በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖት አባላት ጋር በመቀላቀል አምልኮ ያከናውናሉ?

የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች ሃይማኖት አባላት ጋር በመቀላቀል አምልኮ ያከናውናሉ?

 የይሖዋ ምሥክሮች የየትኛውም ሃይማኖት አባላት ከሆኑ ሰዎች ጋር ከእምነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን አንስተው መወያየት ያስደስታቸዋል፤ ሆኖም የሌሎች ሃይማኖት አባላት ከሆኑ ሰዎች አብረው አምልኮ በማከናወን ሃይማኖትን አይቀላቅሉም። መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘ፍጹም አንድነት’ ሊኖራቸው እንደሚገባ ይናገራል፤ እንዲህ ያለው አንድነት ዋና ገጽታ ደግሞ የእምነት አንድነት ነው። (1 ቆሮንቶስ 1:10፤ ኤፌሶን 4:16፤ ፊልጵስዩስ 2:2) ይህም እንደ ፍቅር፣ ርኅራኄና ይቅር ባይነት ያሉት ባሕርያት ጠቃሚ ስለመሆናቸው ከማመን ያለፈ ነገርን ይጨምራል። ሃይማኖታዊ እምነታችን የተመሠረተው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው ትክክለኛ እውቀት ላይ ነው፤ እምነታችን በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ካልሆነ ምንም ዋጋ አይኖረውም።—ሮም 10:2, 3

 መጽሐፍ ቅዱስ ሌላ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር አብሮ አምልኮ ማከናወንን አቻ ባልሆነ ቀንበር ከመጠመድ ጋር ያወዳድረዋል፤ እንዲህ ያለው ጥምረት የአንድን ክርስቲያን እምነት መጉዳቱ አይቀርም። (2 ቆሮንቶስ 6:14-17) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ሃይማኖትን እንዲቀላቅሉ አልፈቀደም። (ማቴዎስ 12:30፤ ዮሐንስ 14:6) አምላክ በሙሴ በኩል የሰጠው ሕግም በተመሳሳይ የጥንቶቹ እስራኤላውያን በዙሪያቸው ከሚኖሩት አሕዛብ ጋር ተቀላቅለው ማምለክ እንደሌለባቸው ይናገራል። (ዘፀአት 34:11-14) ከጊዜ በኋላም ታማኝ እስራኤላውያን ሌላ እምነት ያላቸው ሰዎችን እርዳታ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል፤ ምክንያቱም እንዲህ ያለው እርዳታ ሃይማኖትን ወደመቀላቀል ሊያመራ ይችል ነበር።—ዕዝራ 4:1-3

የይሖዋ ምሥክሮች የሌላ እምነት አባላት ከሆኑ ሰዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ?

 አዎ። ልክ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉ እኛም በአገልግሎታችን ላይ ‘በተቻለ መጠን የብዙ’ ሰዎችን አስተሳሰብና እምነት ለመረዳት እንሞክራለን። (1 ቆሮንቶስ 9:19-22) ከሰዎቹ ጋር በምንነጋገርበት ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች “ጥልቅ አክብሮት” እንድናሳይ የሚሰጠንን ምክር ለመከተል ከልባችን ጥረት እናደርጋለን።—1 ጴጥሮስ 3:15