በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት መጀመር የምችለው መቼ ነው?

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት መጀመር የምችለው መቼ ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት መጀመር የምችለው መቼ ነው?

ትምህርት ቤት ውስጥ ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው ጋር ጓደኛ ካልሆናችሁ ችግር እንዳለባችሁ ይሰማችኋል!—ብሪተኒ

“የወንድ ጓደኛ እንድይዝ ከየአቅጣጫው ግፊት ይደረግብኛል። ደግሞም ብዙ ቆንጆ ቆንጆ ወንዶች አሉ።”ዊትኒ

ትምህርት ቤት ውስጥ አንድ ወንድና አንዲት ሴት እጅ ለእጅ ተያይዘው ኮሪደር ላይ ሲንሸራሸሩ ተመለከታችሁ እንበል። ምን ይሰማችኋል?

ምንም አይመስለኝም

ትንሽ የቅናት ስሜት ይሰማኛል

በጣም እቀናለሁ

ከጓደኞቻችሁ ጋር ፊልም ቤት ሄዳችሁ ሳለ ከእናንተ በስተቀር ሁሉም ጥንድ ጥንድ መሆናቸውን አስተዋላችሁ እንበል! ምን ይሰማችኋል?

ምንም አይመስለኝም

ትንሽ የቅናት ስሜት ይሰማኛል

በጣም እቀናለሁ

የቅርብ ወዳጃችሁ ሰሞኑን ተቃራኒ ጾታ ያለው አንድ ሰው ወድዶ ጓደኝነት መሥርቷል እንበል። ምን ይሰማችኋል?

ምንም አይመስለኝም

ትንሽ የቅናት ስሜት ይሰማኛል

በጣም እቀናለሁ

ከላይ ለሰፈሩት ጥያቄዎች “ትንሽ የቅናት ስሜት ያድርብኛል” ወይም “በጣም እቀናለሁ” የሚል መልስ ሰጥታችሁ ከሆነ እንዲህ የሚሰማችሁ እናንተ ብቻ አይደላችሁም። ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት መመሥረት በተለመደባቸው አገሮች የሚገኙ ብዙ ወጣቶች ተመሳሳይ መልስ ሊሰጡ ይችላሉ። የ14 ዓመቷ ኢቬት፣ “እኩዮቻችሁ ሁሉ የወንድ ጓደኛ ኖሯቸው እናንተ ከሌላችሁ አንዳንድ ጊዜ የሆነ ነገር እንደቀረባችሁ ይሰማችኋል” ብላለች።

የተለየ የፍቅር ስሜት ከሚያሳያችሁና እናንተም ከወደዳችሁት ሰው ጋር ለመሆን ያላችሁ ፍላጎት በጣም ኃይለኛ ሊሆን ይችላል። በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ አንድ ወጣት፣ “የሴት ጓደኛ ለመያዝ ያለኝ ፍላጎት ከቀን ወደ ቀን እያየለ ስለሚሄድ ይህን ስሜት መቋቋም በጣም ይከብዳል!” ሲል ተናግሯል። እንዲያውም አንዳንዶቹ ጓደኛ መያዝ የሚጀምሩት ገና በለጋ ዕድሜያቸው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ታይም የተሰኘው መጽሔት ያደረገው አንድ ጥናት እንዳመለከተው 13 ዓመት ከሆናቸው ልጆች መካከል 25 በመቶ የሚያህሉት “ጓደኛ” አላቸው። እነዚህ ልጆች ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ እንደሆኑ ይሰማችኋል? እናንተስ እንዲህ ዓይነቱን ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ናችሁ? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከመስጠታችን በፊት ይበልጥ መሠረታዊ የሆነ አንድ ጥያቄ ማንሳታችን ተገቢ ነው።

ጓደኛዬ ነው የምትሉት ማንን ነው?

ተቃራኒ ጾታ ካለው አንድ ሰው ጋር በተደጋጋሚ ጊዜ እየተገናኛችሁ ትጫወታላችሁ።

ይህ ሰው ጓደኛችሁ ነው? አዎ አይደለም

ተቃራኒ ጾታ ላለው አንድ ሰው በቀን ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት በሞባይል መልእክት ትልካላችሁ አሊያም በስልክ ታወራላችሁ።

ይህ ሰው ጓደኛችሁ ነው? አዎ አይደለም

ተቃራኒ ጾታ ካለው አንድ ሰው ጋር በድብቅ ትገናኛላችሁ። ወላጆቻችሁ ስለዚህ ጉዳይ የሚያውቁት ነገር የለም። ያልነገራችኋቸው እንደሚቃወሟችሁ ስለምታውቁ ነው።

ይህ ሰው ጓደኛችሁ ነው? አዎ አይደለም

ከጓደኞቻችሁ ጋር ጊዜ ስታሳልፉ ሁልጊዜ ተቃራኒ ጾታ ካለው ከአንዱ ሰው ጋር ብቻ አብራችሁ ትሆናላችሁ።

ይህ ሰው ጓደኛችሁ ነው? አዎ አይደለም

የመጀመሪያውን ጥያቄ በቀላሉ መልሳችሁት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ሌሎቹን ጥያቄዎች ለመመለስ ፈራ ተባ ብላችሁ ይሆናል። በእርግጥ ጓደኛችሁ ነው ሊባል የሚችለው ማን ነው? ካነሳነው ርዕሰ ጉዳይ አንጻር በማንኛውም ማኅበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ለምታገኙት አንድ ግለሰብ የፍቅር ስሜት ካደረባችሁና ያም ሰው ለእናንተ ተመሳሳይ ስሜት ካለው ጓደኛችሁ ነው ሊባል ይችላል። በቡድን ሆናችሁም ይሁን ለብቻችሁ፣ በስልክም ይሁን በአካል ወይም ደግሞ በግልጽም ይሁን በድብቅ፣ ተቃራኒ ጾታ ካለው አንድ ሰው ጋር የፍቅር ግንኙነት ካላችሁ ጓደኛሞች ናችሁ ማለት ነው።

ይሁንና በዚህ መንገድ ጓደኝነት ለመመሥረት ዝግጁ ናችሁ? ለሚከተሉት ሦስት ጥያቄዎች የሚሰጠው ማብራሪያ ዝግጁ መሆን አለመሆችሁን እንድትገነዘቡ ይረዳችኋል።

ዓላማችሁ ምንድን ነው?

በብዙ ባሕሎች ውስጥ ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ሁለት ሰዎች በሚገባ ለመተዋወቅ ሲሉ ጓደኝነት መመሥረታቸው ተቀባይነት ያለው ድርጊት ተደርጎ ይታያል። ነገር ግን እንዲህ ያለውን ጓደኝነት መመሥረት ከዚህም የተሻለ ዓላማ ሊኖረው ይገባል፤ ይኸውም አንድ ወንድና አንዲት ሴት እንዲህ ያለውን ግንኙነት መጀመር ያለባቸው ተስማሚ የትዳር ጓደኛሞች መሆን ይችሉ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማየት መሆን ይኖርበታል። ለምን?

መጽሐፍ ቅዱስ የጾታና የፍቅር ስሜቶች የሚያይሉበትን የዕድሜ ክልል ለማመልከት ‘አፍላ የጉርምስና ዕድሜ’ የሚለውን ሐረግ ይጠቀማል። (1 ቆሮንቶስ 7:36 NW) ‘በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ’ ውስጥ እያላችሁ ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረታችሁ እንዲህ ያለውን ስሜት ይበልጥ ያቀጣጥለዋል። ከዚህም በላይ በገላትያ 6:7 ላይ የሚገኘውን “ሰው የሚዘራውን ያንኑ ያጭዳል” የሚለውን ሐቅ ከችግር ለመማር ትገደዳላችሁ።

አንዳንድ እኩዮቻችሁ ምንም የጋብቻ ዕቅድ ሳይኖራቸው ከተቃራኒ ጾታ ጋር ወዳጅነት እንደሚመሠርቱ የታወቀ ነው። እነዚህ ሰዎች ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው ጋር ጓደኝነት መመሥረቱንና እንዲህ ካለ ሰው ጋር በአደባባይ መታየቱን እንደ ጀብዱ ይቆጥሩት ይሆናል። ሆኖም እንዲህ እያደረጉ በሰው ስሜት መጫወት ጭካኔ ነው። በመሆኑም ይህ ዓይነቱ ወዳጅነት አብዛኛውን ጊዜ ዘላቂ አለመሆኑ ምንም አያስደንቅም። ሄዘር የተባለች አንዲት ወጣት “ተቃራኒ ጾታ ካለው ሰው ጋር ጓደኝነት የሚመሠርቱ ብዙ ወጣቶች በአንድ ወይም በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ግንኙነታቸው ይቋረጣል” ብላለች። አክላም “እነዚህ ወጣቶች የመሠረቱትን ጓደኝነት ወደ ጋብቻ ሳይሆን ወደ ፍቺ የሚያሸጋግራቸው ጊዜያዊ ግንኙነት አድርገው ይመለከቱታል” ብላለች።

ለመዝናናት አሊያም የወንድ ጓደኛ ወይም የሴት ጓደኛ አለኝ ለማለት ያህል ብቻ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት መመሥረት በቀላሉ የስሜት ጉዳት ሊያደርስ ይችላል። የ18 ዓመት ልጅ ሳለ በቅን ልቦና ተነሳስቶ ከአንዲት ልጅ ጋር መቀራረብ የጀመረውን ኤሪክን እንውሰድ። ይህ ወጣት ከተራ ጓደኝነት ያለፈ ግንኙነት የመመሥረት ሐሳብ አልነበረውም። በኋላ ግን ልጅቷ ለግንኙነታቸው የተለየ ትርጉም እንደሰጠችው አስተዋለ። “ብዙም ሳንቆይ እያመረረች መምጣቷ አስገረመኝ! እኔ እንኳ ተራ ጓደኝነት የመሠረትን ነበር የመሰለኝ!” ብሏል።

እርግጥ ነው፣ ተገቢው ቁጥጥር እስከተደረገ ድረስ ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ወጣቶች ጋር ጊዜ ማሳለፉ ምንም ስህተት የለውም። ጓደኝነት መመሥረትን በተመለከተ ግን አፍላ የጉርምስና ዕድሜያችሁ እስኪያልፍና ስለ ጋብቻ በቁም ነገር ማሰብ እስከምትጀምሩበት ጊዜ ድረስ ብትታገሱ መልካም ነው። ቼልሲ የተባለች ወጣት ይህን ሐሳብ ተገንዝባለች። “አንዳንድ ጊዜ ጓደኛ የሚያዘው ሁኔታው ደስ የሚል ስሜት ስለሚፈጥር ብቻ እንደሆነ ይሰማኛል” በማለት ሐቁን ሳትሸሽግ ተናግራለች። አክላም “ይሁን እንጂ አንደኛው ወገን በቁም ነገር ተመልክቶት ሌላኛው ወገን ምንም ካልመሰለው እንደዚያ ብሎ ማሰብ ከባድ ነው” ብላለች።

ዕድሜያችሁ ስንት ነው?

አንድ ወጣት ተቃራኒ ጾታ ያለው ጓደኛ ለመያዝ ብቁ እንደሆነ የሚሰማችሁ ስንት ዓመት ሲሆነው ነው? ______

አሁን ደግሞ ከወላጆቻችሁ አንዱን ወይም ሁለቱንም ይህንኑ ጥያቄ ጠይቋቸውና የሚሰጧችሁን መልስ ጻፉ። ______

የመጀመሪያው ቁጥር ከሁለተኛው የማነሱ አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። የመብለጥ አጋጣሚ ሊኖረውም ይችላል! እንደ ብዙዎቹ ወጣቶች ሁሉ አንተም ራስህን በደንብ የምታውቅበት ዕድሜ ላይ እስክትደርስ ድረስ የተቃራኒ ጾታ ጓደኛ ከመያዝ መቆጠቡ አስተዋይነት እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። ሶንድራ የተባለች ክርስቲያን ወጣት በሕግ ለማግባት በሚያስችላት የዕድሜ ክልል ውስጥ ብትሆንም እንኳ ተመሳሳይ እርምጃ ለመውሰድ ወስናለች። ሶንድራ ምክንያቷን ስትገልጽ እንዲህ ብላለች:- “ጓደኛችሁ አብራችሁ በምታሳልፉት ጊዜ ውስጥ በደንብ እንዲያውቃችሁ ትፈልጋላችሁ። ይሁን እንጂ እናንተ ራሳችሁን ሳታውቁት ሌላው እንዲያውቃችሁ እንዴት መጠበቅ ትችላላችሁ?”

የ17 ዓመቷ ዳንየልም ተመሳሳይ አመለካከት አላት። እንዲህ ብላለች:- “ከሁለት ዓመት በፊት የነበረኝን አመለካከት መለስ ብዬ ሳስበው ያኔ ጓደኛዬ እንዲሆን ከምፈልገው ሰው እጠብቀው የነበረውን ነገር ከአሁኑ ጋር ሳወዳድረው ብዙ ልዩነት አለው። በመሠረቱ አሁንም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ውሳኔ ማድረግ እችላለሁ ብዬ በራሴ አልተማመንም። የተረጋጋ አቋም እንዳለኝ ሆኖ ሲሰማኝ የዚያን ጊዜ የወንድ ጓደኛ ስለ መያዝ ማሰብ እጀምራለሁ።”

ለማግባት ዝግጁ ናችሁ?

ከተቃራኒ ጾታ ጋር የምትመሠርቱት ወዳጅነት ወደ ትዳር የሚያሻግራችሁ አንድ እርምጃ እንደመሆኑ መጠን ባል ወይም ሚስት አልፎ ተርፎም አባት ወይም እናት መሆን የሚያስከትለውን ኃላፊነት ለመሸከም ብቁ ነኝ ወይ? ብላችሁ ራሳችሁን መጠየቃችሁ አስፈላጊ ነው። ይህን ኃላፊነት ለመቀበል የሚያስችል ብቃት ይኖራችሁ እንደሆነ ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በሉ።

ከሌሎች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ወላጆቻችሁን ብሎም ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን የምትይዙት እንዴት ነው? ከእነርሱ ጋር ስትሆኑ ብዙ ጊዜ ራሳችሁን መቆጣጠር ተስኗችሁ ሐሳባችሁን ለመግለጽ ሻካራ ቃል አሊያም የሽሙጥ አነጋገር ትጠቀማላችሁ? ይህን ጉዳይ በተመለከተ እነርሱስ ስለ እናንተ ምን ይላሉ? የቤተሰባችሁን አባላት የምትይዙበት መንገድ የትዳር ጓደኛ ቢኖራችሁ እንዴት እንደምትይዙት ይጠቁማል።—ኤፌሶን 4:31, 32

የገንዘብ አያያዝ ጥሩ የገንዘብ አያያዝ ችሎታ አላችሁ? ሁልጊዜ ትበደራላችሁ? በአንድ ሥራስ ትጸናላችሁ? የማትጸኑ ከሆነ ለምን? በሥራው አሊያም በአሠሪያችሁ ምክንያት ነው? ወይስ አንዳንድ መጥፎ ባሕርያት ስላሏችሁ? ኃላፊነት ተሰምቷችሁ ገንዘባችሁን በአግባቡ መያዝ ካልቻላችሁ እንዴት አድርጋችሁ ቤተሰብ ማስተዳደር ትችላላችሁ?—1 ጢሞቴዎስ 5:8

መንፈሳዊነት የይሖዋ ምሥክር ከሆናችሁ መንፈሳዊ እንደሆናችሁ የሚጠቁሙ ምን ምን ባሕርያት አሏችሁ? ማንም ሳይጎተጉታችሁ የአምላክን ቃል ለማንበብ፣ በአገልግሎቱ ለመካፈልና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመሳተፍ ጥረት ታደርጋላችሁ? የራሳችሁን መንፈሳዊነት የማትገነቡ ከሆነ የትዳር ጓደኛ ቢኖራችሁ መንፈሳዊ ሰው እንዲሆን እንዴት ልታበረታቱት ትችላላችሁ?—2 ቆሮንቶስ 13:5

ከላይ የቀረቡት ሐሳቦች ተቃራኒ ጾታ ያለው ጓደኛ ለመያዝም ይሁን ትዳር ለመመሥረት ከማሰባችሁ በፊት ልታስቡባቸው የሚገቡ ጥቂት ነጥቦች ናቸው። እስከዚያው ድረስ ግን ተገቢ ቁጥጥር በሚደረግባቸው ዝግጅቶች ላይ ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ወጣቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ትችላላችሁ። ከጊዜ በኋላ የተቃራኒ ጾታ ጓደኛ ለመያዝ ስትወስኑ ራሳችሁንም ሆነ የዕድሜ ልክ ተጓዳኝ እንዲሆናችሁ የምትመርጡትን ሰው በተሻለ ሁኔታ ልታውቁ ትችላላችሁ።

ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው?

ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ይህን መጽሐፍ ገጽ 13-26 መመልከት ትችላላችሁ።

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “የወጣቶች ጥያቄ . . .” በሚለው ቋሚ አምድ ሥር የወጡ ሌሎች ርዕሶችንም ማግኘት ይቻላል

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ወጣቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ ብትፈልጉ ምን መደረግ ይኖርበታል?

▪ ተስማሚ የትዳር ጓደኛ ለመሆን በይበልጥ የትኛውን ባሕርይ ማዳበር ይኖርባችኋል?

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

አንዳንድ እኩዮቻችሁ እንደሚከተለው ብለዋል:-

“አንዳንድ ጊዜ ወንድና ሴት ጓደኛሞች ስመለከት ሌላው ቀርቶ የተጋቡ ሰዎች እንኳ ሳይ የቅናት ስሜት ያድርብኛል። ይሁን እንጂ የሴት ጓደኛ መያዝ እንዲያው ደስ ስለሚል ብቻ የሚደረግ አይደለም። ለዚህ ብላችሁ ብቻ ጓደኛ ከያዛችሁ በሰው ስሜት እየተጫወታችሁ ነው። እኔ እንደሚመስለኝ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት የሚመሠረትበት ምክንያት ግለሰቡ ልታገቡት የምትፈልጉት ዓይነት ሰው መሆኑን ለማረጋገጥ ተብሎ መሆን ይኖርበታል።” —የ17 ዓመቱ ብሌን

“ወደፊት ወዳጅነት ስትመሠርቱ የሚኖረው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማወቅ ስትሉ ብቻ የወንድ ጓደኛ መያዙ ጥሩ ነው ብዬ አላስብም። እንዲህ ዓይነቱ ድርጊት የሌላውን ሰው ስሜት ከመጉዳት ያለፈ ፋይዳ የለውም።”—የ17 ዓመቷ ቼልሲ

“ጓደኛ ከመያዛችሁ በፊት ትዳር ለመመሥረት የሚያስችላችሁ ዕድሜ ላይ መድረስ የሚኖርባችሁ ይመስለኛል። አለበለዚያ ግን ሁኔታው ገና ተማሪ ሆናችሁና ሥራ የመግባት ዕቅድ ሳትይዙ ቃለ መጠይቅ እንዲደረግላችሁ ወደ አንድ መሥሪያ ቤት የመሄድ ያህል ይሆንባችኋል።”

—የ21 ዓመቷ ሶንድራ

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ለወላጆች የተሰጠ ምክር

ይዋል ይደር እንጂ ልጆቻችሁ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ጓደኝነት እንዲመሠርቱ ግፊት ሳይደረግባቸው አይቀርም። “እኔ’ኮ ምንም ማድረግ አይጠበቅብኝም!” ይላል ፊሊፕ። “ሴቶቹ ጓደኛ እንድሆናቸው መጥተው ሲጠይቁኝ፣ ‘እሺ አሁን ምንድን ነው የማደርገው?’ ብዬ አስባለሁ። አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም ቆንጆዎች ስለሆኑ እምቢ የምልበት አንደበት አጣለሁ!”

ወላጅ እንደመሆናችሁ መጠን ልትወስዱት የምትችሉት ከሁሉ የተሻለው እርምጃ ጓደኛ መያዝን በተመለከተ ከልጆቻችሁ ጋር መነጋገር ነው። በዚህ ርዕስ ላይ የተሰጠውን ሐሳብ መሠረት አድርጋችሁ ለምን አትወያዩም? ልጆቻችሁ በትምህርት ቤትም ሆነ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ስለሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ምን እንደሚሰማቸው ለማወቅ ጣሩ። አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ያለውን ውይይት ‘ቤታችሁ ተቀምጣችሁ ወይም በመንገድ ስትሄዱ’ አሊያም በሌላ አጋጣሚ ልታደርጉት ትችላላችሁ። (ዘዳግም 6:6, 7) ውይይቱን የትም አደረጋችሁት የት ‘ለመስማት የፈጠናችሁ፣ ለመናገር የዘገያችሁ’ መሆን እንዳለባችሁ አትዘንጉ።—ያዕቆብ 1:19

ልጃችሁ ተቃራኒ ጾታ ካለው አንድ ሰው ጋር ፍቅር እንደያዘው ቢነግራችሁ አትደናገጡ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የምትገኝ አንዲት ወጣት “አባቴ የወንድ ጓደኛ እንዳለኝ ሲያውቅ በጣም ተበሳጨ!” ስትል ተናግራለች። አክላም “ለማግባት የተዘጋጀሁ መሆን አለመሆኔን በተመለከተ የተለያዩ ጥያቄዎችን በመጠየቅ ሊያስፈራራኝ ሞክሮ ነበር። ይህ ደግሞ ወጣቶች ወላጆቻቸው እንደተሳሳቱ ለማሳየት ሲሉ ግንኙነታቸውን እንዲገፉበት ያነሳሳቸዋል!”

ልጆቻችሁ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ወዳጅነት ስለ መመሥረት ማውራት እንደሌለባቸው ከተሰማቸው አንድ አሳዛኝ ሁኔታ ሊከሰት ይችላል:- ግንኙነታቸውን በድብቅ ለማድረግ ወስነው በምስጢር ሊገናኙ ይችላሉ። አንዲት ወጣት እንዲህ ስትል ተናግራለች:- “የወላጆች መቆጣት የሚያተርፈው ነገር ቢኖር ልጆቹ ግንኙነታቸውን ይበልጥ በድብቅ እንዲያደርጉት መገፋፋት ብቻ ነው። መገናኘታቸውን አያቆሙም። ይልቁን አታላይ መሆን ይጀምራሉ።”

በግልጽ በመነጋገር የተሻለ ውጤት ማግኘት ትችላላችሁ። አንዲት የ20 ዓመት ወጣት እንዲህ ብላለች:- “ሁልጊዜ ወላጆቼ የተቃራኒ ጾታ ጓደኛ ስለመያዝ በግልጽ ያነጋግሩኝ ነበር። ማንን እንደወደድኩ ማወቃቸው አስፈላጊ ነው። ይህ ደግሞ ጥሩ እንደሆነ ይሰማኛል! አባቴ የወደድኩትን ሰው ያናግረዋል። ወላጆቼ ምንም ዓይነት አሳሳቢ ሁኔታ ካለ ያሳውቁኛል። ስለዚህ አብዛኛውን ጊዜ ጓደኝነት ከመመሥረቴ በፊት ያ ሰው ቢቀርብኝ ይሻላል ብዬ እወስናለሁ።”

[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሥርዓታማ እስከሆነ ድረስ ተቃራኒ ጾታ ካላቸው ወጣቶች ጋር ጊዜ ማሳለፍ አስደሳችና ጠቃሚ ሊሆን ይችላል