በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ኢየሱስ ክርስቶስ ማን ነው?

ተአማኒነት ያለው የታሪክ ዘገባ እንደሚያረጋግጠው ከ2,000 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ኢየሱስ የሚባል አንድ ሰው በይሁዳ ምድር በምትገኘው ቤተ ልሔም በተባለች ትንሽ ከተማ ተወለደ። በወቅቱ ታላቁ ሄሮድስ በኢየሩሳሌም ንጉሥ የነበረ ሲሆን አውግስጦስ ቄሳር ደግሞ ንጉሠ ነገሥት ሆኖ በሮም ይገዛ ነበር። (ማቴዎስ 2:1፤ ሉቃስ 2:1-7) በዚያን ጊዜ ሮማውያን ገዢዎች ክርስትናን ለማጥፋት ሙከራ ያደርጉ ስለነበር በመጀመሪያዎቹ ሁለት መቶ ዘመናት የኖሩ ሮማውያን ታሪክ ጸሐፊዎች በአጠቃላይ ስለ ኢየሱስ ከመጻፍ ተቆጥበዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ ዘ ሂስቶሪያን ሂስትሪ ኦቭ ዘ ወርልድ እንዲህ ይላል:- “[ኢየሱስ] ያደረጋቸው ነገሮች በታሪክ ላይ ያስከተሉት ውጤት ከሃይማኖታዊ አመለካከት ውጪ ሲታይ እንኳን ማንኛውም ሰው ካሳደረው ተጽዕኖ እጅግ የሚልቅ ነው። በዓለም ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ ላይ በደረሱ አገራት ዘንድ እውቅና ያገኘው አዲስ ዘመን የጀመረው [ከኢየሱስ] ልደት ወዲህ ነው።”

በታሪክ ውስጥ ከነበረ ከማንኛውም ሰው በበለጠ ስለ ኢየሱስ በርካታ መጻሕፍት እንደተጻፉ ታይም መጽሔት ዘግቧል። ከእነዚህ መጻሕፍት መካከል አብዛኞቹ የሚያተኩሩት በኢየሱስ ማንነት ላይ ነው። በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የኢየሱስን ማንነት ያህል የሚያከራክር ጉዳይ አልተነሳም ለማለት ይቻላል።

በኢየሱስ ዘመን ስለ ማንነቱ የተነሱ ጥያቄዎች

ማርያም ልጅ እንደምትወልድና ስሙን ኢየሱስ እንደምትለው በተነገራት ጊዜ “እኔ ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?” የሚል ጥያቄ አንስታ ነበር። ከዚያም የአምላክ መልአክ የሆነው ገብርኤል “የልዑልም ኀይል ይጸልልሻል፤ ስለዚህ የሚወለደው ቅዱሱ ሕፃን፣ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” በማለት መልስ ሰጣት።—ሉቃስ 1:30-35

ቆይቶም ኢየሱስ ሐዋርያቱን ያስደነቁ ተአምራት ፈጸመ። በገሊላ ባሕር ላይ ሲጓዙ ጀልባቸውን ኃይለኛ አውሎ ነፋስ በማናወጥ ሊያሰምጣት በደረሰበት ጊዜ ኢየሱስ ውኃውን “ጸጥ፣ ረጭ በል!” ብሎ በመገሠጽ ዝም አሰኘው። ሐዋርያቱ በሁኔታው በመገረም “ይህ ማን ነው?” ተባባሉ።—ማርቆስ 4:35-41፤ ማቴዎስ 8:23-27

በኢየሱስ ዘመን ሰዎች ስለ እርሱ እውነተኛ ማንነት መጠየቃቸው የተለመደ ሆኖ ስለነበር እርሱን በተመለከተ ምን እንደሚባል ሐዋርያቱን ጠየቃቸው። እነርሱም “አንዳንዶቹ መጥምቁ ዮሐንስ፣ ሌሎች ኤልያስ፣ ሌሎች ደግሞ ኤርምያስ ወይም ከነቢያት አንዱ ነው ይላሉ” ብለው መለሱለት። በወቅቱ እነዚህ ሰዎች በሙሉ ሞተው ነበር። ከዚያም ኢየሱስ “‘እናንተስ እኔን ማን ትሉኛላችሁ?’ አላቸው። ስምዖን ጴጥሮስም፣ ‘አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ’ በማለት መለሰ።” ክፉ መላእክት የሆኑት አጋንንት እንኳን ኢየሱስን “አንተ የእግዚአብሔር ልጅ ነህ!” ብለውታል።—ማቴዎስ 16:13-16፤ ሉቃስ 4:41

ኢየሱስ ራሱ ስለ ማንነቱ ተናግሯል

ኢየሱስ አልፎ አልፎ ቢሆንም የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ይናገር ነበር። (ማርቆስ 14:61, 62፤ ዮሐንስ 3:18፤ 5:25, 26፤ 11:4) ሆኖም በአብዛኛው ለማለት ይቻላል፣ ራሱን “የሰው ልጅ” እያለ ይጠራ ነበር። ማንነቱን በዚህ መንገድ በመግለጽ በእርግጥ ሰው ሆኖ እንደተወለደ አጉልቷል። እንዲሁም ራሱን የሰው ልጅ እያለ በመጥራት፣ ዳንኤል በተመለከተው ራእይ ውስጥ “ጥንታዌ ጥንቱ” ተብሎ ወደተገለጸው ሁሉን ቻይ አምላክ የቀረበው ‘የሰው ልጅ’ እርሱ እንደሆነ አረጋግጧል።—ማቴዎስ 20:28፤ ዳንኤል 7:13

ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ራሱ ከመናገር ይልቅ ሌሎች እዚህ መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ ያደርግ ነበር። በመሆኑም መጥምቁ ዮሐንስንና የኢየሱስ የቅርብ ጓደኛ ማርታን ጨምሮ ሐዋርያቱ ያልነበሩ ሌሎች ሰዎች የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ተናግረዋል። (ዮሐንስ 1:29-34፤ 11:27) እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ እንደሚመጣ የተነገረለት መሲሕ መሆኑን ያምኑ ነበር። ቀደም ሲል በሰማይ ኃያል መንፈሳዊ ፍጡር ሆኖ ይኖር እንደነበረና አምላክ ሕይወቱን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ድንግል ወደ ነበረችው ማርያም ማሕጸን እንዳዘዋወረው ተገንዝበዋል።—ኢሳይያስ 7:14፤ ማቴዎስ 1:20-23

ኢየሱስ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው?

ኢየሱስ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጋር በብዙ መንገዶች ይመሳሰላል። ለምሳሌ ያህል ሁለቱም ሰብዓዊ አባት የሌላቸው ፍጹማን ሰዎች ነበሩ። (ዘፍጥረት 2:7, 15) ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “ኋለኛው አዳም” በማለት “ተመጣጣኝ ቤዛ” ሆኖ ሊቀርብ የሚችል ፍጹም ሰው እንደሆነ ይናገራል። የኢየሱስ ሕይወት፣ አምላክ ፍጹም ሰው አድርጎ ከፈጠረው ‘ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም’ ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ነበር።—1 ቆሮንቶስ 15:45፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6 NW

መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያውን አዳም “የእግዚአብሔር ልጅ” ብሎ ይጠራዋል። (ሉቃስ 3:38) ይሁን እንጂ የመጀመሪያው አዳም ሆን ብሎ አምላክን ባለመታዘዙ የእርሱ ልጅ የመሆንን ውድ መብት አጣ። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ምንጊዜም ለሰማያዊ አባቱ ታማኝ ነበር፤ በዚህ ምክንያት የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ቀጥሏል። (ማቴዎስ 3:17፤ 17:5) በኢየሱስ የሚያምኑና እንደ አዳኛቸው አድርገው የሚቀበሉት ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዮሐንስ 3:16, 36፤ የሐዋርያት ሥራ 5:31፤ ሮሜ 5:12, 17-19

ሆኖም አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ብቻ ሳይሆን ራሱ እግዚአብሔር ነው ብለው ይከራከራሉ። ኢየሱስም ሆነ አባቱ ሁሉን ቻይ አምላክ ናቸው ይላሉ። ይህ አባባላቸው ትክክል ነው? ኢየሱስ በሆነ መንገድ አንደኛው የእግዚአብሔር ክፍል ነው? ስለዚህ ጉዳይ ኢየሱስ ወይም ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የተናገሩት ነገር አለ? ብቸኛው እውነተኛ አምላክ በእርግጥ ማን ነው? ኢየሱስ ስለ እውነተኛው አምላክ ማንነት ምን ብሏል? እስቲ እነዚህን ሐሳቦች እንመርምር።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የእርሱን ያህል ታዋቂ ሰው አልተነሳም

ኢየሱስ በኖረበት ዘመን የኖሩ አራት ሰዎች ስለ እርሱ ሕይወት ዘግበዋል። እነርሱም ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስና ዮሐንስ ናቸው፤ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ የቅርብ ወዳጆቹ ነበሩ። እነዚህ ሰዎች የጻፏቸው መጻሕፍት በስማቸው የተሰየሙ ሲሆን በተለምዶ ወንጌሎች ይባላሉ፤ የእነዚህ ወንጌሎች የተወሰነው ክፍል ከሁለት ሺህ በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል። እነዚህ ትናንሽ መጻሕፍት ከሌሎች መጻሕፍት ጋር ተዳምረው መጽሐፍ ቅዱስን አስገኝተዋል። በታሪክ ውስጥ የወንጌሎችን ያህል (በተናጠልም ሆነ ከሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር) በከፍተኛ መጠን የተሰራጨ ጽሑፍ የለም። ስለዚህ ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ታዋቂ መሆኑ ምንም አያስደንቅም!

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐዋርያት “ይህ ማን ነው?” ብለው ጠይቀዋል