በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የውጭ አገር ቆይታዬን ስኬታማ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

የውጭ አገር ቆይታዬን ስኬታማ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

የውጭ አገር ቆይታዬን ስኬታማ ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

“አየር ማረፊያው እንደደረስኩ ማድረግ የፈለኩት ነገር ቢኖር ወደ አገሬ መመለስ ብቻ ነበር! . . . የጀብደኝነት ስሜቴም ሆነ ስለ አዳዲስ ነገሮች ለማወቅ የነበረኝ ያ ሁሉ ጉጉት ጠፍቶ ነበር። ባጭር አነጋገር፣ ከዚህ ቀደም እንደዚያ ያለ ናፍቆት ተሰምቶኝ አያውቅም።”—ኡታ

በባዕድ አገር ለብቻ መኖር የሚለው ሐሳብ ያስፈራል። ሆኖም ከዚህ በፊት የወጣው ርዕስ እንደሚያሳየው ብዙ ወጣቶች ለተወሰነ ጊዜ ውጭ አገር ለመኖር ይመርጣሉ። አንዳንዶች የሚሄዱት ትምህርት ወይም ልዩ ሥልጠና ለማ ግኘት ሲሆን ሌሎች ደግሞ ቋንቋ ለመማር ስለሚፈልጉ ነው። ገንዘብ ለማግኘት ሲሉ ብቻ የሚሄዱም አሉ። አንዳንዶች ግን የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ሲሉ ወደ ውጭ አገር ይሄዳሉ።

ውጭ አገር ለመሄድ ያነሳሱህ መንፈሳዊ ፍላጎቶችህንና ግቦችህን ግምት ውስጥ ያስገቡ ተገቢ ምክንያቶች ናቸው እንበል። * ታዲያ የውጭ አገር ቆይታህ የተሳካ እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?

ራስህን ከሁኔታዎች ጋር ለማለማመድ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ

በመጀመሪያ አዲሱን ሁኔታህን ለመልመድ ፈቃደኛ መሆን አለብህ። ሆኖም ይህ ማለት ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን መጣስ ወይም መንፈሳዊ ልማዶችህን መተው ይኖርብሃል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የአዳዲስ ምግቦችን ጣዕም መልመድ፣ አዳዲስ የሥነ ሥርዓት ደንቦችን መማር ወይም ነገሮችን በተለየ መንገድ መሥራት ማለት ሊሆን ይችላል። እነዚህ አዳዲስ ልማዶች አንተ ነገሮችን በአገርህ ከምታከናውንባቸው መንገዶች በጣም ሊለዩ ይችላሉ። ሆኖም ኢየሱስ “አትፍረዱ” ሲል የሰጠው ምክር እዚህም ላይ ይሠራል። (ማቴዎስ 7:​1) እንደ እውነቱ ከሆነ የትኛውም ዘር ወይም ባህል ከሌላው በልጦ የሚታይበት ምክንያት የለም። (ሥራ 17:​26) በዕድሜ የገፉ ሰዎች የዘመኑን ወጣቶች ከድሮ ወጣቶች ጋር በማወዳደር መተቸት እንደማይገባቸው ሁሉ ውጭ አገር የሚሄዱ ወጣቶችም የራሳቸውን አገርና የውጭውን አገር በማወዳደር ነቃፊ መሆን አይኖርባቸውም። (መክብብ 7:​10) በአዲሱ አገርና ባህል ውስጥ በምታገኛቸው አዎንታዊ ነገሮች ላይ ትኩረት አድርግ። በተጨማሪም ቋንቋውን በፍጥነት ለመማር ጥረት ባደረግህ መጠን ቶሎ የመልመድ አጋጣሚህም ከፍ ይላል።

ሐዋርያው ጳውሎስ ሚስዮናዊ ሆኖ በሚያገለግልበት ወቅት “ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ” ለመሆን ፈቃደኛ ስለነበር ከተለያዩ ባህሎች ጋር በሚገባ መላመድ ችሏል። (1 ቆሮንቶስ 9:​22) አንተም ተመሳሳይ ዝንባሌ ማሳየትህ ቶሎ እንድትለምድ ሊረዳህ ይችላል። አድሪያና በጀርመን ለሚገኝ አንድ ቤተሰብ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የምታከናውን ሲሆን እነርሱ ደግሞ ምግብና መኝታ ይሰጧታል። አድሪያና “ሌሎች ከእኔ ሁኔታ ጋር እንዲስማሙ መጠበቅ ስለማልችል እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ለማድረግ ዝግጁ መሆን ነበረብኝ” ስትል ገልጻለች።

‘ናፍቆቱን አልቻልኩትም!’

በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ትካዜና ናፍቆት መሰማቱ የተለመደ ነው። ያዕቆብ ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት በባዕድ አገር ቢኖርም እንኳ ‘የአባቱን ቤት ናፍቆ’ እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል! (ዘፍጥረት 31:​30) ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ አልቅስ አልቅስ ቢልህ አትደነቅ። እርግጥ፣ ጥለኸው ስለመጣኸው ነገር ያለማቋረጥ የምታስብ ከሆነ ትርፉ ችግሩን ማባባስ ብቻ ነው። (ዘኁልቊ 11:​4, 5) ሐዘንና ትካዜን ለማሸነፍ ከሁሉ የተሻለው መንገድ ከአዲሱ ሥራህና አካባቢህ ጋር መላመድ ነው። ከቤተሰቦችህ ጋር በደብዳቤ ወይም በስልክ መገናኘቱ ጥሩ ቢሆንም ወደ ቤት ብዙ ጊዜ መደወል አዲሱን አካባቢ ቶሎ እንዳትለምድ ሊያደርግህ ይችላል።

ብዙ ክርስቲያን ወጣቶች መንፈሳዊ ልማዶቻቸውን ሳይዘገዩ መጀመራቸው ለብቸኝነት ፍቱን መድሃኒት ሆኖ አግኝተውታል። (ፊልጵስዩስ 3:​16) አምበር በውጭ አገር ያሳለፈቻቸውን የመጀመሪያዎቹን ሳምንታት በማስታወስ እንዲህ ብላለች:- “በተለይ ማታ ማታ ምንም የምሠራው ስላልነበረኝ ይከብደኝ ነበር። ስለዚህ ተጨማሪ ጥናት ለማድረግ ወይም መጽሐፍ ለማንበብ ሞከርኩ።” ከብሪታንያ ወደ ጀርመን የመጣችው ወጣቷ ራሄል ደግሞ ካገኘችው ተሞክሮ በመነሳት እንዲህ የሚል ምክር ሰጥታለች:- “ጊዜ ሳታጠፉ ተቀላቀሉ። ወዲያው በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀምሩ።” መጀመሪያ አካባቢ ወደ ስብሰባዎች ለመሄድ እርዳታ ያስፈልግህ ይሆናል። ሆኖም በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እንደ ‘ወንድም፣ እኅትና እናት’ የሚሆኑልህ ጥሩ ጓደኞች ታገኛለህ።​—⁠ማርቆስ 10:​29, 30

በክርስቲያናዊው የወንጌላዊነት ሥራ መካፈልም በጣም አስፈላጊ የሆነ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ነው። መስበክ መንፈሳዊ ጥቅም ከማስገኘቱም ሌላ ከአዲሱ ባሕልና ቋንቋ ጋር ራስህን እንድታላምድ ይረዳሃል።

በመጨረሻም የመጸለይና የግል ጥናት የማድረግ ልማድ አዳብር። እነዚህ ነገሮች በመንፈሳዊ ጤናማ ሆኖ ለመቀጠል የግድ አስፈላጊ ናቸው። (ሮሜ 12:​12፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​15) ከዚህም የተነሣ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው አድሪያና በራሷ ቋንቋ የተዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አምጥታ ነበር።

በእንግድነት ከሚቀበላችሁ ቤተሰብ ጋር መኖር

አንዳንድ ክርስቲያን ወጣቶች በውጪ ቆይታቸው ወቅት አማኝ ከሆኑ ቤተሰቦች ጋር ለመኖር ዝግጅት አድርገዋል። በእንግድነት የሚቀበሉት ቤተሰቦች የወላጅነትን ኃላፊነት እንዲሸከሙ ባይጠበቅባቸውም ጥሩ ባልንጀሮችና የመንፈሳዊ ብርታት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።​—⁠ምሳሌ 27:​17

ያም ሆኖ ከተቀባዩ ቤተሰብ ጋር ያለው ጥሩ ግንኙነት ተጠብቆ እንዲቆይ ክፍት የሆነ የሐሳብ ግንኙነት መሥመር መኖሩ በጣም አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 15:​22፤ 20:​5፤ 25:​11) አምበር እንዲህ በማለት ትገልጻለች:- “ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ልታውቁ ይገባል። የተቀበላችሁ ቤተሰብ ከእናንተ የሚፈልገውን ነገር ማወቅ ያስፈልጋችኋል። እነርሱም ቢሆኑ እናንተ ምን እንደምትጠብቁባቸው ሊያውቁ ይገባል።” የቤተሰቡ መመሪያዎች ምን እንደሆኑና አንተ ደግሞ ምን ያህሉን የቤት ውስጥ ሥራ ማከናወን እንደሚጠበቅብህ ጠይቅ። እንዲህ ያሉትን ጉዳዮች በጥንቃቄ ልትወያዩባቸው ያስፈልጋል።

በተለይ የአንተን እምነት ለማይጋራ ቤተሰብ የምትሠራ ከሆነ ያለህበት ሁኔታ በጣም ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ቤተሰቡ ለመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ያለህን አቋም ላይገነዘብልህ ስለሚችል አቋምህን የሚያዳክም ሁኔታ ውስጥ እንደገባህ ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። (ምሳሌ 13:​20) እንድታከናውናቸው የምትጠየቃቸው የቤት ውስጥ ሥራዎች በስብሰባዎች ላይ እንደመገኘት ከመሳሰሉት መንፈሳዊ ግዴታዎች ጋር ሊጋጭ ይችላል። ከአቅም በላይ የሆኑ ሁኔታዎች የአንተን እምነት ከማይጋራ ቤተሰብ ጋር እንድትቆይ ካስገደዱህ አንዳንድ ልትወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች አሉ።

ራሔል እንዲህ የሚል ምክር ሰጥታለች:- “ክርስቲያን መሆናችሁን ወዲያውኑ በግልጽ ማሳወቃችሁ በጣም ጥሩ ነው።” ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ አቋምህን ማስረዳትህ ጥበቃ ሊሆንልህ ይችላል። ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና ስብከት ለአንተ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ ለአሠሪህ ግልጽ ማድረግ ይኖርብሃል። በመጨረሻም ሥራ ከመጀመርህ በፊት የሥራ ሰዓትን፣ የእረፍት ጊዜንና ክፍያን የመሳሰሉት በጣም አስፈላጊ ጉዳዮች በጽሑፍ ላይ መስፈራቸውን አረጋግጥ። ይህም በኋላ ሊደርስ ከሚችል ብስጭት ይጠብቅሃል።

ለችግሮች መፍትሄ መፈለግ

ምንም ያህል ጥረት ብታደርግ ችግሮች ሊነሱ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ በእንግድነት የተቀበለህ ቤተሰብ ቤቱን እንድትለቅ ቢጠይቅህስ? ይህ በጣም ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። በመካከላችሁ አንድ ዓይነት አለመግባባት ተፈጥሮ ከሆነ ረጋ ባለ መንፈስና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ከቤተሰቡ ጋር ለመወያየት ሞክር። (ምሳሌ 15:​1) የሠራኸውን ማንኛውንም ስህተት ለማመን ፈቃደኛ ሁን። ምናልባት ሐሳባቸውን ይለውጡ ይሆናል። ካልለወጡ ግን ሌላ መኖሪያ ቦታ መፈለግ ይኖርብሃል።

ሌሎቹ ችግሮች ደግሞ የሌላ ሰው እርዳታ እንድትጠይቅ የሚያስገድዱ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ፣ የገንዘብ ችግር ወይም ሕመም ያጋጥምህ ይሆናል። ወላጆቼ መጥተው ወደ አገሬ ይመልሱኛል ብለህ በመፍራት ችግሩን ለእነርሱ ከማሳወቅ ታመነታ ይሆናል። ከዚህም በላይ እነርሱ ያሉት ብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀው ስለሆነ በውጭ አገር ላጋጠመህ እንዲህ ላለው ችግር መፍትሄ የሚገኝበትን መንገድ አያውቁ ይሆናል። ይሁን እንጂ የጉባኤው ሽማግሌዎች እንዲህ ያሉትን ችግሮች በመፍታት ረገድ ብዙ ልምድ ሊኖራቸው ስለሚችል አንዳንድ ተግባራዊ የሆኑ ሐሳቦች ሊሰጡህ ይችሉ ይሆናል። በተጨማሪም ችግሩ የወላጆችህን ትኩረት ማግኘት ያለበት ጉዳይ መሆን አለመሆኑን እንድትወስን ሊረዱህ ይችሉ ይሆናል።

ወደ አገርህ መመለስ

ችግሮችና ፈተናዎች ቢኖሩትም በውጭ አገር የተወሰነ ጊዜ ማሳለፍ በተለይ የሄድከው ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ከሆነ በጣም አስደሳች ተሞክሮ ሊሆንልህ ይችላል። እርግጥ፣ አንድ ቀን ወደ አገርህ የምትመለስበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል። አንድራስ “በጣም ብዙ አስደሳች ትዝታዎች ስለነበሩኝ ከዚያ ለቅቆ መምጣቱ በጣም ከብዶኝ ነበር። የማያስደስቱት ትዝታዎች ወዲያው ይረሳሉ” በማለት ተናግሯል። ያም ሆኖ አንተ ከውጭ የተለየ አመለካከት አዳብረህ ስለመጣህ ብቻ ጓደኞችህ ወይም ቤተሰቦችህ በአንድ ጊዜ ልማዳቸውን እንዲለውጡ መጠበቅ አይኖርብህም። ከዚህም በተጨማሪ ነገሮች ሌላ ቦታ ስለሚከናወኑበት መንገድ በመወትወት አታበሳጫቸው። ላገኘኸው ሰው ሁሉ ተሞክሮህን ለመናገር መፈለግህ በተፈጥሮ ያለ ነገር ቢሆንም ሁሉም ሰው አንተ የምታወራውን ነገር ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሆኖ ባይገኝ አትበሳጭ።

በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ለተወሰነ ጊዜ ውጭ አገር ለመኖር መወሰን በቁም ነገር ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። በጉዳዩ ላይ ከወላጆችህ ጋር ከተወያየህ በኋላ ውጭ ለመሄድ የሚያበቁ ተገቢ ምክንያቶች እንዳሉህ ከተሰማህ በዚያ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች ለመቋቋም ራስህን አዘጋጅ። በሕይወት ውስጥ ትልቅ ውሳኔ ማድረግ የሚጠይቅ ማንኛውም ነገር ሲያጋጥም አስቀድሞ ወጪውን ማስላት ጥበብ ነው።​—⁠ሉቃስ 14:​28-30

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . . ውጭ አገር መሄድ ይኖርብኛልን?” የሚለውን በነሐሴ 2000 ንቁ! ላይ የወጣ ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለጥንቃቄ የሚረዱ ሐሳቦች

ፓስፖርትህን፣ ገንዘብህንና የመመለሻ ትኬትህን አስተማማኝ ቦታ አስቀምጥ።

ፓስፖርትህን ጨምሮ የመግቢያ ፈቃድህን እና/ ወይም ቪዛህን፣ የመመለሻ ትኬትህን እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን ፎቶ ኮፒ አድርጋቸው። ፎቶ ኮፒ የተደረጉትን ወረቀቶች አንድ ቅጂ ለራስህ ካስቀረህ በኋላ ሌላኛውን ደግሞ ወደ አገርህ ለቤተሰቦችህ ወይም ለጓደኞችህ ላከው።

ሁልጊዜ የወላጆችህን ወይም በአገርህ ያሉትን የጓደኞችህን እንዲሁም በእንግድነት የተቀበለህን ቤተሰብ ስልክ ቁጥር ያዝ።

በእንግድነት በተቀበለህ ቤተሰብ ውስጥ፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በሌሎች ቦታዎች ከሚገኙት ተቃራኒ ጾታ ጋር የሚኖርህ ግንኙነት ንጹህ ይሁን።

በእንግድነት ያለህበትን አገር ቋንቋ ቢያንስ ጥቂት ቃላት ወይም ሐረጎች ተማር።

መኖሪያህን ለቀህ ከመሄድህ በፊት የህክምና ምርመራ አድርግ። የሚያስፈልግህን ማንኛውንም ዓይነት መድሃኒት በበቂ መጠን መያዝህን አረጋግጥ።

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእንግድነት ከተቀበለህ ቤተሰብ ጋር አለመግባባት ከተፈጠረ ረጋ ባለ መንፈስ ለመወያየት ሞክር