በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከተሳሳተ መረጃ ራስህን ጠብቅ

ከተሳሳተ መረጃ ራስህን ጠብቅ

 አሁን የምንኖረው መረጃ ማግኘት ከምንጊዜውም ይበልጥ ቀላል በሆነበት ዘመን ላይ ነው፤ ራስህን ከአደጋ መጠበቅና ጤንነትህን መንከባከብ የምትችልበትን መንገድ ጨምሮ የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት ትችላለህ። ሆኖም መረጃ ለማግኘት በምታደርገው ጥረት ለተሳሳቱ መረጃዎች እንዳትጋለጥ መጠንቀቅ ያስፈልግሃል፤ የተሳሳቱ መረጃዎች በሚከተሉት መልኩ ሊመጡ ይችላሉ፦

 ለምሳሌ ያህል፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት አደገኛ ስለሆነው የተሳሳተ መረጃ ወረርሽኝ ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር። “ጤናን በተመለከተ የሚሰጡ ጎጂና አሳሳች ምክሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው” በማለት ተናግረዋል። አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “የሐሰት መረጃ ዙሪያችንን ከቦናል። ኢንተርኔት መሠረተ ቢስ በሆኑ ወሬዎች ተሞልቷል። በተለያዩ ሰዎችና ቡድኖች ላይ ያነጣጠረ ጥላቻና መድልዎ በጣም ተስፋፍቷል።”

 እርግጥ ነው፣ የተሳሳተ መረጃ መሰራጨት የጀመረው ዛሬ አይደለም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው በዘመናችን “ክፉ ሰዎችና አስመሳዮች እያሳሳቱና እየተሳሳቱ በክፋት ላይ ክፋት እየጨመሩ ይሄዳሉ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1, 13) ደግሞም የኢንተርኔት መስፋፋት የተሳሳቱ ዜናዎችን ከምንጊዜውም ይበልጥ በቀላሉና በፍጥነት ማሰራጨት እንዲቻል አድርጓል። በዚህም የተነሳ ኢሜይላችን፣ ማኅበራዊ ሚዲያችንና በኤሌክትሮኒክ መሣሪያችን የሚደርሰን ዜና በተዛባ ወይም ግማሽ እውነትነት ባለው መረጃ የተሞላ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ሳናስበው እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ልናሰራጭ እንችላለን።

 ታዲያ ከተሳሳቱ መረጃዎች እና መሠረተ ቢስ ከሆኑ ወሬዎች ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ የሚረዱህን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች እንመልከት።

  •   የምታየውን ወይም የምትሰማውን ነገር ሁሉ አትመን

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ተላላ ቃልን ሁሉ ያምናል፤ ብልህ ግን አካሄዱን አንድ በአንድ ያጤናል።”—ምሳሌ 14:15

     ጠንቃቃ ካልሆንን በቀላሉ ልንታለል እንችላለን። በኢንተርኔት ላይ በተለይ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የሚሰራጩትን በላያቸው ላይ መግለጫ የተጻፈባቸው ፎቶግራፎች ወይም አጫጭር ቪዲዮዎች እንደ ምሳሌ እንመልከት። እነዚህ ነገሮች በተለምዶ ሜም ተብለው የሚጠሩ ሲሆን በአብዛኛው ዓላማቸው ሰዎችን ማሳቅ ነው። ሆኖም ፎቶግራፎችና የቪዲዮ ክሊፖች በቀላሉ ለውጥ ሊደረግባቸው ወይም ተዛብተው ሊቀርቡ ብሎም አለቦታቸው ሊጠቀሱ ይችላሉ። ሌላው ቀርቶ በእውነታው ዓለም ያሉ ሰዎች ፈጽሞ ያልተናገሩትን ወይም ያላደረጉትን ነገር እንደተናገሩ ወይም እንዳደረጉ የሚያስመስሉ ቪዲዮዎችን መሥራት ይቻላል።

     “ተመራማሪዎች አብዛኛውን ጊዜ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያጋጥማቸው የተሳሳተ መረጃ፣ ፎቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን በማዛባት ወይም አለቦታቸው በመጥቀስ የሚቀርብ ነው፤ ሜሞችን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል።”—አክሲዮስ ሚዲያ

     ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ይህ መረጃ በእርግጥ ትክክለኛ ዜና ነው ወይስ ሜም?’

  •   የመረጃውን ምንጭ እና ይዘት ገምግም

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “ሁሉንም ነገር መርምሩ።”—1 ተሰሎንቄ 5:21

     አንድን ዘገባ ከማመንህ ወይም ለሌሎች ከማስተላለፍህ በፊት እውነት መሆኑን አረጋግጥ፤ ዘገባው በስፋት የተሰራጨ ወይም ዜና ላይ በተደጋጋሚ የተነገረ ቢሆንም እንኳ እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ ነው። ታዲያ መረጃው እውነት መሆኑን ማረጋገጥ የምትችለው እንዴት ነው?

     የመረጃው ምንጭ አስተማማኝ መሆኑን ገምግም። የዜና ተቋማትና ሌሎች ድርጅቶች ትርፍ ለማግኘት ወይም ፖለቲካዊ አቋማቸውን ለማራመድ ሲሉ አንድን ዘገባ አዛብተው ሊያቀርቡ ይችላሉ። ከአንድ ምንጭ የሰማኸውን ዜና ሌሎች ምንጮች ካወጡት ዜና ጋር አወዳድር። አንዳንድ ጊዜ ጓደኞችህ ባለማወቅ አንድን የተሳሳተ መረጃ በኢሜይል ሊልኩልህ ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ ሊለጥፉ ይችላሉ። ስለዚህ አንድን መረጃ ምንጩን አግኝተህ እስካላረጋገጥክ ድረስ መረጃውን አትመን።

     የመረጃው ይዘት ጊዜ ያላለፈበትና ትክክለኛ መሆኑን አረጋግጥ። እየተነገረ ያለው ነገር ትክክለኛ መሆኑን ለማረጋገጥ ቀኖችን፣ ሊታወቁ የሚችሉ እውነታዎችንና ጠንካራ ማስረጃዎችን ለማግኘት ሞክር። ውስብስብ የሆነ ዘገባ በጣም ቀላል ተደርጎ ከቀረበ ወይም ዘገባው የሰዎችን ስሜት ለመቀስቀስ ታስቦ የተዘጋጀ ከሆነ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልግሃል።

     “በአሁኑ ጊዜ የአንድን መረጃ እውነተኛነት ማረጋገጥ፣ እጅን ከመታጠብ ያልተናነሰ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ ይመስለኛል።”—ስሪዳር ዳርማፑሪ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የምግብ ደህንነትና ጥናት ማዕከል ከፍተኛ ሹም

     ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ይህ የዜና ዘገባ የአንዳንዶችን አመለካከት እንደ ትክክለኛ መረጃ አድርጎ የሚያቀርብ ወይም መረጃውን ከአንድ ወገን ብቻ የሚዘግብ ነው?’

  •   ማመን በምትፈልገው ነገር ሳይሆን በእውነታው ተመራ

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “በገዛ ልቡ የሚታመን ሁሉ ሞኝ ነው።”—ምሳሌ 28:26

     ሁላችንም ብንሆን ማመን የምንፈልገውን ነገር የሚያረጋግጥልንን መረጃ መቀበል ይቀለናል። ደግሞም አብዛኛውን ጊዜ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጪዎች ዜናዎችንና መረጃዎችን የሚልኩልን ትኩረታችንን በሚስቡትና ከዚህ በፊት ኢንተርኔት ላይ በፈለግናቸው ነገሮች ላይ ተመሥርተው ነው። ይሁንና መስማት የምንፈልገው ነገር፣ መስማት ካለብን ነገር የተለየ ሊሆን ይችላል።

     “ሰዎች ምክንያታዊ ሆነው የማሰብ ችሎታ አላቸው፤ ሆኖም የምንመኘው፣ ተስፋ የምናደርገው፣ የምንፈራው ወይም የምንወደው ነገር በአብዛኛው ሚዛን ሊደፋና ማመን የምንፈልገውን ነገር የሚደግፍልንን ነገር ወደመቀበል እንድናዘነብል ሊያደርገን ይችላል።”—ፒተር ዲቶ፣ የማኅበራዊ ሥነ ልቦና ባለሙያ

     ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ይህን መረጃ የምቀበለው ማመን የምፈልገው ነገር ስለሆነ ብቻ ነው?’

  •   የተሳሳተ መረጃ ከማሰራጨት ተቆጠብ

     መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል? “የሐሰት ወሬ አትንዛ።”—ዘፀአት 23:1

     ለሌሎች የምታስተላልፈው መረጃ በአስተሳሰባቸውና በድርጊታቸው ላይ ተጽዕኖ የማሳደር ኃይል እንዳለው አስታውስ። የተሳሳተ መረጃ የተናገርከው ሆን ብለህ ባይሆንም እንኳ ውጤቱ ጎጂ ሊሆን ይችላል።

     “በዚህ ረገድ ልትከተሉት የሚገባው ተቀዳሚው መርሕ አንድን ነገር ለሌሎች ከማስተላለፋችሁ በፊት ቆም ብላችሁ ‘ይህ መረጃ ትክክለኛ ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ?’ ብላችሁ ራሳችሁን መጠየቅ ነው። ሁሉም ሰው እንዲህ ቢያደርግ በኢንተርኔት ላይ የምናየው የተሳሳተ መረጃ ብዛት በእጅጉ ይቀንሳል።”— ፒተር አዳምስ፣ የኒውስ ሊትሬሲ ፕሮጀክት ከፍተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት

     ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘ለሌሎች የማስተላልፈው መረጃ እውነት ስለመሆኑ እርግጠኛ ነኝ?’