በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች

ቋንቋ ምረጥ አማርኛ

በካናዳ ለሚኖሩ አቦርጅኖች ምሥራቹን መስበክ

በካናዳ ለሚኖሩ አቦርጅኖች ምሥራቹን መስበክ

በካናዳ ከ60 በላይ የሚሆኑ የአቦርጅን ቋንቋዎች የሚነገሩ ሲሆን 213,000 ገደማ የሚሆኑ ካናዳውያን አፋቸውን የፈቱት ከእነዚህ ቋንቋዎች በአንዱ እንደሆነ ተናግረዋል።

በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ለእነዚህ ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለመስበክ ሲሉ ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል አንዳንዶቹን ተምረዋል። በ2015 መጨረሻ ከ250 በላይ ሰዎች በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን የአቦርጅን ቋንቋ ትምህርት አጠናቀዋል።

በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች አጫጭር ቪዲዮዎችንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን በስምንት የአቦርጅን ቋንቋዎች ማለትም በሞሆክ፣ በሰሜን ኦጂብዋ፣ በብላክፉት፣ በአልጎንኩዊን፣ በኢኑክቲቱት፣ በኦዳዋ፣ በዌስት ስዋምፒ ክሪና በፕሌንስ ክሪ ተርጉመዋል። *

የአቦርጂኖችን ቋንቋ የሚማሩ ሰዎች ቋንቋውን መማር ቀላል እንዳልሆነ ይናገራሉ። ካርማ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “የብላክፉትን ቋንቋ የትርጉም ቡድን መርዳት ስጀምር ዓይኔ ተሸፍኖ እንድሠራ የተደረግኩ ሆኖ ነበር የተሰማኝ። ቋንቋውን በደንብ አላውቀውም። ማንበብም ሆነ ድምፆቹን መለየት አልችልም ነበር።”

በዌስት ስዋምፒ ክሪ የትርጉም ቡድን ውስጥ የሚሠራው ቴረንስ “አብዛኞቹ ቃላት ረጅምና ለመጥራት የሚከብዱ ናቸው” በማለት ተናግሯል። በማኒቶሊን ደሴት፣ ኦንታሪዮ የሚያገለግል ዳንኤል የተባለ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንዲህ ብሏል፦ “ቋንቋውን ለመማር የተዘጋጁ በቂ መሣሪያዎች የሉንም። ኦዳዋ ቋንቋ ለመማር ከሁሉ የተሻለው ዘዴ ቋንቋውን ወደሚናገሩ አረጋውያን ጠጋ ማለት ነው።”

ታዲያ ይህ ሁሉ ልፋት ምን ውጤት አስገኝቶ ይሆን? የኦጂብዋ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነች አንዲት ሴት፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉት ጥረት ከሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ ለየት እንደሚያደርጋቸው ተናግራለች። የይሖዋ ምሥክሮች፣ በየቤቱ በመሄድ ለሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በኦጂብዋ ቋንቋ ማንበባቸው ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ቀላል እንዲሆንላቸው እንደሚረዳ ገልጻለች።

አልበርታ ውስጥ ብለድ ትራይብ በሚባል አካባቢ ያደገ በርት የተባለ ተርጓሚ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ የብላክፉት ቋንቋ ተናጋሪዎች ጽሑፉን እቅፍ አድርገው ‘በቋንቋዬ አገኘሁ። ይህ ለእኔ የተዘጋጀ ነው!’ ብለው ሲናገሩ ሰምቻለሁ። በቋንቋቸው የተዘጋጀ ቪዲዮ ሲያዩ ብዙ ጊዜ ዓይናቸው እንባ ሲያቀር ተመልክቻለሁ።”

የክሪ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነች ሴት መጽሐፍ ቅዱስን መማር የሚኖርብን ለምንድን ነው? የተባለውን ቪዲዮ በቋንቋዋ በመመልከቷ በጣም ተደስታለች። እናቷ እያናገረቻት እንዳለ ሆኖ እንደተሰማት ተናግራለች።

ከፍተኛ ጥረት ይጠይቃል

በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎችን የሚያጽናናውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ለአቦርጅኖች ለማድረስ ልዩ ጥረት አድርገዋል። ቴረንስና ባለቤቱ ኦርሊን ምሥራቹን ለመስበክ ስላደረጉት ጉዞ እንዲህ በማለት ይናገራሉ፦ “ሊትል ግራንድ ራፒድስ በሚባለው አካባቢ ለመስበክ ከሄደው ቡድን መካከል የነበርን ሲሆን እዚህ ቦታ ለመድረስ በበረዶ ላይ ለ12 ሰዓታት መንዳት ነበረብን። ይሁንና የሰዎቹ ምላሽ በጣም የሚያስገርም ነበር!”

አንዳንዶች ደግሞ እነዚህ ሕዝቦች ወደሚኖሩባቸው አካባቢዎች ቀረብ ለማለት ሲሉ የተመቻቸ ቤታቸውን ለቀዋል። ዳንኤልና ባለቤቱ ሊአን ለሦስት ወር የስብከት ዘመቻ በማኒቶሊን ደሴት ከቆዩ በኋላ ቤታቸውን ለቀው እዚያ ለመኖር ወሰኑ። ዳንኤል “ከሰዎቹ ጋር ለመላመድና ያሳዩትን ፍላጎት ለማሳደግ ከበፊቱ የበለጠ ጊዜ ያለን መሆኑ አስደስቶናል” በማለት ተናግሯል።

“ከልብ ስለምወዳቸው ነው”

የይሖዋ ምሥክሮች ለአቦርጅኖች ለመስበክ ይህን ያህል ጥረት የሚያደርጉት ለምንድን ነው? የበርት ባለቤት የሆነችው ሮዝ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “እኔ ራሴም አቦርጅን ነኝ፤ የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስገኘውን ጥቅም በራሴ ሕይወት አይቻለሁ፤ ይህም ሌሎችን ለመርዳት ያነሳሳኛል።”

ኦርሊን እንዲህ ብላለች፦ “የክሪ ሕዝቦች በፈጣሪያችን የሚመሩበት አጋጣሚ እንዲያገኙ እፈልጋለሁ፤ ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ እንዲሁም በዛሬው ጊዜ የሚያጋጥሟቸውን ፈተናዎች እንዲወጡ መርዳት ትልቅ መብት ነው።”

ማርክ የሚያገለግለው በብላክፉት የትርጉም ቡድን ውስጥ ነው። በአካባቢው የሚገኙ አቦርጅኖችን ለመርዳት ጥረት የሚያደርገው ለምንድን ነው? “ከልብ ስለምወዳቸው ነው” በማለት መልስ ሰጥቷል።

^ አን.4 ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል አንዳንዶቹ በዩናይትድ ስቴትስ በሚኖሩ አቦርጅኖችም ይነገራሉ።