በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሽታ ፈጽሞ የማይኖርበት ጊዜ!

በሽታ ፈጽሞ የማይኖርበት ጊዜ!

በሽታ ፈጽሞ የማይኖርበት ጊዜ!

ዙ ሰዎች ከሞት በኋላ በሰማይ ላይ በሚያገኙት ሕይወት ከሥቃይና ከበሽታ እንደሚገላገሉ ተስፋ ያደርጋሉ። ይሁን እንጂ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ካለው ከዚህ እምነት በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ በአብዛኛው ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ እንደሚኖሩ ተስፋ ይሰጣል። (መዝሙር 37:11፤ 115:16) ይህ ተስፋ ፍጹም ጤንነት፣ ደስታና ዘላለማዊ ሕይወት ማግኘትንም ይጨምራል።

ለመሆኑ የምንታመመውና የምንሞተው ለምንድን ነው? ደግሞስ በሽታ የሌለበት ዓለም የሚመጣው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።

የበሽታ ዋነኛ መንስኤ የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ወላጆቻችን የሆኑት አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት ፍጹም ጤንነት ያለው አካል እንዲኖራቸው ተደርጎ ነበር። (ዘፍጥረት 1:31፤ ዘዳግም 32:4) በምድር ላይ ለዘላለም መኖር እንዲችሉ ሆነው ተሠርተው ነበር። አካላቸው በበሽታ መጠቃት የጀመረው ሆን ብለው በአምላክ ላይ ካመጹ በኋላ ነው። (ዘፍጥረት 3:17-19) የአምላክን ሥልጣን ሳይቀበሉ በመቅረታቸው የፍጹም ሕይወት ምንጭ ከሆነው ከፈጣሪያቸው ጋር የነበራቸው ዝምድና ተቋረጠ። ከዚያን ጊዜ አንስቶ እንከን ያለባቸው ሆኑ። በዚህም ሳቢያ አምላክ አስቀድሞ እንዳስጠነቀቃቸው ለበሽታና ለሞት ተዳረጉ።—ዘፍጥረት 2:16, 17፤ 5:5

አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ካመጹ በኋላ ለልጆቻቸው ሊያወርሱ የሚችሉት ኃጢአትን ብቻ ነበር። (ሮሜ 5:12) ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው በዛሬው ጊዜ የሳይንስ ሊቃውንት ሰዎች እንዲታመሙና እንዲሞቱ የሚያደርግ በዘር የሚተላለፍ አንድ ዓይነት እንከን እንዳለባቸው ተገንዝበዋል። በቅርቡ የተወሰኑ ሳይንቲስቶች በቡድን ሆነው ሰፊ ጥናት ካካሄዱ በኋላ “አንዴ የሕይወት ሞተር ከተለኮሰ ሰውነት አይቀሬ የሆነውን የገዛ ጥፋቱን ዘር ይዘራል፤ ይህ ማንም ሰው ቢሆን ሊያመልጠው የማይችለው ባዮሎጂያዊ ሐቅ ነው” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

በሽታ የሌለበት ዓለም የሚመጣው በሰው ጥረት አይደለም ሳይንስ ከበሽታ ጋር በሚደረገው ፍልሚያ ታላላቅ ድሎችን በመቀዳጀት ላይ ይገኛል። ይሁን እንጂ የበሽታ መንስኤ ሳይንስ የተሟላ መፍትሔ ሊያገኝለት የማይችል ውስብስብ ነገር መሆኑ ተረጋግጧል። “በገዦች አትታመኑ፤ ማዳን በማይችሉ ሥጋ ለባሾችም አትመኩ” የሚሉትን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ ቃላት ጠንቅቀው የሚያውቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዚህ አይደነቁም።—መዝሙር 146:3

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻላል።” (ሉቃስ 18:27) ይሖዋ አምላክ የበሽታን መንስኤ ጨርሶ ሊያስወግድ ይችላል። ወደፊት ደዌያችንንም ሁሉ ይፈውሳል። (መዝሙር 103:3) በመንፈሱ አነሳሽነት የተጻፈው ቃሉ እንደሚከተለው በማለት ተስፋ ይሰጣል:- “እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፎአልና።”—ራእይ 21:3, 4

ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ኢየሱስ ክርስቶስ በሽታ በማይኖርበት ዓለም ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል ለመገኘት ምን ማድረግ እንዳለብን በግልጽ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል:- “እውነተኛ አምላክ የሆንኸውን አንተንና የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።”—ዮሐንስ 17:3

ስለ አምላክ የሚገልጸው እውቀትና ልጁ ኢየሱስ ያስተማረው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። እንዲህ ዓይነቱ እውቀት አሁንም ቢሆን ሕይወትህን ሊያሻሽልልህ የሚችል ጠቃሚ ምክርም ይዟል። ከሁሉ በላይ ግን አምላክ ታዛዥ ለሆኑ አምላኪዎቹ ሥቃይ የሌለበት ዓለም እንደሚያመጣ ቃል ገብቷል። አዎን፣ አምላክ ‘ታምሜአለሁ የሚል የማይኖርበትን’ ጊዜ አዘጋጅቶልሃል!—ኢሳይያስ 33:24

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ስለ ጤንነት ሊኖረን የሚገባው ሚዛናዊ አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስ ለሕይወት አክብሮት እንዲኖረን ያበረታታል። የይሖዋ ምሥክሮች ጤንነታቸውን ለመንከባከብ አስፈላጊውን ጥረት በማድረግ እንዲህ ያለው አክብሮት እንዳላቸው ያሳያሉ። ዕፅ መውሰድንና ትንባሆ ማጨስን ከመሳሰሉ ጎጂ ድርጊቶች ይርቃሉ። አምላክ እርሱን የሚያመልኩ ሰዎች በመጠጥና በአመጋገብ ልማዳቸው ረገድ ልከኞች እንዲሆኑ ይጠብቅባቸዋል። (ምሳሌ 23:20፤ ቲቶ 2:2, 3) እንዲህ ያሉት ተግባራዊ እርምጃዎች በቂ እረፍትና አካላዊ እንቅስቃሴ ሲታከልባቸው ብዙ በሽታዎችን ለመከላከል አሊያም በበሽታዎች የመያዝ አጋጣሚዎችን ለመቀነስ ይረዳሉ። የጤና እክል ያጋጠማቸው ሰዎች ደግሞ እምነት የሚጣልባቸው የጤና ባለሞያዎች የሚሰጡት እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታዊ እንድንሆንና “ጤናማ አስተሳሰብ” እንዲኖረን ያበረታታል። (ቲቶ 2:12 NW፤ ፊልጵስዩስ 4:5 NW) በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ሚዛናቸውን ስተው ከበሽታቸው ለመፈወስ የሚያስችላቸውን መፍትሔ ለማግኘት ከልክ በላይ ከመጨነቃቸው የተነሳ መንፈሳዊነታቸውን ችላ እስከ ማለት ደርሰዋል። አንዳንዶች ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ አጠያያቂ የሕክምና ዓይነቶችን ለመከታተል ይመርጣሉ። ሌሎች ደግሞ ውጤት ለሌላቸው፣ አልፎ ተርፎም ጎጂ ለሆኑ ሕክምናዎችና መድኃኒቶች ሲሉ ገንዘባቸውን ብሎም ጊዜያቸውን ያባክናሉ።

እውነታው ግን በአሁኑ ጊዜ ፍጹም ጤንነት ሊገኝ የማይችል መሆኑ ነው። በሽታ የማይኖርበትን ጊዜ ከመጠባበቅ ጎን ለጎን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክርና ምክንያታዊ አመለካከት መቅሰምህ ጥሩ ጤንነት ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ሚዛናዊ ሆነህ እንድትቀጥል ይረዳሃል።