በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችና ማብራሪያቸው

ዮሐንስ 16:33—“እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”

ዮሐንስ 16:33—“እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ”

 “እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በእኔ አማካኝነት ሰላም እንዲኖራችሁ ነው። በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ! እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”—ዮሐንስ 16:33 አዲስ ዓለም ትርጉም

 “በእኔ ሰላም እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።”—ዮሐንስ 16:33 አዲሱ መደበኛ ትርጉም

የዮሐንስ 16:33 ትርጉም

 ኢየሱስ ለተከታዮቹ እነዚህን ቃላት የተናገረው ፈተናና ተቃውሞ ቢያጋጥማቸውም እንኳ እነሱም አምላክን ማስደሰት እንደሚችሉ በመግለጽ ሊያጽናናቸው ስለፈለገ ነው።

 “እነዚህን ነገሮች የነገርኳችሁ በእኔ አማካኝነት a ሰላም እንዲኖራችሁ ነው።” የጥቅሱ ቀጣይ ክፍል እንደሚያሳየው እዚህ ላይ የተጠቀሰው ሰላም ከችግር ነፃ መሆንን የሚያመለክት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህ ሰላም ውስጣዊ ሰላምን ያመለክታል። እንዲህ ያለውን ውስጣዊ ሰላም ማግኘት የሚቻለው በኢየሱስ “አማካኝነት” ነው። ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን እንደሚልክ ቃል ገብቷል። ይህ ኃያል “ረዳት” የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ማንኛውንም ችግር በተሳካ ሁኔታ ለመወጣት ያስችላቸዋል።—ዮሐንስ 14:16, 26, 27

 “በዓለም ሳላችሁ መከራ ይደርስባችኋል፤ ነገር ግን አይዟችሁ!” ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ ፈተና እንደሚያጋጥማቸው፣ ማለትም ግፍና ስደት እንደሚደርስባቸው ሳይሸሽግ ተናግሯል። (ማቴዎስ 24:9፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12) ያም ቢሆን ኢየሱስ “አይዟችሁ” በማለት አበረታቷቸዋል።—ዮሐንስ 16:33

 “እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” እዚህ ላይ ያለው “ዓለም” የሚለው ቃል ከአምላክ የራቁትን ክፉ ሰዎች ያመለክታል። b አንደኛ ዮሐንስ 5:19 ‘መላው ዓለም በክፉው ማለትም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር’ እንደሆነ ይናገራል። በመሆኑም የዚህ “ዓለም” ሰዎች አስተሳሰባቸውም ሆነ ምግባራቸው ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚጋጭ ነው።—1 ዮሐንስ 2:15-17

 ሰይጣንና የእሱ ዓለም ኢየሱስ የአምላክን ፈቃድ እንዳይፈጽም ማለትም ሌሎችን ስለ አምላክ እንዳያስተምርና ፍጹም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ እንዳይሰጥ ሊያግዱት ሞክረው ነበር። (ማቴዎስ 20:28፤ ሉቃስ 4:13፤ ዮሐንስ 18:37) ሆኖም ኢየሱስ ዓለም በአስተሳሰቡ ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድርበትና ከአምላክ እንዲያርቀው አልፈቀደም። እስከ ሞት ድረስ እንኳ ታማኝነቱን ጠብቋል። ኢየሱስ ዓለምን እንዳሸነፈውና “የዚህ ዓለም ገዢ” የሆነው ሰይጣን በእሱ ላይ “ምንም ኃይል” እንደሌለው የተናገረው ለዚህ ነው።—ዮሐንስ 14:30

 ኢየሱስ ተከታዮቹ ንጹሕ አቋማቸው በሚፈተንበት ጊዜም ጭምር ልክ እንደ እሱ ለአምላክ ታማኝ መሆን እንደሚችሉ የራሱን ምሳሌ ተጠቅሞ አሳይቷቸዋል። በሌላ አባባል ኢየሱስ “እኔ ዓለምን ማሸነፍ ከቻልኩ እናንተም ትችላላችሁ” ያላቸው ያህል ነበር።

የዮሐንስ 16:33 አውድ

 ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ነው። በቅርቡ እንደሚሞት ስላወቀ ለታማኝ ሐዋርያቱ የመሰነባበቻ ምክር ለመስጠት አጋጣሚውን ተጠቀመበት። ከሰጣቸው ምክር መካከል አንዳንድ ከበድ ያሉ ሐሳቦች ይገኙበታል፤ ለምሳሌ ከዚያ በኋላ እንደማያዩት እንዲሁም ስደት እንደሚደርስባቸው አልፎ ተርፎም እንደሚገደሉ ነገራቸው። (ዮሐንስ 15:20፤ 16:2, 10) እነዚህ ሐሳቦች ሐዋርያቱን ሊያስፈሯቸው ስለሚችሉ ኢየሱስ እነሱን ለማበረታታትና ለማጽናናት በዮሐንስ 16:33 ላይ የሚገኙትን ቃላት ተናገረ።

 ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብና የተወው ምሳሌ በዛሬው ጊዜ ያሉ ተከታዮቹንም ያበረታታል። ሁሉም ክርስቲያኖች፣ መከራ ቢደርስባቸውም እንኳ ለአምላክ ታማኝ መሆን ይችላሉ።

a “በእኔ አማካኝነት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ አገላለጽ “በእኔ ሳላችሁ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ይህም የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከእሱ ጋር ያላቸውን አንድነት ጠብቀው በመኖር ሰላም ማግኘት እንደሚችሉ ይጠቁማል።

b “ዓለም” የሚለው ቃል በዮሐንስ 15:19 እና በ2 ጴጥሮስ 2:5 ላይም ተመሳሳይ ትርጉም አለው።