በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ—አስተማማኝ የእውነት ምንጭ

መጽሐፍ ቅዱስ—አስተማማኝ የእውነት ምንጭ

በታሪክ ዘመናት ሁሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ የእውነት ምንጭ እንደሆነ የሚያምኑ የተለያየ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው በርካታ ሰዎች ነበሩ። በዛሬው ጊዜም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች መሠረት ሕይወታቸውን ይመራሉ። ሌሎች ግን መጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ያለፈበት ወይም ልብ ወለድ እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንተስ ምን ይመስልሃል? መጽሐፍ ቅዱስ የእውነት ምንጭ እንደሆነ ይሰማሃል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት መጣል የምትችለው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥ እምነት የሚጣልበት መጽሐፍ እንደሆነ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ለበርካታ ዓመታት የምታውቀው ጓደኛህ ሁሌም እውነት የሚናገር ከሆነ እምነት አትጥልበትም? እንዴታ! ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ እንደዚህ ጓደኛህ እምነት የሚጣልበት መሆኑን አስመሥክሯል? እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት።

እውነት የሚናገሩ ጸሐፊዎች

መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት ሰዎች በጣም ሐቀኞች ነበሩ፤ የሠሩትን ስህተትና ድክመቶቻቸውን ጭምር ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ነቢዩ ዮናስ አምላክን ያልታዘዘበት ጊዜ እንደነበረ ጽፏል። (ዮናስ 1:1-3) እንዲያውም መጽሐፉን የደመደመው አምላክ ተግሣጽ እንደሰጠው በመግለጽ ነው፤ ያደረጋቸውን የሚያስመሰግኑ ነገሮች ለምሳሌ አመለካከቱን ያስተካከለው እንዴት እንደሆነ እንኳ አልተናገረም። (ዮናስ 4:1, 4, 10, 11) ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሐቀኛ መሆናቸው ለእውነት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ ያሳያል።

እውነተኛና ጠቃሚ ምክር

መጽሐፍ ቅዱስ ለዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚሰጠው ምክር ምንጊዜም ጠቃሚ ነው? እንዴታ! መጽሐፍ ቅዱስ ከሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መመሥረት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ የሚሰጠውን ምክር እንደ ምሳሌ እንውሰድ፦ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም አድርጉላቸው።” (ማቴዎስ 7:12) “የለዘበ መልስ ቁጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቁጣን ያነሳሳል።” (ምሳሌ 15:1) በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ጥንትም ሆነ ዛሬ እውነተኛና ጠቃሚ ነው።

እውነተኛ ታሪክ

በርካታ የአርኪኦሎጂ ግኝቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ የተለያዩ ሰዎች፣ ቦታዎችና ክንውኖች ታሪካዊ እውነተኝነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሰ አንድ አጭር ሐሳብ ለዚህ ምሳሌ ይሆናል። በነህምያ ዘመን በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩ የጢሮስ ሰዎች (ከጢሮስ የመጡ ፊንቄያውያን) “ዓሣና የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦችን እያመጡ” ይሸጡ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ነህምያ 13:16

ይህ ጥቅስ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ አለ? በሚገባ። የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች እስራኤል ውስጥ የፊንቄ ዕቃዎችን አግኝተዋል፤ ይህም በሁለቱ ብሔራት መካከል ንግድ ይካሄድ እንደነበር ይጠቁማል። ከዚህም ሌላ ኢየሩሳሌም ውስጥ የሜድትራንያን ዓሣዎች ቅሪት በቁፋሮ ተገኝቷል። ዓሣዎቹን ነጋዴዎች ርቆ ከሚገኘው የባሕር ዳርቻ እንዳመጧቸው የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች ያምናሉ። አንድ ምሁር ማስረጃውን ከመረመሩ በኋላ “የጢሮስ ሰዎች ኢየሩሳሌም ውስጥ ዓሣ ይሸጡ እንደነበር የሚገልጸው በነህምያ 13:16 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ትክክለኛ ይመስላል” የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል።

ከሳይንስ አንጻር እውነተኛ

መጽሐፍ ቅዱስ በዋነኝነት ታሪክና ሃይማኖታዊ መመሪያ የያዘ መጽሐፍ ቢሆንም የሚጠቅሳቸው ሳይንሳዊ ሐሳቦች በሙሉ ትክክል ናቸው። አንድ ምሳሌ እንመልከት።

ምድር “ያለምንም ነገር” እንደተንጠለጠለች መጽሐፍ ቅዱስ ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ገልጾ ነበር። (ኢዮብ 26:7) ይህ ሐሳብ በወቅቱ ከነበረው አመለካከት በእጅጉ የተለየ ነው፤ በዘመኑ ምድር ውኃ ላይ እንደምትንሳፈፍ ወይም ግዙፍ ኤሊ ላይ እንደተቀመጠች የሚገልጹ አፈ ታሪኮች ነበሩ። የኢዮብ መጽሐፍ ከተጻፈ ከ1,100 ዓመታት በኋላም እንኳ ሰዎች ምድር ያለምንም ነገር ልትንጠለጠል እንደማትችል ያምኑ ነበር። ምድር ያለምንም ነገር እንደተንጠለጠለች የተረጋገጠው ከ300 ዓመታት ገደማ በፊት ማለትም አይዛክ ኒውተን በ1687 የመሬት ስበትን በተመለከተ ያደረገውን ጥናት ባሳተመበትና ምድር በምህዋሯ ላይ እንድትገኝ ያደረጋት በዓይን የማይታይ ኃይል እንደሆነ በገለጸበት ወቅት ነው። ይህ ትልቅ ሳይንሳዊ ግኝት፣ መጽሐፍ ቅዱስ ከ3,000 የሚበልጡ ዓመታት አስቀድሞ የገለጸውን ሐሳብ ትክክለኛነት አረጋግጧል።

እውነተኛ ትንቢት

መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ ትንቢቶችን ይዟል፤ ለመሆኑ እነዚህ ትንቢቶች በትክክል ተፈጽመዋል? ኢሳይያስ የባቢሎንን አወዳደቅ በተመለከተ የተናገረውን ትንቢት እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

ትንቢቱ፦ በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ኢሳይያስ የባቢሎን ከተማ እንደምትገለበጥና በኋላም ማንም እንደማይኖርባት ተንብዮ ነበር፤ የሚገርመው በወቅቱ ባቢሎን ገና የዓለም ኃያል መንግሥት አልሆነችም ነበር። (ኢሳይያስ 13:17-20) እንዲያውም ኢሳይያስ ባቢሎንን ድል የሚያደርገው ቂሮስ የተባለ ሰው እንደሆነ ገልጾ ነበር። ኢሳይያስ ‘ወንዞቹ እንደሚደርቁ’ በመናገር ቂሮስ የሚጠቀምበትን የጦር ስልት ጭምር ጠቅሷል። እንዲሁም የከተማዋ በሮች እንደማይዘጉ ተናግሯል።—ኢሳይያስ 44:27 እስከ 45:1

ፍጻሜው፦ ኢሳይያስ ትንቢቱን ከተናገረ ከ200 ዓመታት ገደማ በኋላ አንድ የፋርስ ንጉሥ በባቢሎን ላይ ጥቃት ሰነዘረ። የዚህ ንጉሥ ስም ቂሮስ ነው። ባቢሎን የተመሸገች ከተማ ስለነበረች ቂሮስ ትኩረቱን በኤፍራጥስ ወንዝ ላይ አደረገ፤ የኤፍራጥስ ወንዝ የባቢሎንን ከተማ አቋርጦ የሚያልፍ ከመሆኑም ሌላ ዙሪያዋን ይከባት ነበር። የቂሮስ ወታደሮች ቦይ በመቆፈር ወንዙ አቅጣጫውን ቀይሮ እንዲፈስ አደረጉ። በዚህም ምክንያት የወንዙ መጠን ቀንሶ እስከ ጭን የሚደርስ ሆነ፤ ስለዚህ የቂሮስ ሠራዊት በወንዙ መሃል ተራምዶ ወደ ከተማዋ ቅጥሮች መድረስ ቻለ። የሚደንቀው ነገር በዚያ ዕለት ባቢሎናውያኑ በወንዙ በኩል ያሉትን የከተማዋን በሮች አልዘጓቸውም ነበር። የቂሮስ ወታደሮች በተከፈተው በር ሰተት ብለው በመግባት ባቢሎንን ድል አደረጓት።

አሁን ደግሞ በቀሪው የትንቢቱ ክፍል ላይ እናተኩር፤ ባቢሎን ሰው የማይኖርባት ቦታ ሆናለች? ለተወሰኑ መቶ ዓመታት ሰዎች በባቢሎን መኖራቸውን ቀጥለው ነበር። አሁን ግን ባቢሎን የፍርስራሽ ክምር ሆናለች፤ በባግዳድ፣ ኢራቅ አቅራቢያ የሚገኘው የባቢሎን ፍርስራሽ ትንቢቱ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን እንዳገኘ ያረጋግጣል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚናገረው ትንቢት በትክክል ይፈጸማል።