በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

በ15 ወራት ጊዜ ውስጥ 82 ጨቅላ ሕፃናት በሜክሲኮ ሲቲ አውራ ጎዳናዎች ላይ ተጥለው የተገኙ ሲሆን 27ቱ ሕይወታቸው አልፎ ነበር።—ኤል ዩኒቨርሳል፣ ሜክሲኮ

በካሊፎርኒያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኙ ሁለት ብሔራዊ ፓርኮች ውስጥ ባሉ ዋሻዎች ላይ በተደረገ ጥናት 27 ዓይነት አዳዲስ የእንስሳት ዝርያዎች ተገኝተዋል። “ይህ በዙሪያችን ስላለው ዓለም የምናውቀው በጣም ትንሽ መሆኑን ያረጋግጣል” በማለት በብሔራዊ ፓርኩ ውስጥ ከዋሻ ጋር የተያያዘ ሥራ የሚያከናውኑት ጆኤል ዴስፔን ተናግረዋል።—ስሚዝሶኒያን፣ ዩናይትድ ስቴትስ

ሃያ በመቶ የሚሆነው የዓለም ሕዝብ ንጹሕ የመጠጥ ውኃ አያገኝም። አርባ በመቶ የሚሆነው ደግሞ መሠረታዊ የሆነውን የመጸዳጃ አገልግሎት አያገኝም።ሚሌንዮ፣ ሜክሲኮ

ሕገ ወጥ አዳኞች ከሴረንጌቲ ብሔራዊ ፓርክ ብቻ በየዓመቱ ከ20,000 እስከ 30,000 የሚደርሱ እንስሳትን ይገድላሉ።ዘ ዴይሊ ኒውስ፣ ታንዛኒያ

በባርሴሎና፣ ስፔን የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ዕድሜያቸው 16 ዓመት ከሆኑ ሦስት ተማሪዎች መካከል አንዱ ካናቢስ የሚባለውን አደገኛ ዕፅ አዘውትሮ ያጨሳል።ላ ባንግዋርድያ፣ ስፔን

በቢሮ ውስጥ ያሉ ጀርሞች

የአሪዞና ዩኒቨርሲቲ ማይክሮባዮሎጂስቶች በበርካታ የዩናይትድ ስቴትስ ከተሞች በሚገኙ ቢሮዎች ውስጥ ምን ያህል ባክቴሪያ እንደሚገኝ ጥናት አድርገው ነበር። “ብዛት ያለው ጀርም የተገኘባቸው አምስቱ ቦታዎች (በቅደም ተከተል ሲቀመጡ) ስልኮች፣ የቢሮ ጠረጴዛዎች፣ የቧንቧ መዝጊያና መክፈቻዎች፣ የማይክሮዌቭ ምድጃ በር እጀታ እና የኮምፒውተር መተየቢያ ቁልፎች” መሆናቸውን እንደደረሱበት ግሎብ ኤንድ ሜይል የሚባለው ጋዜጣ ይናገራል። ዘገባው በገለጸው መሠረት “በአማካይ በቢሮ ጠረጴዛዎች ላይ የሚገኘው ባክቴሪያ ብዛት በኩሽና ጠረጴዛ ላይ ከሚገኘው በ100 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን በመጸዳጃ ቤት መቀመጫ ላይ ካለው ባክቴሪያ ደግሞ በ400 እጥፍ ይበልጣል።”

‘በተግባር የማይታይ ክርስትና’

በእስያ ካሉት አገሮች ሁሉ “ክርስቲያን” የሆነችው ፊሊፒንስ ብቻ እንደሆነች ይነገራል። ይሁን እንጂ የፊሊፒን የወንጌላውያን ቤተ ክርስቲያን ምክር ቤት ጳጳስ የሆኑት ኤፍራኢን ቴንዴሮ “ብዙዎቻችን ክርስቲያን እንደሆንን ብንናገርም ተግባራችን ግን ይህን አያሳይም” ብለዋል። በማኒላ ቡሌቲን ላይ እንደተገለጸው ለዚህ ሁኔታ በከፊል ተወቃሾቹ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ናቸው፤ እነዚህ መሪዎች ሕዝቡ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያውቅና መጽሐፉን ከፍ አድርጎ እንዲመለከተው መርዳት” አልቻሉም። አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን ስብከቶች ከቅዱሳን መጻሕፍት ይልቅ በፖለቲካ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

ሰዎችና እንስሳት በቀለብ ተጣሉ

“ድርቅ ባጠቃት ሶማሊያ፣ ዝንጀሮዎችና ጅቦች ሕዝቡን እንዳስቸገሩ የሚገልጽ ዜና መስማት የተለመደ እየሆነ ነው” በማለት ዚ ኢስት አፍሪካን የተሰኘው የናይሮቢ ጋዜጣ ይናገራል። በአንድ ወቅት ከውኃ ጋር በተያያዘ በተፈጠረ ጠብ ምክንያት በርካታ ዝንጀሮዎች ሲሞቱ አንዳንድ ከብት አርቢዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። የዝንጀሮ መንጋዎች በአካባቢው ወደሚገኝ ገበያ ምግብ ጭነው የሚያልፉ መኪኖችን ለመዝረፍ “አመቺ በሆኑ መንገዶች ወይም ድልድዮች” ላይ አድፍጠው እንደሚጠብቁ ይነገራል። ጋዜጣው አክሎም እነዚህ እንስሳት “የሙዝ እስሮችን ወይም ትላልቅ ሃብሃቦችን ቀምተው ሲሮጡ ማየት የተለመደ ነው” ብሏል።

መርከቦች በባሕር አካባቢ ባለው የአየር ጠባይ ላይ ተጽዕኖ ያደርጋሉ

መርከቦች በሚበዙባቸው ቦታዎች በባሕሩ አካባቢ ያለው የአየር ጠባይ ሊለወጥ እንደሚችል ኮልነ ሽታትአንጻይግ የተሰኘ የጀርመን ጋዜጣ ዘገበ። ሃምበርግ በሚገኘው ማክስ ፕላንክ የተባለ የሚቲዮሮሎጂ ተቋም የሚገኙት ተመራማሪዎች ኢንግሊሽ ቻናል በሚባለው የውኃ አካል አካባቢ ደመና የሚፈጠርበትን መንገድ በተመለከተ ጥናት አካሂደው ነበር። በባሕር ዳርቻዎች አካባቢ ደመናው ስስ እንደሆነና ወደ ባሕሩ መሃል አካባቢ ግን ደመናው ይበልጥ ጥቅጥቅ ያለ እንደሚሆን ደርሰውበታል። ይህ ክስተት ከመርከቦች ከሚወጣው ጭስ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተገልጿል። ከመርከቦቹ ጭስ ጋር በሚወጣው የጥላሸት ብናኝ ላይ የሚከማቸው ጤዛ ጥቃቅን የውኃ ነጠብጣቦች በብዛት እንዲፈጠሩ እንደሚያደርግ ይታመናል። ጋዜጣው እንደገለጸው “ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ የመርከቦች የነዳጅ ፍጆታ ከአራት እጥፍ በላይ አድጓል።”