በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ፦ ከሙሴ ምን እንማራለን?

ሙሴ ማን ነበር?

ሙሴ ማን ነበር?

ሙሴ የሚለውን ስም ስትሰማ መጀመሪያ ወደ አእምሮህ የሚመጣው ነገር ምንድን ነው?

  • እናቱ ቅርጫት ውስጥ አድርጋ ዓባይ ወንዝ ላይ በቄጠማ መካከል የሸሸገችው ሕፃን?
  • በግብፅ የፈርዖን ሴት ልጅ በቅንጦት ብታሳድገውም እስራኤላዊ መሆኑን ያልረሳ ልጅ?
  • ለ40 ዓመታት በምድያም ምድር እረኛ የነበረ ሰው?
  • በእሳት በተያያዘ ቁጥቋጦ ፊት ከይሖዋ * ጋር የተነጋገረ ሰው?
  • የግብፅ ንጉሥ፣ በባርነት የያዛቸውን እስራኤላውያንን እንዲለቅ የጠየቀ ደፋር ሰው?
  • ንጉሡ ለእውነተኛው አምላክ ንቀት ባሳየ ጊዜ አሥር መቅሠፍቶች በግብፅ ላይ እንደሚመጡ በአምላክ አመራር የተናገረ ሰው?
  • እስራኤላውያን ግብፅን ለቀው ሲወጡ የመራቸው ሰው?
  • አምላክ ቀይ ባሕርን ለሁለት ለመክፈል የተጠቀመበት ሰው?
  • ከአምላክ የተቀበላቸውን አሥርቱን ትእዛዛት ለእስራኤላውያን የሰጠ ሰው?

ሙሴ እነዚህን ብቻ ሳይሆን በሕይወቱ ብዙ ነገሮችን አሳልፏል። በመሆኑም ይህ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ በክርስቲያኖች፣ በአይሁዶችና በሙስሊሞች ዘንድ ከፍተኛ አክብሮት ማትረፉ ምንም አያስደንቅም!

ሙሴ አስደናቂ ነገሮችን የፈጸመ ነቢይ እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘዳግም 34:10-12) አምላክ ታላቅ ኃይሉን ለማሳየት በእሱ እንዲጠቀም ፈቃደኛ ሆኗል። ያም ቢሆን ሙሴ ከሰው የተለየ ችሎታ አልነበረውም። በኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ሙሴ ከነቢዩ ኤልያስ ጋር በራእይ ታይቶ ነበር፤ እንደ ኤልያስ ሁሉ ሙሴም “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት ያለው ሰው ነበር።” (ያዕቆብ 5:17፤ ማቴዎስ 17:1-9) ሙሴ እኛ ከሚያጋጥሙን ጋር የሚመሳሰሉ ብዙ ችግሮች የደረሱበት ቢሆንም በተሳካ መንገድ ተወጥቷቸዋል።

ታዲያ ችግሮቹን በተሳካ መንገድ ሊወጣ የቻለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ? ሙሴ ያሳያቸውን ሦስት ግሩም ባሕርያት እንዲሁም እሱ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

^ စာပိုဒ်၊ 7 የአምላክ የግል ስም ይሖዋ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጿል።