በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ርቆ በሚገኝ አካባቢ መስበክ

የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ርቆ በሚገኝ አካባቢ መስበክ

በ2014 የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል በአውሮፓና በሰሜን አሜሪካ ወዳሉና በስተ ሰሜን ርቀው ወደሚገኙ አካባቢዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለማዳረስ አዲስ ዝግጅት መደረጉን ገለጸ። (የሐዋርያት ሥራ 1:8) መጀመሪያ ላይ ትኩረት የተደረገው በአላስካ (ዩናይትድ ስቴትስ)፣ በላፕላንድ (ፊንላንድ) እንዲሁም በኑናቩትና በሰሜን ምዕራብ በሚገኙ የካናዳ ክልሎች ላይ ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በነዚህ አካባቢዎች ሲሰብኩ ቆይተዋል። ሆኖም የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ የነበረ ሲሆን እንቅስቃሴያቸውም በአብዛኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከማሰራጨት ያለፈ አልነበረም።

በአዲሱ ዝግጅት መሠረት በእነዚህ አካባቢዎች ያለውን የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ የሚመሩ ቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች (አቅኚዎች) በተመረጡ ቦታዎች ላይ ቢያንስ ለሦስት ወራት ያህል እንዲቆዩ ግብዣ አቅርበዋል። ከነዋሪዎቹ መካከል መጽሐፍ ቅዱስን የመማር ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ከተገኙ እነዚህ ሰባኪዎች ቆይታቸውን ሊያራዝሙና ለሕዝብ ክፍት የሆኑ ስብሰባዎችን ሊያካሂዱ ይችላሉ።

እርግጥ ነው፣ ይህ አካባቢ የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉት። በባሮው፣ አላስካ እንዲያገለግሉ ከተመደቡት ሁለት አቅኚዎች አንደኛው ቀደም ሲል ይኖር የነበረው በደቡባዊ ካሊፎርኒያ ሲሆን ሌላኛው ይኖር የነበረው ደግሞ በጆርጂያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ነበር። በባሮው ባሳለፉት የመጀመሪያ ክረምት አየሩ በጣም ቀዝቃዛ ከመሆኑ የተነሳ ከዜሮ በታች 38 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ደርሶ ነበር! ይሁንና እዚያ በሄዱ በጥቂት ወራት ውስጥ የከተማዋን 95 በመቶ የሚያክሉ ቤቶች ያዳረሱ ከመሆኑም ባሻገር ከአራት ሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል፤ ከእነዚህ መካከል ጆን የተባለ አንድ ወጣት ይገኝበታል። እሱና የሴት ጓደኛው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ እያጠኑ ነው፤ በተጨማሪም ጆን የተማረውን ነገር ለጓደኞቹና ለሥራ ባልደረቦቹ ይናገራል። በተጨማሪም JW Library የተባለውን አፕሊኬሽን በሞባይሉ ላይ በመጫን ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር ከተባለው ቡክሌት የዕለቱን ጥቅስ ያነብባል።

የካናዳ ክፍል በሆነችው በኑናቩት ውስጥ ወደሚገኘው ወደ ራንኪን ኢንሌት የሚወስድ መንገድ የለም። በመሆኑም ሁለት አቅኚዎች ወደዚህች ትንሽ መንደር በአውሮፕላን ተጉዘው በመሄድ ከበርካታ ሰዎች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረዋል። አንድ ሰው በመንግሥት አዳራሻችን ውስጥ ምን ይከናወናል? የሚለውን ቪዲዮ ከተመለከተ በኋላ በእነሱ አካባቢ የመንግሥት አዳራሽ የሚገነባው መቼ እንደሆነ ጠየቀ። በመቀጠልም “በምትገነቡበት ጊዜ እዚህ ካለሁ ስብሰባችሁ ላይ እገኛለሁ” በማለት ተናግሯል።

የርኤሞች ብዛት ከሰዎች ቁጥር አሥር እጥፍ በሚበልጥባት በሳቩኮስኪ፣ ፊንላንድ የተመደቡ ሁለት አቅኚዎች “አየሩ በጣም ቀዝቃዛ ሲሆን አካባቢው በበረዶ የተሸፈነ ነው” በማለት ተናግረዋል። ያም ቢሆን እነዚህ አቅኚዎች የሄዱት በጣም ጥሩ ወቅት ላይ እንደሆነ ገልጸዋል። ለምን? እንዲህ ብለዋል፦ “ክልላችንን አጣርተን መሸፈን ችለናል። ወደ መንደሮቹና ራቅ ወዳሉት አካባቢዎች በሚወስዱት መንገዶች ላይ የተጋገረው በረዶ ስለተነሳ መንገዱ በጥሩ ይዞታ ላይ ይገኝ ነበር። አየሩ ቀዝቃዛ መሆኑ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን ቤት ውስጥ እንዲያሳልፉ አድርጓቸው ነበር።”

የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በስተ ሰሜን ርቀው ወደሚገኙ አካባቢዎች ለማዳረስ የምናደርገው ጥረት የሰዎችን ትኩረት ስቧል። ሁለት አቅኚዎች፣ በአላስካ ውስጥ የምትገኝን አንድ ከተማ ከንቲባ አነጋግረው ነበር፤ ከንቲባዋ ከእነሱ ጋር ያደረገችውን ውይይት አስመልክታ አዎንታዊ የሆነ አስተያየት በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ አስፍራለች፤ ከዚህም ሌላ የአምላክ መንግሥት ምንድን ነው? የተባለውን ትራክት ፎቶግራፍም አውጥታለች።

በሄይንዝ፣ አላስካ የተመደቡ ሁለት አቅኚዎች በሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ስምንት ሰዎች ተገኝተው ነበር፤ በአካባቢው የሚታተም ጋዜጣ ከቴክሳስና ከኖርዝ ካሮላይና የመጡ ሁለት ሰዎች፣ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ቤታቸው ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲማሩ ግብዣ እያቀረቡ መሆናቸውን ዘግቧል። ዘገባው “ለበለጠ መረጃ jw.orgን ተመልከቱ” በማለት ይደመድማል።