በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ከአንተ የሚጠብቀው ምንድን ነው?

አምላክ ከአንተ የሚጠብቀው ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ ከአንተ የሚጠብቀው ምንድን ነው?

ሕይወታችን ሩጫ የበዛበት መሆኑ ከፍተኛ ውጥረት ይፈጥርብናል። አንዳንዴ ያሉብንን ግዴታዎች በሙሉ መወጣት ብርቱ ትግል ማድረግ ይጠይቅብን ይሆናል። ያም ሆኖ ሕይወት ራሱ ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ መሆኑን ማስታወስ ያስፈልገናል። (መዝሙር 36:9) አምላክ፣ ካለን ጊዜና ጉልበት ምን ያህሉን ለእሱ እንድንሰጠው ይጠብቅብናል? ለዚህ ጥያቄ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው መልስ ምክንያታዊ መሆኑን ማወቃችን የሚያበረታታ ነው።

ኢየሱስ፣ አባቱ ከሰው ልጆች ምን እንደሚጠብቅ ከማንም በተሻለ ያውቃል። (ማቴዎስ 11:27) ኢየሱስ ከትእዛዛት ሁሉ የሚበልጠው የትኛው እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ እንዲህ ብሏል:- “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ።” (ማርቆስ 12:30) እንዲህ ሲባል ምን ማለት ነው? ከአቅማችን በላይ እንድናደርግ የሚጠይቅ ነው?

አምላክን በፍጹም ነፍስ መውደድ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

አምላክ ለእኛ ባሳየን ገደብ የለሽ ጥሩነቱ ላይ የምናሰላስል ከሆነ ለእሱ ያለን ፍቅር እያደገ ይሄዳል። በፍጹም ነፍሳችን አምላክን የምንወድ ከሆነ ያለን ነገር ምንም ይሁን ምን ለእሱ ምርጣችንን ለመስጠት እንነሳሳለን። እኛም “ስለ ዋለልኝ ውለታ ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር ምን ልክፈለው?” በማለት እንደጠየቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ይሰማናል። (መዝሙር 116:12) ለአምላክ ያለን እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር በጊዜ አጠቃቀማችን ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በእያንዳንዱ ሳምንት ይህን ያህል ሰዓት ለአምልኮ ልንመድብ ይገባል የሚል ገደብ አያበጅም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ እንቅስቃሴዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለይቶ ያሳውቀናል፤ እንዲሁም እነዚያ እንቅስቃሴዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገባው ለምን እንደሆነ ይገልጽልናል። ለምሳሌ ኢየሱስ፣ ስለ አምላክ እውቀት መቅሰማችንን መቀጠላችን “የዘላለም ሕይወት” ለማግኘት የሚያስችል ወሳኝ እርምጃ መሆኑን አስተምሯል። (ዮሐንስ 17:3) በተጨማሪም ተከታዮቹ ይህን እውቀት አምላክን ለማያውቁ ሰዎች በማስተማር ሕይወት እንዲያገኙ መርዳት እንደሚገባቸው ተናግሯል። (ማቴዎስ 28:19, 20) መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ጥንካሬ ለማግኘትና እርስ በርስ ለመበረታታት ከእምነት ወዳጆቻችን ጋር አዘውትረን እንድንሰበሰብ አዞናል። (ዕብራውያን 10:24, 25) እነዚህ ሁሉ እንቅስቃሴዎች ጊዜ ይጠይቃሉ።

አምላክ፣ ከአምልኮ በቀር ሌላ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ማድረግ አያስፈልግም የሚል ድርቅ ያለ አቋም እንድንይዝ ይጠብቅብናል? በጭራሽ! በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚያጋጥሙን አስፈላጊ ጉዳዮች ጭምር ትኩረት ያሻቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የቤተሰብ ራሶች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ማቅረብ እንዳለባቸው ሲያዝ እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰው ዘመዶቹን፣ በተለይም የቅርብ ቤተ ሰቡን የማይረዳ ከሆነ . . . ከማያምንም ሰው ይልቅ የባሰ ክፉ ነው።”—1 ጢሞቴዎስ 5:8

አምላክ ሰውን የፈጠረው በሕይወቱ ደስታ ማግኘት እንዲችል አድርጎ ነው። እንግዲያው ከቤተሰባችንም ሆነ ከወዳጆቻችን ጋር አብረን በመመገብና ጤናማ በሆኑ መዝናኛዎች ላይ በመካፈል አስደሳች ጊዜ ማሳለፋችን ተገቢ ነው። ንጉሥ ሰሎሞን እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ለሰዎች፣ በሕይወት እያሉ ደስ ከመሰኘትና መልካምን ነገር ከማድረግ የተሻለ ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ፣ በሚደክምበትም ሁሉ ርካታን ያገኝ ዘንድ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ነው።”—መክብብ 3:12, 13

በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ ‘ትቢያ መሆናችንን ስለሚያስብ’ ያሉብንን የአቅም ገደቦች ይረዳል። (መዝሙር 103:14) መጽሐፍ ቅዱስ በቂ እረፍት ማድረጋችን አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል። በሥራ ተጠምደው ከቆዩ በኋላ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ወደ አንድ ገለልተኛ ስፍራ እንሂድና ጥቂት ዕረፉ” ብሏቸዋል።—ማርቆስ 6:31

እንግዲያው አምላክን የሚያስደስት አኗኗር ሚዛናዊነት የሚንጸባረቅበት ሲሆን ልዩ ልዩ እንቅስቃሴዎችንም ሊያካትት ይችላል። ሆኖም የምናደርገው ማንኛውም ነገር፣ ከአምልኮታችን ጋር በቀጥታ የተያያዘም ይሁን አይሁን አምላክን በሙሉ ነፍስ እንደምንወደው የሚያሳይ ሊሆን ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ “ስትበሉም ሆነ ስትጠጡ፣ ወይም ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ሁሉንም ነገር ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” የሚል ምክር ይሰጣል።—1 ቆሮንቶስ 10:31

ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች በሚገባ መምረጥ

የይሖዋን አምልኮ በሕይወትህ ውስጥ ማስቀደሙ ተግባራዊ ሊሆን እንደማይችል ወይም ከአቅምህ በላይ እንደሆነ ይሰማሃል? አምላክ የሚፈልግብንን ነገር መፈጸም፣ በጊዜ አጠቃቀማችን ላይ ለውጥ ማድረግን አልፎ ተርፎም መሥዋዕትነት መክፈልን እንደሚጠይቅ የተረጋገጠ ነው። ሆኖም አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን የማይቻል ነገር እንድናደርግ አይጠይቀንም። እንዲያውም ፈቃዱን እንድንፈጽም በእጅጉ ይረዳናል። ‘አምላክ በሚሰጠው ብርታት’ የምንታመን ከሆነ ስኬታማ መሆን እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 4:11

በፕሮግራምህ ውስጥ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን ለማካተት ስትል የምታደርጋቸው ማስተካከያዎች በተወሰነ መጠን ውጥረት ሊፈጥሩብህ ይችላሉ። ‘ጸሎት ሰሚ’ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር ዘወትር ለመነጋገር ጊዜ መድብ። (መዝሙር 65:2) ‘እሱ ስለ አንተ እንደሚያስብ’ ተገንዝበህ በጸሎትህ ውስጥ የሚሰማህን ማንኛውንም ጭንቀት መግለጽ ትችላለህ። (1 ጴጥሮስ 5:7) ንጉሥ ዳዊት “አንተ አምላኬ ነህና፣ ፈቃድህን እንድፈጽም አስተምረኝ” በማለት ጸልዮአል። (መዝሙር 143:10) አንተም በተመሳሳይ በሕይወትህ ውስጥ አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ እንድትችል እንዲረዳህ አምላክን መጠየቅ ትችላለህ።

መጽሐፍ ቅዱስ “ወደ እግዚአብሔር ቅረቡ፤ እርሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” በማለት ሞቅ ያለ ግብዣ ያቀርባል። (ያዕቆብ 4:8) መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማጥናትና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንደ መገኘት ባሉ አምላክን በሚያስደስቱ እንቅስቃሴዎች በምትካፈልበት ጊዜ ወደ እሱ ትቀርባለህ። እሱም በምላሹ እድገት ማድረግ እንድትችል ያበረታሃል።

ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ የምትገኘው ጀሊና፣ ቅድሚያ በምትሰጣቸው ጉዳዮች ረገድ ማስተካከያ ለማድረግ ስላደረገችው ጥረት ስትናገር፣ “እንዲህ ማድረጉ ቀላል አልነበረም” ብላለች። አክላም እንዲህ ብላለች:- “በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መካፈል ከጀመርኩ ወዲህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ብርታት አግኝቻለሁ። ከሌሎች ያገኘሁት ያልተቋረጠ ድጋፍም ረድቶኛል።” አምላክን ማገልገል የሚያስገኘውን በረከት መቅመሳችን ለውጥ እንድናደርግ ተጨማሪ ኃይል ይሰጠናል። (ኤፌሶን 6:10) ጀሊና፣ “ከባለቤቴ ጋር ያለኝን ግንኙነትና ለልጆቼ ተግሣጽ የምሰጥበትን መንገድ አሻሽያለሁ” ብላለች።

ዛሬ ያለው ኑሮ ጫና ቢፈጥርብህም እንኳ በሕይወትህ ውስጥ ቅድሚያ መስጠት የሚገቡህን ነገሮች እንድትመረምርና አምላክን ለማገልገል ትችል ዘንድ ‘ዘመኑን በሚገባ እንድትዋጅ’ ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ሊያጠነክርህ ብሎም ሊያነሳሳህ ይችላል። (ኤፌሶን 3:16፤ 5:15-17) ኢየሱስ “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል” ብሏል።—ሉቃስ 18:27

ይህን አስተውለኸዋል?

▪ በሕይወትህ ውስጥ ለአምላክ ፈቃድ ቅድሚያ መስጠት ያለብህ ለምንድን ነው?—መዝሙር 116:12፤ ማርቆስ 12:30

▪ አምላክ በየትኞቹ እንቅስቃሴዎች እንድትካፈል ይጠብቅብሃል?—ማቴዎስ 28:19, 20፤ ዮሐንስ 17:3፤ ዕብራውያን 10:24, 25

▪ አምላክን ለማስደሰት ቅድሚያ በምትሰጣቸው ነገሮች ረገድ ተገቢውን ማስተካከያ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?—ኤፌሶን 5:15-17፤ ያዕቆብ 4:8

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክን ማስደሰት ሚዛናዊ መሆንን ይጠይቃል