በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ

አምላክ የሚጠይቅህን ነገር ታደርጋለህ?

አምላክ የሚጠይቅህን ነገር ታደርጋለህ?

“የፈለግከውን ጠይቀኝ፤ ምንም ቢሆን አደርግልሃለሁ።” ጨርሶ ለማታውቀው ወይም ከሰላምታ ያለፈ ትውውቅ ለሌለህ ሰው እንዲህ ብለህ እንደማትናገር የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ በጣም ለምትወደው ጓደኛህ እንዲህ ብለህ መናገር ላይከብድህ ይችላል። የሚቀራረቡ ጓደኛሞች አንዳቸው ሌላኛው የጠየቃቸውን ነገር ለመፈጸም ፈቃደኞች ናቸው።

ይሖዋ አገልጋዮቹ የሚያስደስታቸውን ነገር ዘወትር እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ለምሳሌ ያህል፣ ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና የነበረው ንጉሥ ዳዊት “አምላኬ ሆይ፤ አንተ ያደረግኸው ድንቅ ነገር ብዙ ነው፤ ለእኛ ያቀድኸውን፣ ሊዘረዝርልህ የሚችል ማንም የለም፤ ላውራው ልናገረው ብል፣ ስፍር ቍጥር አይኖረውም” ብሏል። (መዝሙር 40:5) ከዚህም በላይ ይሖዋ እሱን ለማያውቁትም ጭምር ‘የተትረፈረፈ ምግብ በማቅረብና ልባቸውን በደስታ በመሙላት’ የሚያስደስታቸውን ነገር ያደርጋል።—የሐዋርያት ሥራ 14:17

የምንወዳቸውና የምናከብራቸው ሰዎች የሚፈልጓቸውን ነገሮች ማድረግ ያስደስተናል

ይሖዋ ሌሎችን የሚያስደስት ነገር ለማድረግ ይፈልጋል፤ በመሆኑም የእሱ ወዳጆች መሆን የሚፈልጉ ሰዎች ‘ልቡን ደስ የሚያሰኙ’ ነገሮችን እንዲያደርጉ መጠበቁ ምክንያታዊ ነው። (ምሳሌ 27:11) ይሁን እንጂ አምላክን ለማስደሰት ምን ማድረግ ትችላለህ? መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ፤ ምክንያቱም አምላክ እንዲህ ባሉት መሥዋዕቶች እጅግ ይደሰታል” በማለት መልስ ይሰጣል። (ዕብራውያን 13:16) ታዲያ ይሖዋን ለማስደሰት መልካም ማድረግና ያለንን ነገር ለሌሎች ማካፈል ብቻውን በቂ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ “ያለ እምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም” በማለት ይናገራል። (ዕብራውያን 11:6) አብርሃም “የይሖዋ ወዳጅ” ተብሎ የተጠራው ‘በይሖዋ ካመነ’ በኋላ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል። (ያዕቆብ 2:23) ኢየሱስ ክርስቶስም የአምላክን በረከት እንድናገኝ ከተፈለገ ‘በአምላክ እንደምናምን በተግባር ማሳየት’ አስፈላጊ መሆኑን ጎላ አድርጎ ገልጿል። (ዮሐንስ 14:1) ታዲያ አምላክ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ከሚመለከታቸው ሰዎች የሚፈልገውን ዓይነት እምነት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረህ ማጥናት ይኖርብሃል። እንዲህ ስታደርግ ስለ አምላክ ፈቃድ “ትክክለኛ እውቀት” ይኖርሃል፤ ይህም ‘ይሖዋን ሙሉ በሙሉ ማስደሰት’ የምትችለው እንዴት እንደሆነ እንድታውቅ ያስችልሃል። ስለ ይሖዋ ያለህ ትክክለኛ እውቀት ሲጨምርና ጽድቅ ስለሆኑት መሥፈርቶቹ ያወቅኸውን ነገር ተግባራዊ ስታደርግ በእሱ ላይ ያለህ እምነት እየጠነከረ ይሄዳል፤ እሱም ይበልጥ ወደ አንተ ይቀርባል።—ቆላስይስ 1:9, 10