የሚያስጨንቁ ነገሮችን መቆጣጠር የሚቻለው እንዴት ነው?
ከልክ በላይ መጨነቅ አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ጉዳት ያስከትላል። እንዲያውም መጀመሪያ ላይ ካስጨነቀህ ችግር የበለጠ ጉዳት ላይ ሊጥልህ ይችላል።
የሚያስጨንቁ ነገሮችን ለመቆጣጠር የሚረዱ ምክሮች
መጥፎ ዜናዎችን አዘውትረህ ከመከታተል ተቆጠብ፦ ስለ መጥፎ ዜናዎች በዝርዝር ማወቅ አያስፈልግህም። መጥፎ ዜናዎችን አዘውትሮ መከታተል ፍርሃትንና ጭንቀትን ከመጨመር ውጪ የሚፈይደው ነገር የለም።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የተደቆሰ መንፈስ . . . ኃይል ያሟጥጣል።”—ምሳሌ 17:22
“አዳዲስና አስደንጋጭ ዜናዎችን አዘውትሮ መከታተል ሱስ ሊሆንብን ይችላል። ሆኖም ይህ ጎጂ ልማድ ነው። ዜናዎችን መከታተሌን ስቀንስ የሚሰማኝ ጭንቀትም የዚያኑ ያህል ቀነሰ።”—ጆን
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ እያንዳንዱን ዜና መከታተል ይኖርብሃል?
ቋሚ ፕሮግራም ይኑርህ። ከእንቅልፍህ የምትነሳበት፣ የምትመገብበት፣ የቤት ውስጥ ሥራዎችን የምታከናውንበትና የምትተኛበት ቋሚ ሰዓት ይኑርህ። በፕሮግራም የምትመራ ከሆነ ሕይወትህ የተረጋጋ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ጭንቀትህን ይቀንሰዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።”—ምሳሌ 21:5
“የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲጀምር፣ ቀደም ሲል በፕሮግራም አከናውናቸው የነበሩ ነገሮችን እርግፍ አድርጌ ተውኩኝ። አብዛኛውን ጊዜዬን የማጠፋው በመዝናኛ ነበር። ጊዜዬን በተሻለ መንገድ መጠቀም እንዳለብኝ ተሰማኝ። ስለዚህ የዕለት ተለት እንቅስቃሴዎቼን የማከናውንበት ፕሮግራም አወጣሁ።”—ጆሴፍ
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ በየዕለቱ የሆነ ነገር እንዳከናወንክ እንዲሰማህ የሚያደርግ ፕሮግራም አለህ?
በጥሩ ነገሮች ላይ አተኩር። ‘እንዲህ ቢሆንስ’ እያሉ መጨነቅና ሊከሰት ስለሚችለው የከፋ ነገር ብቻ ማሰብ ጭንቀትህን ከማባባስ ውጭ የሚፈይደው ነገር የለም። ስለዚህ ስላሉህ ጥሩ ነገሮች ለማሰብ ሞክር።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።”—ቆላስይስ 3:15
“መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቤ መጥፎ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዳላሰላስልና ጥሩ በሆኑ ነገሮች ላይ እንዳተኩር ረድቶኛል። እንደ ቀላል ነገር እናየው ይሆናል። ግን በጣም ጠቃሚ ነው።”—ሊሳ
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ በሕይወትህ ውስጥ ያጋጠሙህን መልካም ነገሮች ትተህ አሉታዊ በሆኑት ላይ ማተኮር ይቀናሃል?
ሌሎችን መርዳት ስለምትችልበት መንገድ አስብ። የሚያስጨንቁ ነገሮች ያጋጠሙት ሰው ራሱን ማግለል ይቀናዋል፤ አንተ ግን እንዲህ ከማድረግ ይልቅ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎችን መርዳት ስለምትችልበት መንገድ አስብ።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵስዩስ 2:4
“ለሌሎች መልካም ነገር ማድረግ ደስታ ይሰጠኛል። እንዲህ ማድረጌ ሌሎች ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል። የእኔም ጭንቀት ይቀንሳል። እንዲያውም በሚያስጨንቁኝ ነገሮች ላይ የማሰላስልበት ጊዜ አይኖረኝም።”—መሪያ
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ከምታውቃቸው ሰዎች መካከል ለየት ያለ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው እነማን ናቸው? እነሱን ለመርዳትስ ምን ማድረግ ትችላለህ?
ጤንነትህን ተንከባከብ። በቂ የአካል ብቃት እንቅስቃሴና እረፍት አድርግ። ለጤና ጠቃሚ የሆኑ ምግቦችን ተመገብ። አካላዊ ጤንነትህን መንከባከብህ በአመለካከትህ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል። ይህም ጭንቀትህን ይቀንሰዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “የአካል ብቃት እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል።”—1 ጢሞቴዎስ 4:8
“እኔና ልጄ እንደ ቀድሞው ውጭ ወጥተን እንቅስቃሴ ማድረግ አንችልም። ስለዚህ ቤት ውስጥ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የምንችልበትን ፕሮግራም አወጣን። ይህም ጥሩ ስሜት እንዲሰማንና እርስ በርስ ያለን ግንኙነት እንዲሻሻል አድርጓል።”—ካተሪን
ሊታሰብበት የሚገባ ነጥብ፦ ጤንነትህ እንዲሻሻል በአመጋገብህና በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ፕሮግራምህ ላይ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብህ ይሰማሃል?
ጭንቀትን ለመቀነስ የሚረዱትን እነዚህ ጠቃሚ ምክሮች ተግባራዊ ከማድረግ በተጨማሪ ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን አስተማማኝ ተስፋዎች መማራቸው ጠቅሟቸዋል። “የአምላክ መንግሥት ምን ነገሮችን ያከናውናል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።