በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ እውነቱ ምንድን ነው?

የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ እውነቱ ምንድን ነው?

‘የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?’ ብለህ አስበህ ታውቃለህ? መጽሐፍ ቅዱስ በሁላችንም ሕይወት ላይ ለውጥ የሚያመጡ ወሳኝ ክስተቶች በቅርቡ እንደሚፈጸሙ ይናገራል።

ኢየሱስ “የአምላክ መንግሥት እንደቀረበ እርግጠኞች” መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ነግሮናል። (ሉቃስ 21:31) ታላላቅ ጦርነቶች፣ ከባባድ የምድር ነውጦች፣ የምግብ እጥረት፣ ቸነፈር እንዲሁም ሌሎች ነገሮች እንደሚከሰቱ ተንብዮአል። በአሁኑ ጊዜ እነዚህ ነገሮች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነው።—ሉቃስ 21:10-17

መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀናት” የሰዎች ባሕርይ በእጅጉ እንደሚበላሽ ይናገራል። እባክህ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ተመልከት። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች ጥቅሱ ላይ የተዘረዘሩትን ባሕርያት እንደሚያንጸባርቁ አስተውለህ መሆን አለበት፤ ይህ ደግሞ ትንቢቱ በዘመናችን እየተፈጸመ እንዳለ ያረጋግጣል።

ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት የሚናገሩት ትንቢቶች መፈጸማቸው ምን ያመለክታል? የአምላክ መንግሥት በምድር ላይ ያለውን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ የሚቀይርበት ጊዜ በጣም እንደቀረበ ያመለክታል። (ሉቃስ 21:36) አምላክ ለምድርም ሆነ ለሰው ልጆች መልካም ነገሮችን እንደሚያደርግ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ቃል ገብቷል። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

መልካም አስተዳደር

“ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያገለግሉት የገዢነት ሥልጣን፣ ክብርና መንግሥት [ለኢየሱስ] ተሰጠው። የገዢነት ሥልጣኑ የማያልፍና ዘላለማዊ፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።”ዳንኤል 7:14

ምን ማለት ነው? አምላክ ዓለም አቀፋዊ መንግሥት ያቋቋመ ሲሆን ልጁን ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል፤ በዚህ አስደናቂ መንግሥት ሥር አስደሳች ሕይወት መምራት ትችላለህ።

ጥሩ ጤንነት

“በዚያም የሚቀመጥ ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ አይልም።”ኢሳይያስ 33:24

ምን ማለት ነው? ሕመምም ሆነ የአካል ጉዳት ሳያጋጥምህ ለዘላለም መኖር ትችላለህ።

ዓለም አቀፋዊ ሰላም

“ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል።”መዝሙር 46:9

ምን ማለት ነው? ጦርነትም ሆነ የሚያስከትላቸው ችግሮች አይኖሩም።

ምድር በጥሩ ሰዎች ትሞላለች

“ክፉዎች አይኖሩም፤ . . . የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ።”መዝሙር 37:10, 11

ምን ማለት ነው? ክፉ ሰዎች ይጠፋሉ፤ ምድር ላይ የሚኖሩት አምላክን የሚታዘዙ ሰዎች ብቻ ናቸው።

ምድር ገነት ትሆናለች

“ቤቶችን ይሠራሉ፤ በዚያም ይኖራሉ፤ ወይንንም ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ።”ኢሳይያስ 65:21, 22

ምን ማለት ነው? መላዋ ምድር ውብ ገነት ትሆናለች። በዚያ ወቅት የአምላክ ‘ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም’ የምናቀርበው ጸሎት ምላሽ ያገኛል።—ማቴዎስ 6:10