የጀርመን ክፍለ ሃገር በሆነችው በሽሌስቪኽ ሆልሽታይን ምዕራባዊ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ ሃሊገን ተብለው የሚጠሩ ትናንሽ ደሴቶች ይገኛሉ፤ በሰሜን ባሕር ላይ ተራርቀው የሚገኙት እነዚህ ደሴቶች ወደ 300 የሚጠጉ ነዋሪዎች አሏቸው። ታዲያ እነዚህ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩትን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት መስማት የሚችሉት እንዴት ነው?—ማቴዎስ 24:14

የይሖዋ ምሥክሮች ወደ አንዳንዶቹ ደሴቶች ለመጓዝ ጀልባ ይጠቀማሉ። በሌሎቹ ደሴቶች ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ለማግኘት ግን ጥቂት የይሖዋ ምሥክሮች ለየት ያለ ዘዴ ይጠቀማሉ፤ አምስት ኪሎ ሜትር ገደማ በባሕሩ ወለል ላይ በእግራቸው ይጓዛሉ። ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?

ማዕበሉ የሚሸሽበትን ጊዜ መጠቀም

ሚስጥሩ ያለው በማዕበሉ ላይ ነው። በሃሊገን ደሴቶች አካባቢ የሰሜን ባሕር ከፍታ በየስድስት ሰዓቱ በሦስት ሜትር ገደማ ሊጨምር ወይም ሊቀንስ ይችላል! ማዕበሉ በሚሸሽበት ጊዜ በውኃ ተሸፍኖ የነበረው መሬት ደረቅ ይሆናል፤ በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሦስት ደሴቶች በእግራቸው ተጉዘው መድረስ ይችላሉ።

ይህ ጉዞ ምን ይመስላል? ወደዚህ አካባቢ የሚሄደውን ቡድን የሚመራ ኡልሪኽ የተባለ አካባቢውን በደንብ የሚያውቅ ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ሃሊገን ውስጥ ወዳለው አንደኛው ደሴት ለመድረስ ሁለት ሰዓት ገደማ ይወስዳል። ብዙውን ጊዜ የምንጓዘው በባዶ እግራችን ነው። ምክንያቱም የባሕሩን ወለል ለማቋረጥ ቀላልና አመቺ የሆነው መንገድ ይህ ነው። አየሩ ቀዝቃዛ በሚሆንበት ጊዜ ደግሞ ቦቲ ጫማ እናደርጋለን።”

አካባቢው በገሃዱ ዓለም ያለ አይመስልም። ኡልሪኽ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “ሌላ ፕላኔት ላይ ያላችሁ ሊመስላችሁ ይችላል። በባሕሩ ወለል ላይ የሚገኙት አንዳንዶቹ አካባቢዎች ረግረጋማ ሌሎቹ ደግሞ ድንጋያማ ናቸው፤ ባሕር ውስጥ በሚበቅል ሣር የተሸፈኑ ቦታዎችም አሉ። በዙሪያችሁ በርካታ የባሕር ወፎችን፣ ሸርጣኖችንና ሌሎች እንስሳትን ታያላችሁ።” ቡድኑ በረግረጋማ ቦታዎቹ ላይ የተፈጠሩ በጀርመንኛ ፕሪሌ ተብለው የሚጠሩ ትናንሽ ወንዞችን ማቋረጥ የሚኖርበት ጊዜ አለ።

ይህን ጉዞ የሚያደርጉ ሰዎች ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ይኖርባቸዋል። ኡልሪኽ እንዲህ ሲል አስጠንቅቋል፦ “በቀላሉ ልትጠፉ ትችላላችሁ፤ አካባቢው በጭጋግ ከተሸፈነ ደግሞ ሁኔታው የከፋ ነው። በመሆኑም ኮምፓስና ጂፒኤስ [አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ] እንጠቀማለን፤ እንዲሁም ማዕበሉ እንዳይዘን የጉዞ ፕሮግራማችንን በጥብቅ እንከተላለን።”

ከሃሊገን ደሴቶች በአንዱ ላይ መስበክ

ይህ ሁሉ ጥረት ምን ውጤት አስገኝቶ ይሆን? ኡልሪኽ መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! አዘውትረው ስለሚያነቡ አንድ የ90 ዓመት አረጋዊ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ቀን፣ በቂ ጊዜ ስላልነበረን እሳቸው ጋር ሳንሄድ ቀረን። ሰውየው ግን ለመሄድ ከመነሳታችን በፊት በብስክሌት ደረሱብን፤ ከዚያም ‘መጠበቂያ ግንብ መጽሔቴን አትሰጡኝም እንዴ?’ በማለት ጠየቁን። እኛም መጽሔቱን በደስታ ሰጠናቸው።”