ጥሩ ጣዕም ያላቸውን የእውነት ቃላት መናገር

ጥሩ ጣዕም ያላቸውን የእውነት ቃላት መናገር

ጥናት 1

ጥሩ ጣዕም ያላቸውን የእውነት ቃላት መናገር

1–3. የሰው ልጅ የመናገር ችሎታ የተገኘው እንዴት ነው? እንዴትስ ሊስፋፋ ቻለ?

1 ታላቁ የንግግር ፈጣሪ ይሖዋ ነው። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጡራን በሙሉ ይህ አስደናቂ የሆነ በንግግር ግንኙነት የማድረግ ችሎታ እንዲኖራቸው በማድረጉም ሊመሰገን የሚገባው እርሱ ነው። አምላክ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ጥሩ ስለሆነ ለሰው ልጅ የተሰጠው የንግግር ስጦታም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በያዕቆብ 1:17 ላይ ‘ፍጹም ስጦታ’ ከተባሉት ስጦታዎች መካከል እንደሚገኝበት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። የሥነ ቃላት ሊቅ የሆኑት ሉድቪግ ከህለር ስለ ሰው ልጅ የንግግር ችሎታ ሲናገሩ “አንድ ሰው በሚናገርበት ጊዜ ስለሚፈጸሙት ነገሮች፣ ማለትም አንድ የሐሳብ ብልጭታ መንፈስን አቀጣጥሎ . . . ወደ ቃል ስለሚለወጥበት ሁኔታ ለመረዳት አንችልም። ለሰው ልጅ የተሰጠው የመናገር ችሎታ ፍጹም ምሥጢር ነው። መለኮታዊ ስጦታ ከመሆኑም በላይ ተአምር ነው” ብለዋል።

2 ስለዚህ አዳም እንደተፈጠረ ወዲያው ሐሳቡን የሚገልጽባቸው ቃላት ተሰጥተውታል። በተጨማሪም አዳዲስ ቃላትን የመፍጠርና የማቀነባበር ችሎታ ነበረው። በእርግጥም ሐሳቡን በጥሩ ሁኔታ የመግለጽ ችሎታ ተሰጥቶት ነበር። ሐሳቡን በጥሩ ቃላት ለመግለጽ ከመቻሉም በላይ የሌሎችንም ንግግር የመረዳት ችሎታ ነበረው። አምላክ አዳምን ሊያነጋግረውና መመሪያም ሊሰጠው የቻለው በዚህ ምክንያት ነው። አዳምም በተራው ከሔዋን ጋር ለመነጋገር ይችል ነበር። — ዘፍ. 1:27–30፤ 2:16–20

3 ይሁን እንጂ በምድር ላይ ክፋት እጅግ መስፋፋት በጀመረበት ጊዜ አምላክ በባቤል ግንብ የሰው ልጆችን ንግግር ዘበራረቀ። (ዘፍ. 11:4–9) በዛሬው ጊዜ ብዙ ቋንቋዎችና የቋንቋ ቤተሰቦች ሊኖሩ የቻሉት በዚህ ምክንያት ነው። ከእነዚህ ቋንቋዎች አንዳንዶቹ ጥቂት ቁጥር ባላቸው ጎሣዎች የሚነገሩ ሲሆኑ አንዳንዶቹ ደግሞ በሚልዮን በሚቆጠሩ ሰዎች የሚነገሩ ናቸው። የሰው ልጅ ቋንቋ ልክ እንደ ሰው ሁሉ ጥንት ከነበረበት የፍጽምና ደረጃ በጣም ርቋል። የሰው ልጅ በቋንቋው ሐሰትን ለማስፋፋትና ሰዎችን ከአምላክ ለማራቅ ብዙ ጊዜ ተጠቅሞበታል።

4. በንግግር ችሎታችን መጠቀም የሚገባን እንዴት ነው?

4 እኛ ግን የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን የንግግር ችሎታችንን በተገቢ ሁኔታ ለመጠቀም እንፈልጋለን። ከሰዎች ጋር ስለ እውነተኛው አምላክ የመነጋገርና ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ሥርዓት ውስጥ የዘላለም ሕይወት ስለማግኘት የሚገልጸውን አስደሳች መልእክት የማካፈል መብት አለን። ይህንንም ሥራ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ በሚችል ሁኔታ እንድንፈጽም ይህ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት መመሪያ መጽሐፍ ተዘጋጅቷል።

5, 6. የምንናገረው ሁሉ እውነት መሆኑ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

5 የእውነትን ቃላት መናገር። የንግግር ችሎታችንን በተገቢ ሁኔታ እንድንጠቀም ከተፈለገ ሁልጊዜ ከአምላክ ቃል ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማማውን እውነት መናገር ይኖርብናል። የሐሰት ንግግር ለአድማጮች መንፈሳዊ ጤንነት ሊሰጥ አይችልም። በዚህም ምክንያት ሐዋርያው ጳውሎስ “ከእኔ የሰማኸውን የጤናማ ቃል ምሳሌ ያዝ” በማለት ጥበብ ያለበት ምክር ሰጥቷል። (2 ጢሞ. 1:13) አንዳንዶች “እውነትን ከመስማት ጆሮቻቸውን” እንደሚመልሱ ጳውሎስ አስጠንቅቋል። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜ “ቃሉን” ማለትም የአምላክን ቃል መስበክ ተገቢ እንደሚሆን ተናግሯል። ስለዚህ የአምላክን ቃል ለስብከታችንና ለምንሰጠው ትምህርት መሠረት ማድረግ ይኖርብናል። ከአምላክ ቃል ዝንፍ ማለት አይገባንም። — 2 ጢሞ. 4:1–5

6 በተገቢው ጊዜ የተነገረ ትክክለኛ ቃል አንድን ሰው በዘላለም ሕይወት ጎዳና መመላለስ እንዲጀምር ሊያነሳሳው ወይም ይህን ጉዞ ቀደም ሲል ጀምሮ ከነበረ ከዚያ የሕይወት ጎዳና እንዳይወጣ ሊረዳው እንደሚችል እንገነዘባለን። (ምሳሌ 18:21፤ ያዕ. 5:19, 20) ስለዚህ የአምላክ አገልጋዮች የሆንን ሁሉ በምንናገራቸው ቃላት በተገቢ ሁኔታ መጠቀም በጣም ያስፈልገናል። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትም አበክሮ ሊያስገነዝብ የሚፈልገው ይህንን ቁም ነገር ነው።

7–9. አብዛኛውን ጊዜ በጣም ጥሩ ውጤት የሚያስገኘው እንዴት ያለ አነጋገር ነው?

7 የቃላት አመራረጥ። ቃላት በተናጋሪው አእምሮ ውስጥ ያሉትን ሐሳቦች ወደ አድማጮቹ ለማስተላለፍ የሚያገለግሉ መሣሪያዎች ናቸው። ተናጋሪው በጥሩ ሁኔታ ሐሳቡን ሊያስተላልፍ የሚችለው ደግሞ ሐሳቡን በትክክል የሚገልጹለትንና አድማጮቹ በቀላሉ የሚረዷቸውንና የሚያውቋቸውን ቃላት መርጦ ሲጠቀም ብቻ ነው። በመጀመሪያ ላይ ጥሩ ቃላትን መምረጥ ቀላል አይሆንም። ጠቢብ የነበረው የእስራኤል ሕዝብ አደራጅ ንጉሥ ሰሎሞን እንኳን “ብዙ ምሳሌዎችን መረመረና ፈላለገ አስማማም። ሰባኪው ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ።” (መክ. 12:9, 10) ስለዚህ ተፈላጊና ጥሩ ቃላትን ለማግኘት የአእምሮ ጥረት፣ መፈላለግና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ያስፈልጋል። በዚሁ የመጽሐፍ ቅዱስ ምዕራፍ በቁጥር አሥራ አንድ ላይ በደንብ የተመረጡ ጥሩ ቃላት የሚያስገኙት ውጤት ተገልጾአል። “የጠቢባን ቃል” ሰዎች በሕይወት ጎዳና ላይ ጸንተው እንዲመላለሱ ለመቀስቀስና ለማበረታታት ስለሚያገለግል “በበሬ መውጊያ” ተመስሏል።

8 በመጀመሪያ መማር ከሚያስፈልጉን መሠረታዊ ሥርዓቶች አንዱ በቀላል ቃላት መጠቀም ነው። ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ ንግግር ለመናገር አስቸጋሪ ወይም የተወሳሰቡ ቃላትን መጠቀም አስፈላጊ አይደለም። እንዲያውም ንግግርን ለመረዳት ቁልፍ ከሆኑት ነገሮች አንዱ በቀላል ቃላት መጠቀም ነው። ንግግሩን ለማስታወስም ትልቅ እርዳታ ያበረክታል። “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ከሚሉት የመጽሐፍ ቅዱስ የመክፈቻ ቃላት የበለጠ ቀላል የሆነ፣ ግን ክብርና ግርማ ያለው ቃል ሊገኝ ይችላልን? እነዚህን ቃላት ልትረሳቸው አትችልም። ጠቢቡ የሕዝብ አደራጅም ከብዙ ጥናትና ምርምር በኋላ በመጨረሻ ላይ የደረሰበት መደምደሚያ በተመሳሳይ ቀላል በሆኑ፤ ግን ትልቅ ግርማና ክብር ባላቸው ቃላት የተገለጸ ነው። “የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ እንስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፤ እግዚአብሔርን ፍራ፣ ትዕዛዙንም ጠብቅ።” — መክ. 12:13

9 ግልጽ የሆነውን የአምላክ እውነት ድምፅ የሚያፍኑ ቃላትን ለማስወገድ እንፈልጋለን። ‘ያለ እውቀት በሚነገር ቃል ምክርን ለማጨለም’ አንፈልግም። (ኢዮብ 38:2) “የመለከት ድምፅ ግልጽ ያልሆነ ጥሪ ቢያሰማ” ማን ሊሰማና ሊረዳው ይችላል? — 1 ቆሮ. 14:8 አዓት

10, 11. ኢየሱስ በንግግር ረገድ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው?

10 ሁላችንም ግሩም ከሆነው የኢየሱስ ምሳሌ ጥቅም ልናገኝ እንችላለን። በጣም ቀላል የሆነው አነጋገሩና ዕለት ተለት በሕይወት ውስጥ ከሚያጋጥሙት ነገሮች ወስዶ ያቀረባቸው ምሳሌዎች በአድማጮቹ ላይ ከፍተኛ ውጤት አስከትለው ነበር። በማቴዎስ ወንጌል ውስጥ ከምዕራፍ አምስት እስከ ምዕራፍ ሰባት ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውንና በቅፍርናሆም አጠገብ በሚገኝ ተራራ ላይ ያደረገውን ንግግር እናስታውስ። በጣም የተራቀቀ ዲስኩር ነበርን? አልነበረም። ግራ በሚያጋቡ ቃላት ተጠቅሟልን? አልተጠቀመም። ዋነኛው የኢየሱስ ትኩረት እውነት የሰዎችን ልብ ለመንካት እንዲችል ወደ አእምሮአቸው እንዲገባ ማድረግ ነበር። በእርግጥም የአባቱ የይሖዋ አስተሳሰብ ነበረው። የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ በንግግር ረገድ መከተል የሚገባቸው የኢየሱስን አርዓያ ነው።

11 ግልጽ፣ ቀላልና በደንብ ታስቦባቸው የተመረጡ የእውነት ቃላት የሚኖራቸውን ኃይል አቅልለን አንመልከት። ሊያስደስቱ፣ ሊመስጡና ለሥራ ሊቀሰቅሱ ይችላሉ። በሉቃስ 4:22 ላይ የሚገኘው ታሪክ ስለ ኢየሱስ አነጋገር ሲገልጽ “ሁሉም ስለ እርሱ ጥሩ ምሥክርነት መስጠትና ከአፉ በሚወጡት ማራኪ ቃላት መደነቅ ጀመሩ” ይላል። [አዓት] ሐዋርያቱም ቢሆኑ በጉጉት የሚያዳምጡ ብዙ ሰዎችን አግኝተዋል። እነዚህ ሐዋርያት ይህን ያህል የሰዎችን ትኩረት ሊስቡ የቻሉት በዘመኑ የነበሩት ታላላቅ አይሁዶች እንደተናገሩት ‘ያልተማሩና ተራ ሰዎች ሆነው ሳሉ’ ነበር። (ሥራ 4:13) ታዲያ ይህን የመሰለ የንግግር ችሎታ ከየት አገኙ? የንግግር ዘዴያቸውን የተማሩት ከጌታቸው ከክርስቶስ ነበር። ታዲያ ይህ በዘመናችን ላሉ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ፣ ለወጣቶችም ሆነ ለሽማግሌዎች እጅግ የሚያበረታታ አይደለምን?

12. ወላጆች ልጆቻቸውን ሐሳባቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲገልጹ እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ?

12 ወላጆች ልጆቻቸው በጥሩ ሁኔታ ሐሳባቸውን ለመግለጽ እንዲችሉ ብዙ ሊረዷቸው ይችላሉ። ራሳቸው ምሳሌ በመሆንና ልጆቻቸውን በማስተማር በቤታቸው ውስጥ በየዕለቱ ጥሩ የንግግር ችሎታ ሊቀርጹባቸው ይችላሉ። ለአንድ ሰው አነጋገር መመሪያ ሊሆኑ የሚገባቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በልጆቻቸው አእምሮ ውስጥ እንዲሰርጹ ሊያደርጉ ይችላሉ። (ዘዳ. 6:6–9) ብዙ ቤተሰቦች ሁልጊዜ ጠዋት ጠዋት ጥቂት ጊዜ መድበው ቅዱሳን ጽሑፎችን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት የቀኑን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይወያያሉ። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ መጠበቂያ ግንብ ወይም ንቁ! መጽሔት አብረው ያነባሉ። ይህን ማድረጋቸው ለቤተሰቡ አስደናቂ የሆነ ማሠልጠኛ ይሰጣል። አዳዲስ ቃላትን እንዲማሩ ከማስቻሉም በላይ እንዴት እነዚህን ቃላት ተጠቅመው ሐሳባቸውን በጥሩ ሁኔታ ለሌሎች ሊገልጹ እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል። በተጨማሪም ቤተሰቡ ይህን ሲያደርግ ይሖዋ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ያለውን አስተሳሰብ ሊያውቅ ይችላል። እውቀታቸውም በዕለታዊ አነጋገራቸው ላይ ይንጸባረቃል።

13–16. ሁላችንም ከቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት የተሟላ ጥቅም ለማግኘት ከፈለግን በየግላችን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት በመካፈል እድገት ማሳየት። በአገልግሎት ዕድገት ለማሳየት ልባዊ ፍላጎት ያለን ሁሉ በዚህ መመሪያ መጽሐፍ ውስጥ የተዘረዘሩትን ሥርዓተ ትምህርቶች በመከተል ‘አስደሳችና ትክክል የሆኑትን የእውነት ቃላት’ ለመናገር እንችላለን። ዕድሜህና የትምህርት ደረጃህ የቱንም ያህል ቢሆን በይሖዋ አመራርና በመንፈሱ ከተማመንክ እድገት ልታሳይና በክርስቲያናዊ አገልግሎትህ ልትሻሻል ትችላለህ። ይሁን እንጂ አስፈላጊውን ጥረት ማድረግ ይኖርብሃል። “ማደግህ በነገር ሁሉ እንዲገለጥ ይህን አስብ፣ ይህንም አዘውትር” ተብለህ ተመክረሃል። — 1 ጢሞ. 4:15

14 ከእያንዳንዳችን ከሚፈለጉት ጥረቶች መካከል በሁሉም የይሖዋ ሕዝቦች የጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ ማድረግና በዚህም ውሳኔ መጽናት ይገኝበታል። በተለይ በየሳምንቱ በሚደረገው ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ስብሰባ ላይ የሚከተለውን የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር እንድትፈጽም የሚያስችልህ እርዳታ ይሰጣል። “የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገር የማያሳፍርም ሠራተኛ ሆነህ፣ የተፈተነውን ራስህን ለእግዚአብሔር ልታቀርብ ትጋ።” — 2 ጢሞ. 2:15

15 በጉባኤው ስብሰባዎች ላይ የሚገኝ ማንኛውም ሰው፣ ወንድም ሆነ ሴት፣ ወጣትም ሆነ ሽማግሌ በዚህ ትምህርት ቤት ለመሰልጠን ሊመዘገብና ከትምህርት ቤቱም ከሚገኘው ጥቅም ተሳታፊ ሊሆን ይችላል። የተጠመቅህ ሆንክም አልሆንክ ልትመዘገብ ትችላለህ። ምናልባት በቂ የሆነ ዓለማዊ ትምህርት ያላገኙ ካሉ በሥጋዊ መንገድ ጠቢባን የሆኑ፣ ከትላልቅ ሰዎች የተወለዱ፣ በዓለማዊ አመለካከት ብዙ የተማሩ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንደማይቀበሉ አምላክ አስቀድሞ ያወቀ መሆኑን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮ. 1:26–29) በዓለም አመለካከት የተናቁት ግን መልእክቱን ተቀብለው እውነትን ለተራቡ ሌሎች ሰዎች በፈቃደኝነት እንደሚያስተላልፉ አስቀድሞ አውቋል። በዚህ ትምህርት ቤት በመመዝገብና የሚሰጡትን ትምህርቶች በታማኝነት በመከታተል ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ጥሩ ጣዕም ያላቸው የእውነት ቃላት ለመናገር የሚያስችልህን እውቀት ለማግኘት ትችላለህ። ይህም አንተንም ሆነ የሚሰሙህን የሚያረካና የሚያስደስት ይሆናል።

16 ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህን የትምህርት ፕሮግራም በትጋት ከተከታተልክ ንጉሥ ዳዊት “አቤቱ፣ ረድኤቴ መድኃኒቴም፣ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” በማለት የጸለየለትን ነገር ለማግኘት እንደምትፈልግ በአነጋገርህና በድርጊትህ ታሳያለህ። (መዝ. 19:14) እያንዳንዱ ክርስቲያን በደንብ የመናገር ችሎታ እንዲኖረውና በማንኛውም ጊዜ ፈጣሪውን የሚያስደስት ቃል እንዲናገር ጠንካራ ፍላጎት ሊኖረው ይገባል። ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችል በጣም ጠቃሚ የሆነ እርዳታ ሊሰጥህ ይችላል።

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]