በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት

ሰይጣን ማን ነው? በእርግጥ እውን አካል ነው?

ሰይጣን ማን ነው? በእርግጥ እውን አካል ነው?

አንዳንድ የዘመናችን ምሁራን ሰይጣን እውን አካል አይደለም ይላሉ። እንዲያውም የሰው ሐሳብ የፈጠረው ነገር እንደሆነ ይናገራሉ። እንዲህ ያለው አመለካከት አዲስ አይደለም። የ19ኛው መቶ ዘመን ገጣሚ የሆኑት ሻርል ፕዬር ቡድሌር “የሰይጣን ዋነኛ ማታለያ እኛን ሕልውና እንደሌለው አድርጎ ማሳመን ነው” በማለት ጽፈዋል።

ሰይጣን በእርግጥ እውን አካል ነው? ከሆነስ የመጣው ከየት ነው? ዓለማችንን ከሚያስጨንቋት ችግሮች በስተጀርባ ያለው የማይታየው ኃይል እርሱ ነው? ከሆነ፣ ከሚያሳድረው መጥፎ ተጽዕኖ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣንን በማይታየው መንፈሳዊ ዓለም ውስጥ የሚገኝ እውን አካል እንደሆነ አድርጎ ይገልጸዋል። (ኢዮብ 1:6) ክፋትና ጭካኔ ስለሚንጸባረቅባቸው ባሕርያቱ እንዲሁም ስለ መጥፎ ድርጊቶቹ ይነግረናል። (ኢዮብ 1:13-19፤ 2:7, 8፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:26) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን ከአምላክና ከኢየሱስ ጋር ያደረጋቸውን ውይይቶች ይዟል።—ኢዮብ 1:7-12፤ ማቴዎስ 4:1-11

ይህ ክፉ አካል ከየት መጣ? አምላክ ሰውን ከመፍጠሩ ከበርካታ ጊዜያት ቀደም ብሎ በኋላ ላይ ኢየሱስ ተብሎ የተጠራውን ‘የበኵር’ ልጁን ፈጠረ። (ቈላስይስ 1:15) ቆይቶም መላእክት ተብለው የሚጠሩት ‘የእግዚአብሔር ልጆች’ ተፈጠሩ። (ኢዮብ 38:4-7 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ሁሉ ፍጥረታቱ ፍጹምና ጻድቅ ነበሩ። ከጊዜ በኋላ ግን ከእነዚህ መላእክት መካከል አንዱ ሰይጣን ሆነ።

 ሰይጣን የሚለው መጠሪያ ሲፈጠር የተሰጠው ስም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ተግባሩን የሚገልጽ ስም ሲሆን “ባላጋራ፣ ጠላት፣ ከሳሽ” የሚል ትርጉም አለው። ሰይጣን ተብሎ የተጠራው ከአምላክ ጋር የሚቃረን አካሄድ ለመከተል በመምረጡ ነው።

በዚህ መንፈሳዊ ፍጡር ውስጥ ኩራትና አምላክን የመቀናቀን ስሜት ስላደገ ሌሎች እርሱን እንዲያመልኩት ፈለገ። እንዲያውም ሰይጣን የአምላክ የበኩር ልጅ የሆነው ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ‘ወድቆ እንዲሰግድለት’ ለማድረግ ሞክሮ ነበር።—ማቴዎስ 4:9

ሰይጣን “በእውነት አልጸናም።” (ዮሐንስ 8:44) እርሱ ራሱ ውሸታም ሆኖ ሳለ አምላክን ውሸታም እንደሆነ አድርጎ በተዘዋዋሪ መንገድ ተናግሯል። ምንም እንኳ እንደ አምላክ መሆን የፈለገው እርሱ ቢሆንም ለሔዋን እንደ አምላክ መሆን እንደምትችል ነግሯታል። መሰሪ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ሔዋን ከአምላክ አስበልጣ እንድታየው በማድረግ የራስ ወዳድነት ምኞቱን አሳክቷል። ሔዋንም ሰይጣንን በመታዘዝ እርሱን አምላኳ እንደሆነ አድርጋ ተቀብላዋለች።—ዘፍጥረት 3:1-7

በአንድ ወቅት እምነት ይጣልበት የነበረው ይህ መልአክ ዓመጽን በማስፋፋት ራሱን ሰይጣን ይኸውም የአምላክም ሆነ የሰዎች ባላጋራና ጠላት አድርጓል። ይህ ክፉ አድራጊ የፈጸመው ተግባር “ስም አጥፊ” የሚል ትርጉም ያለውን “ዲያብሎስ” የተባለ ስምም አሰጥቶታል። ኃጢአትን በመሥራት ረገድ ግንባር ቀደም የሆነው ሰይጣን ከጊዜ በኋላ ሌሎች መላእክትም አምላክን እንዳይታዘዙ በመገፋፋት የዓመጹ ተባባሪ እንዲሆኑ አድርጓል። (ዘፍጥረት 6:1, 2፤ 1 ጴጥሮስ 3:19, 20) እነዚህ መላእክት የሰው ዘር ያለበትን ሁኔታ አላሻሻሉትም። እንዲያውም የሰይጣንን የራስ ወዳድነት አካሄድ በመኮረጃቸው ምክንያት ‘ምድር በዐመፅ ተሞልታለች።’—ዘፍጥረት 6:11፤ ማቴዎስ 12:24

ሰይጣን የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን ያህል ኃይል አለው?

አንድ ወንጀለኛ ማንነቱን የሚጠቁም ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይገኝ ለማድረግ ሲል ወንጀሉን ከፈጸመበት ቦታ የጣት አሻራውን ለማጥፋት ይሞክር ይሆናል። ነገር ግን ፖሊስ በቦታው ሲደርስ ወንጀል እስከተፈጸመ ድረስ ወንጀሉን የፈጸመ ሰው መኖሩ የግድ መሆኑን ይገነዘባል። የመጀመሪያው “ነፍሰ ገዳይ” የሆነው ሰይጣንም ማንነቱን ሊያሳውቅ የሚችል ምንም ዓይነት መረጃ እንዳይገኝ ለማድረግ ይሞክራል። (ዮሐንስ 8:44፤ ዕብራውያን 2:14) ሰይጣን ሔዋንን ባነጋገራት ጊዜ በእባብ በመጠቀም ማንነቱን ደብቋል። ዛሬም ቢሆን ማንነቱን ለመደበቅ ይሞክራል። ሌሎች የሚያሳድረውን ኃይለኛ ተጽዕኖ እንዳያስተውሉ ለማድረግ ሲል “የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሯል።”—2 ቆሮንቶስ 4:4

ይሁን እንጂ ኢየሱስ ብልሹ ከሆነው ከዚህ ዓለም በስተጀርባ ያለው ወንጀለኛ ሰይጣን መሆኑን ተናግሯል። ዲያብሎስን “የዚህ ዓለም ገዥ” ሲል ጠርቶታል። (ዮሐንስ 12:31፤ 16:11) ሐዋርያው ዮሐንስም ‘መላው ዓለም በክፉው ሥር እንደ ሆነ’ ጽፏል። (1 ዮሐንስ 5:19) ሰይጣን ‘ዓለምን ሁሉ ለማሳት’ ‘የሥጋ ምኞትን፣ የዐይን አምሮትንና የኑሮ ትምክህትን’ ውጤታማ በሆነ መንገድ ይጠቀማል። (1 ዮሐንስ 2:16፤ ራእይ 12:9) በጥቅሉ ሲታይ የሰው ዘር እየታዘዘ ያለው ለእርሱ ነው።

በሔዋን ላይ እንደታየው፣ ለሰይጣን የሚታዘዙ ሁሉ እርሱን አምላካቸው ያደርጉታል። ስለዚህ ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:4) የእርሱ አገዛዝ ካስከተላቸው ውጤቶች መካከል ግብዝነት፣ ውሸት፣ ጦርነት፣ መከራ፣ ጥፋት፣ ወንጀል፣ ስግብግብነትና ሙስና ይገኙበታል።

ራስህን ከሰይጣን ተጽዕኖ መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “ራሳችሁን የምትገዙ ሁኑ፤ ንቁም” በማለት ያስጠነቅቃል። ለምን? ምክንያቱም “ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን በመፈለግ እንደሚያገሣ አንበሳ ወዲያ ወዲህ ይዞራል።” (1 ጴጥሮስ 5:8) ይህ ጥቅስ ቆም ብለን እንድናስብ የሚያደርገን ቢሆንም እንኳ ‘በሰይጣን የሚታለሉት’ ራሳቸውን የማይገዙና ነቅተው የማይኖሩ ብቻ መሆናቸውን ማወቃችን የሚያጽናና ነው።—2 ቆሮንቶስ 2:11 የ1954 ትርጉም

ሰይጣን በእርግጥም ሕያው አካል መሆኑን አምነን መቀበላችን እንዲሁም አምላክ ‘እንዲያበረታንና አጽንቶ እንዲያቆመን’ መፍቀዳችን በጣም አስፈላጊ ነው። በዚህ መንገድ ሰይጣንን ‘ልንቃወምና’ ከአምላክ ጎን ልንቆም እንችላለን።—1 ጴጥሮስ 5:9, 10

[በገጽ 12 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]

ዓለማችንን ከሚያስጨንቋት ችግሮች በስተጀርባ ያለው የማይታየው ኃይል ሰይጣን ነው?