በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከመቃብር ወጥቶ እንደገና መኖር ይቻላል!

ከመቃብር ወጥቶ እንደገና መኖር ይቻላል!

ከመቃብር ወጥቶ እንደገና መኖር ይቻላል!

ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በተሠራ አንድ ፊልም ላይ አንድ ወጣት በሚወደው ሰው መቃብር አጠገብ ቆሞ ይታያል። ከዚያም ይህ ሰው “ሁልጊዜ እማማ ሞት የሕይወት ክፍል ነው ትል ነበር” በማለት ተናገረ። በኋላም ካሜራው ለቅጽበት በመቃብሩ ላይ ያለውን ምልክት ሲያሳይ ወጣቱ “እንዲህ ባይሆን ኖር ደስ ይለኝ ነበር” አለ።

ይህ አስተያየት የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ስሜት ይገልጻል። ሞት እንዴት ያለ ክፉ ጠላት ነው! ሆኖም አምላክ ‘የመጨረሻው ጠላት ሞት ይደመሰሳል’ በማለት ቃል ገብቷል። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ይሁን እንጂ ለዘላለም ለመኖር የሚያስችል ታላቅ አእምሮ ኖሮን ሳለ የምንሞተው ለምንድን ነው? ሞት የሚወገደውስ እንዴት ነው?

የምናረጀውና የምንሞተው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪያችን የሆነውን ይሖዋ አምላክን በተመለከተ “ሥራው ፍጹም ነው” ይላል። (ዘዳግም 32:4፤ መዝሙር 83:18 NW፤ ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) የመጀመሪያው ሰው አዳም ፍጹም ሆኖ ስለተፈጠረ አምላክ ለመኖሪያነት በሰጠው ምድራዊ ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ችሎታ ነበረው። (ዘፍጥረት 2:7-9) ታዲያ አዳም መኖሪያው ከሆነችው ከኤደን ገነት የወጣውም ሆነ አርጅቶ የሞተው ለምንድን ነው?

በአጭሩ አዳም፣ አምላክ አትብላ ብሎ ካዘዘው ዛፍ ፍሬ በመብላት ታዛዥ ሳይሆን በመቅረቱ ነው። አምላክ ለአዳም “በእርግጥ ትሞታለህ” በማለት ከተከለከለው ዛፍ ፍሬ መብላት የሚያስከትለውን ቅጣት በተመለከተ በግልጽ አስጠንቅቆት ነበር። (ዘፍጥረት 2:16, 17) አዳም ሚስቱ ሔዋን ያለችውን ሰምቶ ይህን ትእዛዝ በመጣሱ አምላክ ሁለቱንም ከኤደን ገነት አስወጣቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “[አዳም] እጁን ዘርግቶ [በአትክልት ስፍራው ካለው] ከሕይወት ዛፍ ቀጥፎ እንዳይበላ፣ ለዘላለምም እንዳይኖር” በማለት መናገሩ አምላክ እንዲህ ያለውን አፋጣኝ እርምጃ የወሰደበትን ምክንያት ግልጽ ያደርግልናል።—ዘፍጥረት 3:1-6, 22

አዳምና ሔዋን የሞቱት ባለመታዘዛቸው ምክንያት ነው፤ ታዲያ ዘሮቻቸው ሁሉ የሚያረጁትና የሚሞቱት ለምንድን ነው? እነሱም ከአዳም ኃጢአትን ስለወረሱና ኃጢአት ደግሞ በእያንዳንዱ የአዳም ዘር ላይ አለፍጽምናንና ሞትን ስለሚያስከትል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ኀጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል።”—ሮሜ 5:12

ወደፊት እንደገና መኖር የሚቻልበት መንገድ

ቀደም ብለን እንዳነበብነው ‘ሞት ይደመሰሳል።’ አዎን፣ ሞት ለዘላለም ይወገዳል! (1 ቆሮንቶስ 15:26) ግን እንዴት? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት ይገልጽልናል:- “በአንዱ የጽድቅ ሥራ ለሰው ሁሉ ሕይወትን የሚሰጥ ጽድቅ ተገኘ።” (ሮሜ 5:18) ሰዎች በአምላክ ፊት የጽድቅ አቋም እንዲኖራቸውና የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ምንድን ነው?

አምላክ፣ ሰዎች ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም የወረሱትን ኃጢአት ለመሰረዝ ያደረገላቸው ዝግጅት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው” በማለት ይናገራል። (ሮሜ 6:23) ኢየሱስ ሰዎች ጻድቃን ተብለው ሕይወትን እንዲያገኙ ስለሚያስችላቸው ስለዚህ ዝግጅት ሲናገር “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል” ይላል።—ዮሐንስ 3:16

አምላክም ሆነ ለእኛ ሲል ብዙ መከራ የተቀበለው ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላሳዩን ጥልቅ ፍቅር እስቲ አስብ። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የአምላክ ልጅ ወዶኛል፤ ስለ እኔም ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል’ በማለት ተናግሯል። (ገላትያ 2:20) ይሁንና ለእኛ “ነፍሱን ቤዛ” አድርጎ በመስጠት አስከፊ ከሆኑት የኃጢአት መዘዞች ሊታደገን የሚችለው ብቸኛው ሰው ኢየሱስ የሆነው ለምንድን ነው?—ማቴዎስ 20:28

ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ኃጢአት ያልወረሰው ብቸኛው ሰው ኢየሱስ ስለሆነ ነፍሱን ቤዛ አድርጎ መስጠት የሚችለው እሱ ብቻ ነው። ኃጢአት ሳይወርስ የቀረው እንዴት ነው? በሰማይ የነበረው የኢየሱስ ሕይወት ድንግል ወደነበረችው ወደ ማርያም ማሕፀን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ስለተዘዋወረ ነው። ስለዚህ አንድ መልአክ ለማርያም እንደነገራት ልጇ ‘ቅዱሱ የአምላክ ልጅ’ ተብሎ ተጠርቷል። (ሉቃስ 1:34, 35) ኢየሱስ “ኋለኛው አዳም” ተብሎ የተጠራውና ‘ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም’ ኃጢአት ያልወረሰው በዚህ ምክንያት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:45) ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት ሰው ስለነበረ ራሱን “ተመጣጣኝ ቤዛ” አድርጎ መስጠት ይችላል። ይህም ሲባል የኢየሱስ ሕይወት፣ በአንድ ወቅት ፍጹም ወይም ኃጢአት አልባ ከነበረው ከመጀመሪያው ሰው ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ነበር ማለት ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:6 NW

በዚህ ቤዛዊ ዝግጅት አማካኝነት አምላክ የመጀመሪያው ሰው አዳም ያጣውን ነገር፣ ማለትም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንድንችል አደረገ። ይሁን እንጂ አብዛኛው የሰው ዘር ይህን በረከት ማግኘት እንዲችል ከሞት ተነስቶ እንደገና በሕይወት መኖር ያስፈልገዋል። ይህ እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ነው! ይሁን እንጂ ከሞት በኋላ እንደገና በሕይወት መኖር የሚለው ሐሳብ ለማመን የሚያዳግት ነው?

ለማመን የሚያስችል መሠረት

ሕይወትን የፈጠረው ይሖዋ አምላክ በአንድ ወቅት በሕይወት የኖረን ሰው እንደገና ሕያው ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ያለው መሆኑን ለማመን አዳጋች ይሆንብሃል? አምላክ ለመጀመሪያዋ ሴት ስለሰጣት የመጸነስ ወይም የማርገዝ ችሎታ እስቲ አስብ። “አዳም ሚስቱን ሔዋንን ተገናኛት፤” ከዘጠኝ ወራት ገደማ በኋላ የአብራካቸው ክፋይ የሆነ ሙሉ አካል ያለው ትንሽ ልጅ ተወለደ። (ዘፍጥረት 4:1) የሕፃኑ የአካል ክፍሎች በሙሉ እንዲፈጠሩና እንዲገጣጠሙ ለማድረግ በሔዋን ማሕፀን ውስጥ የተከናወነው ነገር በአሁኑ ጊዜም ሰው ሙሉ በሙሉ ሊረዳው ያልቻለው ተአምር እንደሆነ ተደርጎ ይገለጻል!—መዝሙር 139:13-16

በየቀኑ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ልጆች ስለሚወለዱ ሰዎች ይህን ችሎታ በአብዛኛው እንደ ተአምር አድርገው አይመለከቱትም። ከዚህ ቀደም በሕይወት ኖሮ የሚያውቅን ሰው እንደገና ወደ ሕልውና ማምጣት ግን በብዙዎች ዘንድ ሊታመን እንደማይችል ነገር ተደርጎ ይታሰባል። ኢየሱስ አንዲት ትንሽ ልጅ ሞታ ሲያለቅሱ ለነበሩ ሰዎች ማልቀሳቸውን እንዲያቆሙ ሲነግራቸው እንደ ሞተች እርግጠኛ ስለነበሩ “ሳቁበት።” ኢየሱስ ግን የሞተችውን ልጅ “ተነሺ!” አላት። ልጅቷም “ወዲያውኑ ተነሥታ ቆመች፤ ወዲያ ወዲህም ሄደች።” ታሪኩ በመቀጠል “ሰዎቹም በሁኔታው እጅግ ተደነቁ” በማለት ይነግረናል።—ማርቆስ 5:39-43፤ ሉቃስ 8:51-56

ኢየሱስ የወዳጁ የአልዓዛር መቃብር እንዲከፈት ባዘዘ ጊዜ የአልዓዛር እህት ማርታ “ጌታ ሆይ፤ አሁንማ አራት ቀን ስለቈየ ይሸታል” በማለት ተቃውማ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አልዓዛርን እንደገና ሕያው ሲያደርገው ምንኛ ተደስተው ይሆን! (ዮሐንስ 11:38-44) ብዙዎች ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት በደንብ ያውቁ ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ እስር ቤት በነበረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱ “ሙታን እየተነሱ ነው” በማለት ኢየሱስ ስለፈጸማቸው ተአምራት ሪፖርት ነግረውታል።—ሉቃስ 7:22 NW

በትንሣኤ አማካኝነት እንደገና መኖር

ኢየሱስ ሰዎቹ ከጊዜ በኋላ እንደገና እንደሚታመሙና እንደሚሞቱ እያወቀ እንዲህ ያለውን ተአምር የፈጸመው ለምንድን ነው? እንዲህ ያደረገው የመጀመሪያው ሰው አዳም ያጣው ነገር፣ ማለትም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ሊገኝ እንደሚችል ደግሞም እንደሚገኝ ለማረጋገጥ ነው። ኢየሱስ የፈጸማቸው ትንሣኤዎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የኋላ ኋላ ‘ምድርን ሊወርሱና በእሷም ላይ ለዘላለም ሊኖሩ’ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳይተዋል።—መዝሙር 37:29

ደስ የሚለው ነገር እኛም ‘ለአምላክ ያደርን’ ሰዎች ከሆንን ለዘላለም የመኖር ታላቅ ተስፋ ከሚኖራቸው ሰዎች መካከል ልንሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱ ‘ለአምላክ የማደር’ ባሕርይ “ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ሕይወት የሚሆን ተስፋ” እንዳለው ይናገራል። ይህ ‘የወደፊት ሕይወት’ ‘እውነተኛ ሕይወት’ ተብሎም ተጠርቷል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8 NW፤ 6:19

ይህ እውነተኛ ሕይወት፣ ማለትም ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረው ሕይወት ምን እንደሚመስል እስቲ እንመልከት።