በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

አደገኛ በሆኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ልትካፈል ይገባል?

አደገኛ በሆኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ልትካፈል ይገባል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አደገኛ በሆኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ልትካፈል ይገባል?

“ቀደም ሲል አብዛኞቹ ሰዎች ከአውሮፕላን ዘሎ በፓራሹት መንሳፈፍን፣ በገመድ ተንጠላጥሎ ከተራራ መውረድን፣ ፏፏቴ ላይ በጀልባ መሄድንና ሻርኮች ያሉበት ውኃ ውስጥ መግባትን ጨምሮ አስፈሪ የሆኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ሌሎች ሲያደርጉ ብቻ ነበር የሚመለከቱት፤ አሁን አሁን ግን እነሱ ራሳቸው በእነዚህ እንቅስቃሴዎች መካፈል ጀምረዋል።”—ዘ ዊሎው ግሌን ሬዚደንት ጋዜጣ

እዚህ ጋዜጣ ላይ የወጣው ሐሳብ በስፖርቱ ዓለም እየታየ ያለውን አዝማሚያ ጥሩ አድርጎ ይገልጻል። ከአውሮፕላን ዘሎ በፓራሹት እንደ መንሳፈፍ፣ በበረዶ የተሸፈኑ ተራራዎችን እንደ መውጣትና ፓራሹት አድርጎ ከፍ ካሉ ቦታዎች ላይ እንደ መዝለል * ያሉ እንቅስቃሴዎች ይበልጥ ተወዳጅነት እያገኙ መምጣታቸው በዓለማችን ላይ ያሉ በርካታ ሰዎች አደገኛ ሁኔታዎችን መሞከር እንደሚወዱ ያሳያል። በረዶ ላይ መንሸራተትን፣ ተራራ ላይ ብስክሌት ማሽከርከርን እንዲሁም ጎማ የተገጠመላቸውን ጫማዎች ወይም መንሸራተቻዎች ተጠቅሞ መንሸራተትን በመሳሰሉ ስፖርቶች የሚካፈሉ ሰዎችም እንኳ እነዚህን ስፖርቶች ከባድ ዳገት ያለው ተራራ ላይ ወይም ረጅም ቋጥኝ ላይ በመሥራት ራሳቸውን ለመፈተን ይሞክራሉ። ታይም የተባለው መጽሔት እንደገለጸው አደገኛ የሆኑ ስፖርቶች ይበልጥ ተወዳጅ እየሆኑ መምጣታቸው በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች “ችሎታቸውን እንዲጠቀሙ እንዲሁም አደገኛ ሁኔታዎችንና ፍርሃትን ተቋቁመው የአቅማቸው ጥግ ድረስ እንዲሠሩ በሚያስችሏቸው እንቅስቃሴዎች ለመካፈል” ያላቸውን ጉጉት የሚያሳይ ነው።

ይሁንና እንዲህ ያሉት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላሉ። ያን ያህል አደገኛ አይደሉም የሚባሉ ስፖርቶች እንኳ ወጣ ባለ መንገድ ሲሠሩ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ። በዩናይትድ ስቴትስ በ1997 ብቻ፣ ጎማ የተገጠመላቸውን መንሸራተቻዎች ተጠቅመው ሲንሸራተቱ ባጋጠማቸው አደጋ ምክንያት ድንገተኛ ክፍል የገቡ ሰዎች ቁጥር ከ33 በመቶ በላይ ጨምሯል፤ በረዶ ላይ በመንሸራተትና ተራራ በመውጣት ያጋጠሙ አደጋዎች ደግሞ የ31 በመቶ እና የ20 በመቶ ጭማሪ አሳይተዋል። በሌሎች ስፖርቶች ላይ የሚያጋጥመው አደጋ ከዚህም የከፋ ነው፤ አደገኛ በሆኑ ስፖርቶች ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ ለዚህ ማስረጃ ይሆናል። እንዲህ ባሉ ስፖርቶች የሚካፈሉ ሰዎች፣ የሚያደርጉት ነገር የሚያስከትለውን አደጋ ጠንቅቀው ያውቁታል። አደገኛ በሆነ የበረዶ ላይ ሸርተቴ ስፖርት የምትካፈል አንዲት ሴት “እሞታለሁ የሚለው ስጋት ከአእምሮዬ ጠፍቶ አያውቅም” ብላለች። ፕሮፌሽናል የበረዶ ላይ ሸርተቴ ተጫዋች የሆነ አንድ ሰው ደግሞ “ጉዳት ካልደረሰብህ በቂ ጥረት እያደረግክ አይደለም ማለት ነው” ሲል የብዙዎችን ሐሳብ ጠቅለል አድርጎ ገልጿል።

ታዲያ እስካሁን ካየናቸው ነገሮች አንጻር ክርስቲያኖች አደገኛ በሆነ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስለመካፈል ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ባሉ እንቅስቃሴዎች መካፈል ይኖርብን እንደሆነና እንዳልሆነ ለመወሰን የሚረዳን እንዴት ነው? አምላክ ለሕይወት ምን ያህል ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ ማወቃችን እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ይረዳናል።

አምላክ ለሕይወት ያለው አመለካከት

መጽሐፍ ቅዱስ “የሕይወት ምንጭ” ይሖዋ እንደሆነ ይናገራል። (መዝሙር 36:9) ይሖዋ እኛን ከመፍጠር ባለፈ በሕይወታችን ደስተኛ ለመሆን የሚያስፈልጉንን ነገሮች ሰጥቶናል። (መዝሙር 139:14፤ የሐዋርያት ሥራ 14:16, 17፤ 17:24-28) በመሆኑም እሱ በደግነት የሰጠንን ነገር በጥንቃቄ እንድንይዝ ይጠብቅብናል ብሎ መደምደሙ ምክንያታዊ ነው። ለእስራኤል ብሔር የተሰጡት ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ ለመረዳት ያስችሉናል።

የሙሴ ሕግ እስራኤላውያን የሌሎችን ሕይወት ከአደጋ ለመጠበቅ የተለያዩ ቅድመ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርጉ ያዛል። አንድ እስራኤላዊ እንዲህ ሳያደርግ ቀርቶ የሰው ሕይወት ቢጠፋ በደም ዕዳ ይጠየቃል። ለምሳሌ ያህል፣ አዲስ ቤት የሚገነባ ሰው በቤቱ ጣሪያ ዙሪያ መከታ እንዲሠራ ይጠበቅበት ነበር። እንዲህ ሳያደርግ ቢቀርና አንድ ሰው ከጣሪያው ላይ ወድቆ ቢሞት የቤቱ ባለቤት በቤቱ ላይ የደም ዕዳ ያመጣል። (ዘዳግም 22:8) አንድ በሬ ሳይታሰብ አንድን ሰው ወግቶ ቢገድል የበሬው ባለቤት ተጠያቂ አይሆንም። ሆኖም በሬው የመዋጋት አመል እንዳለው የሚታወቅ ከሆነና ለባለቤቱም ስለ በሬው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶ የነበረ ከሆነ ይህ በሬ ሰው ወግቶ ቢገድል የበሬው ባለቤት በሬውን ሳይጠብቅ በመቅረቱ የደም ባለዕዳ ስለሚሆን ይገደላል። (ዘፀአት 21:28, 29) ሕይወት በይሖዋ ፊት ውድ ዋጋ አለው፤ ሕጉም የይሖዋን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነበር።

ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ከእነዚህ ሕጎች በስተጀርባ ያሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ ነገሮችን ከማድረግ ጋር በተያያዘም እንደሚሠሩ ተረድተው ነበር። በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ ዳዊት “በቤተልሔም በር አቅራቢያ ካለው የውኃ ማጠራቀሚያ ጉድጓድ [የሚጠጣው] ውኃ” ቢያገኝ ደስ እንደሚለው ተናግሮ ነበር። (1 ዜና መዋዕል 11:17-19) በወቅቱ ቤተልሔም በፍልስጤማውያን ቁጥጥር ሥር ነበረች። ሦስት የዳዊት ወታደሮች ዳዊት የተናገረውን ሲሰሙ ወደ ፍልስጤማውያን ሰፈር ጥሰው በመግባት በቤተልሔም ካለው ጉድጓድ ውኃ ቀድተው አመጡለት። ታዲያ ዳዊት ምን አደረገ? ውኃውን ለመጠጣት ፈቃደኛ አልሆነም፤ ከዚህ ይልቅ መሬት ላይ አፈሰሰው። እንዲህም አለ፦ “ለአምላኬ ካለኝ አክብሮት የተነሳ ይህን ማድረግ ፈጽሞ የማላስበው ነገር ነው! ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው የሄዱትን የእነዚህን ሰዎች ደም ልጠጣ ይገባል? ውኃውን ያመጡት በሕይወታቸው ቆርጠው ነውና።” (1 ዜና መዋዕል 11:17-19) ዳዊት ለራሱ ጥቅም ሲል ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ማድረግ ፈጽሞ የማያስበው ነገር ነበር።

ኢየሱስም መላእክት ያድኑት እንደሆነና እንዳልሆነ ለማየት ራሱን ከቤተ መቅደሱ አናት ላይ እንዲወረውር ዲያብሎስ በጠየቀው ጊዜ (በራእይ ሳይሆን አይቀርም) ተመሳሳይ ነገር አድርጓል። “አምላክህን ይሖዋን አትፈታተነው” በማለት ለሰይጣን መልሶለታል። (ማቴዎስ 4:5-7) አዎ፣ ዳዊትና ኢየሱስ ሳያስፈልግ ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ማድረግ በአምላክ ፊት ስህተት እንደሆነ ተገንዝበው ነበር።

እነዚህን ምሳሌዎች በአእምሯችን በመያዝ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ልናነሳ እንችላለን፦ ‘አንድ ስፖርት አደገኛ ነው ብለን ለመወሰን የሚረዳን ምንድን ነው? በራሱ አደገኛ ያልሆነ መዝናኛም እንኳ ወጣ ባለ መንገድ ሲደረግ አደገኛ ሊሆን ስለሚችል በዚህ ረገድ ሚዛናችንን ለመጠበቅ የሚረዳን ምንድን ነው?’

ይህን ያህል መሥዋዕትነት ሊከፈልለት ይገባል?

በማንኛውም እንቅስቃሴ ከመካፈላችን በፊት ሁኔታውን በሐቀኝነት መገምገማችን መልሱን ለማወቅ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ራሳችንን እንዲህ እያልን ልንጠይቅ እንችላለን፦ ‘ይህ ስፖርት ምን ያህል ለአደጋ ያጋልጣል? አደጋ ለመከላከል የሚያስችል ሥልጠና ወስጃለሁ ወይም ትጥቅ አሟልቻለሁ? ብወድቅ፣ በትክክል ሳልዘል ብቀር ወይም የአደጋ መከላከያ ትጥቄ የሆነ እክል ቢያጋጥመው ምን እሆናለሁ? ቀላል አደጋ ብቻ ነው የሚደርስብኝ ወይስ በጣም ልጎዳ አልፎ ተርፎም ልሞት እችላለሁ?’

አንድ ክርስቲያን በመዝናኛ ስም ሳያስፈልግ ሕይወቱን አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ማድረጉ ከይሖዋ ጋር የመሠረተውን ውድ ዝምድና የሚነካበት ከመሆኑም ሌላ በጉባኤ ውስጥ አንዳንድ መብቶችን ለማግኘት ብቁ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 3:2, 8-10፤ 4:12፤ ቲቶ 2:6-8) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ክርስቲያኖች በሚዝናኑበት ጊዜም እንኳ ፈጣሪያችን ለሕይወት የሚሰጠውን ከፍ ያለ ቦታ ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርባቸዋል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.4 ፓራሹት አድርጎ ከሕንፃዎች፣ ከድልድዮች ወይም ከቋጥኞች ላይ መዝለልን የሚጠይቀው ይህ ስፖርት በጣም አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ በዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ ፓርክ አገልግሎት ታግዷል።