤ ይህን ለማድረግም “የሌላውን ስሜት የምትረዱ ሁኑ፣ . . . [እንዲሁም] ትሑታን ሁኑ” የሚለውን ምክር በተግባር አውሉ። (1 ጴጥሮስ 3:8፤ ያዕቆብ 1:19) የምታዳምጡ ለመምሰል አትሞክሩ። ለትዳር ጓደኛችሁ ሙሉ ትኩረት ለመስጠት እንዲያመቻችሁ የሚቻል ከሆነ የምትሠሩትን ነገር አቋርጡ፤ አለዚያም ጉዳዩን ሌላ ጊዜ ልትወያዩበት ትችሉ እንደሆነ ሐሳብ አቅርቡ። የትዳር ጓደኛችሁን እንደ ጠላት ሳይሆን እንደ አጋር አድርጋችሁ የምትመለከቱ ከሆነ ‘ለቁጣ አትቸኩሉም።’—መክብብ 7:9

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • የትዳር ጓደኛህ የምትናገረው ነገር ባያስደስትህም እንኳ አእምሮህን ክፍት አድርገህ አዳምጣት

  • ባለቤትህ ከምትናገረው ነገር በስተጀርባ ያለውን መልእክት ለመረዳት ሞክር። የትዳር ጓደኛህ የምትጠቀምባቸውን አካላዊ መግለጫዎችና የድምፅዋን ቃና ልብ በል

3 ውሳኔያችሁን ተግባራዊ አድርጉ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል፤ እንዲሁ ማውራት ግን ችግር ላይ ይጥላል።” (ምሳሌ 14:23) ስለ ችግሩ ተወያይታችሁ ጥሩ መፍትሔ ላይ መድረሳችሁ ብቻውን በቂ አይደለም። ሁለታችሁም የወሰናችሁትን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋችኋል። ይህም ልፋትና ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም አያስቆጭም። (ምሳሌ 10:4) ተባብራችሁ በጋራ የምትሠሩ ከሆነ ለልፋታችሁ “ጥሩ ውጤት” ታገኛላችሁ።—መክብብ 4:9

ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

  • ችግራችሁን ለመፍታት እያንዳንዳችሁ ምን እርምጃዎችን እንደምትወስዱ ወስኑ

  • ያደረጋችሁትን መሻሻል በየጊዜው ገምግሙ