ቲምጋድ—የተቀበረው ጥንታዊ ከተማ ሚስጥር ተገለጠ
ደፋሩ አገር አሳሽ ዓይኑን ማመን አቅቶታል። በሰሜናዊ አልጄሪያ በከፊል በአሸዋ የተቀበረ አንድ የሮማውያን የድል ሐውልት እየተመለከተ ነው! ስኮትላንዳዊው ጄምስ ብሩስ በ1765 ይህን ሐውልት ሲያገኝ ከቆመበት ስፍራ በታች አንድ ጥንታዊ ከተማ እንደተቀበረ አላወቀም ነበር፤ በአሁኑ ጊዜ ቲምጋድ ተብሎ የሚጠራው ታሙጋዲ የተባለው ይህ ከተማ በሰሜን አፍሪካ ውስጥ ሮማውያን ከሰፈሩባቸው ከተሞች ሁሉ ትልቁ ነበር።
ይህ ከሆነ ከአንድ መቶ ዓመት የሚበልጥ ጊዜ በኋላ ማለትም በ1881 የፈረንሳይ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኘውን የቲምጋድ ከተማ ቆፍረው ማውጣት ጀመሩ። ባለሙያዎቹ፣ አካባቢው በረሃማና ለኑሮ የማይመች ቢሆንም የከተማው ነዋሪዎች በጣም የተመቻቸና የተንደላቀቀ አኗኗር እንደነበራቸው ደርሰውበታል። ይሁን እንጂ ሮማውያን እንዲህ ባለው ሥፍራ ይህን የመሰለ የበለጸገ ከተማ እንዲገነቡ ያነሳሳቸው ምን ነበር? ደግሞስ ከዚህ ጥንታዊ ከተማና ከነዋሪዎቹ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?
ድብቅ ፖለቲካዊ አጀንዳ
ሮማውያን በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ግዛታቸውን ወደ ሰሜን አፍሪካ ለማስፋፋት በሞከሩበት ወቅት ከአንዳንድ ዘላን ጎሣዎች ኃይለኛ ተቃውሞ አጋጥሟቸው ነበር። ታዲያ ሮማውያን ከአካባቢው ሕዝብ ጋር በሰላም መኖር የቻሉት እንዴት ነው? መጀመሪያ ላይ በሦስተኛው የአውጉስታን ክፍለ ጦር ውስጥ ያሉ ወታደሮች የሰሜናዊ አልጄሪያ ክፍል በሆነው ሰፊ ተራራማ ክልል ውስጥ ብዙ የተመሸጉ ሰፈሮችንና የጥበቃ ማማዎችን ገነቡ። ቆይቶ ደግሞ የቲምጋድን ከተማ የገነቡ ሲሆን ይህን ከተማ የገነቡበት ዓላማ የተለየ ነበር።
ሮማውያን ቲምጋድን የቆረቆሩበት ምክንያት ጡረታ ለወጡ ወታደሮች መኖሪያነት እንደሆነ ቢናገሩም እውነተኛ ምክንያታቸው ግን በአካባቢው ያሉ ጎሣዎችን ተቃውሞ ማለዘብ ነበር። እቅዳቸውም ሰምሮላቸዋል። ምርታቸውን ለመሸጥ ወደ ቲምጋድ የሚመጡት የአካባቢው ነዋሪዎች በከተማው ውስጥ ባለው የቅንጦት አኗኗር መማረክ ጀመሩ። በከተማዋ መኖር የሚፈቀድላቸው የሮም ዜግነት ያላቸው ብቻ ስለነበሩ የአካባቢው ሰዎች ለራሳቸውና ለወንዶች ልጆቻቸው የሮም ዜግነት ለማግኘት ሲሉ ለ25 ዓመታት በሮማውያን ጦር ሠራዊት ውስጥ ለማገልገል ራሳቸውን ያቀርቡ ነበር።
አንዳንዶቹ አፍሪካውያን የሮምን ዜግነት በማግኘት ብቻ አልተወሰኑም፤ ከጊዜ በኋላ በቲምጋድና በሌሎች የቅኝ ግዛት ከተሞች ከፍተኛ ሥልጣን እስከ መያዝ ደርሰው ነበር። ሮማውያን ከአካባቢው ሕዝብ ጋር ለመቀላቀል የወጠኑት ስውር ዘዴ በጣም የሰመረ ከመሆኑ የተነሳ የቲምጋድ ከተማ በተቆረቆረ በሃምሳ ዓመት ውስጥ አብዛኞቹ የከተማው ነዋሪዎች ሰሜን አፍሪካውያን ነበሩ።
ሮማውያን የሕዝቡን ልብ የማረኩት እንዴት ነው?
ሮማውያን የአካባቢውን ሕዝብ ልብ እንዲህ በአጭር ጊዜ መማረክ የቻሉት እንዴት ነው? ሮማዊ የፖለቲካ ሰው የነበረውን የሲሴሮን መርሕ በመከተል በዜጎች መካከል እኩልነት እንዲሰፍን ስላደረጉ ነው። ሮማዊ የሆኑ ጡረተኛ ወታደሮችና አፍሪካዊ ትውልድ ያላቸው ዜጎች የሚያገኙት መሬት እኩል ነበር። ከተማው በሚገባ የተቀየሰ ነበር፤ የመኖሪያ ሕንፃዎቹ የሚሠሩት 20 ሜትር በ20 ሜትር ስፋት ባለው ቦታ ላይ ሲሆን በእነዚህ የመኖሪያ ሕንፃዎች መካከል የሚያልፉ ጠባብ መንገዶች ነበሩ። እንዲህ ያለው እኩል የሆነና በሥርዓት የተዋቀረ አሠራር ለነዋሪዎቹ በጣም ማራኪ እንደነበረ ጥርጥር የለውም።
በብዙዎቹ የሮማውያን ከተሞች ይደረግ እንደነበረው ሁሉ የቲምጋድ ነዋሪዎችም አዳዲስ ዜናዎችን ለመስማት ወይም አንዳንድ ጨዋታዎችን ለመጫወት በገበያ ቀኖች በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ ይገናኙ ነበር። በአቅራቢያው ባሉ በረሃማ ተራራዎች የሚኖሩት የአገሬው ሰዎች በሙቀት ወቅት በከተማዋ ውስጥ ባሉ ዓምዶች ሥር አረፍ ማለት ወይም ከክፍያ ነፃ ወደሆኑት የሕዝብ መታጠቢያዎች ሄደው የሚንዶለዶለውን ውኃ ድምፅ እየሰሙ መዝናናት ይመኙ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ምናልባትም መንፈስ በሚያድሱት የውኃ ፏፏቴዎች ዙሪያ ተቀምጠው ከጓደኞቻቸው ጋር ሲጫወቱ በዓይነ ሕሊናቸው ይታያቸው ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት ቀን ከሌት የሚመኙት ነገር ሳይሆን አይቀርም።
የከተማው የቲያትር ማሳያ ስፍራም የሕዝቡን ልብ በማማለል ረገድ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ከ3,500 በላይ ሰዎችን የመያዝ አቅም ያለው ይህ ክፍት የቲያትር ማሳያ ቦታ ከቲምጋድና ከአጎራባች ከተሞች የመጡ ፈንጠዝያ የሚወዱ ሰዎችን ያስተናግድ ነበር። በመድረክ ላይ የሚቀርቡት ቲያትሮች ሮማውያን የሚወዷቸው ዓይነት ሲሆኑ ተዋናዮቹ አብዛኛውን ጊዜ ዓመፅ ወይም ወሲባዊ ድርጊት ሲፈጽሙ በግልጽ ይታይ ነበር።
የሮማውያን ሃይማኖትም የራሱን ሚና ተጫውቷል። የመታጠቢያ ቤቶቹ ግድግዳዎችና ወለሎች የአረማውያንን አምልኮ በሚያሳዩ በቀለማት ያሸበረቁ የጠጠር ሥዕሎች (ሞዜይክ) ያጌጡ ነበሩ። ነዋሪዎቹ በየዕለቱ ወደ መታጠቢያ ቤቶች ይሄዱ ስለነበር ቀስ በቀስ ከሮማውያን አማልክትና ሃይማኖት ጋር ተለማመዱ። አፍሪካውያኑ የሮማውያንን ባሕል እንዲቀበሉ ለማድረግ የተነደፈው እቅድ በጣም ውጤታማ ስለነበር አብዛኞቹ የመቃብር ሐውልቶች የአካባቢው ሕዝብና ሮማውያን በሚያመልኳቸው ሦስት ጥምር አማልክት ያጌጡ ነበሩ።
ውቡ ከተማ ደብዛው ጠፋ
ንጉሠ ነገሥት ትራጃን ከተማውን በ100 ዓ.ም. ከቆረቆረ በኋላ ሮማውያን በመላው ሰሜን አፍሪካ እህል፣ የወይራ ዘይትና ወይን እንዲመረት ያበረታቱ ነበር። በዚህም የተነሳ በሰሜን አፍሪካ የሚገኘው ይህ ክልል ብዙም ሳይቆይ ለመላው የሮም ግዛት እነዚህን አስፈላጊ ምርቶች ማቅረብ ጀመረ። እንደ ሌሎቹ የቅኝ ግዛት ከተሞች ሁሉ ቲምጋድም በሮማውያን አገዛዝ ወቅት የበለጸገ ከተማ ነበር። ከጊዜ በኋላ የቲምጋድ የሕዝብ ቁጥር በመጨመሩ ነዋሪዎቹ ከከተማው ቅጥር ውጭ መስፈር ጀመሩ።
የከተማው ነዋሪዎችና የመሬት ባለቤቶች ከሮም ጋር በሚደረገው ንግድ በልጽገው የነበረ ቢሆንም የአካባቢው ገበሬዎች ግን ያን ያህል ተጠቃሚ አልነበሩም። በሚደርስባቸው ማኅበራዊ አድልዎና በሚከፍሉት ከመጠን በላይ የሆነ ግብር የተማረሩ አንዳንድ ገበሬዎች በሦስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ዓመፅ አስነስተው ነበር። የካቶሊክን እምነት ከተቀበሉት ገበሬዎች መካከል አንዳንዶቹ ዶናቲስት የተባለውን የሃይማኖት ቡድን ተቀላቀሉ፤ ክርስቲያን እንደሆነ የሚናገረው ይህ ቡድን በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን ሙስና በመቃወም የተነሳ ቡድን ነው።—“ ዶናቲስቶች—‘ንጹሑ ቤተ ክርስቲያን’ አልነበሩም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ከዘለቀ ሃይማኖታዊ ግጭት፣ የእርስ በርስ ጦርነትና የውጭ ወራሪዎች ጥቃት በኋላ የሮም ሥልጣኔ በሰሜን አፍሪካ የነበረው ተቀባይነት እየከሰመ መጣ። በስድስተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የቲምጋድ ከተማ በአካባቢው በሚኖሩ የዓረብ ጎሣዎች ተቃጥሎ የወደመ ሲሆን ከ1,000 ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ደብዛው ጠፍቶ ቆይቷል።
“ሕይወት ማለት እንደዚህ ነው!”
የቲምጋድን ፍርስራሽ ቆፍረው ያወጡ የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች፣ በሕዝብ መሰብሰቢያ ቦታ በተገኘ አንድ ድንጋይ ላይ በላቲን ቋንቋ የተቀረጸው ጽሑፍ አስገርሟቸዋል። ጽሑፉ እንዲህ ይላል፦ “ማደን፣ መታጠብ፣ መጫወት፣ መሣቅ—ሕይወት ማለት እንደዚህ ነው!” አንድ ፈረንሳዊ ታሪክ ጸሐፊ ይህን ጽሑፍ አስመልክተው እንዲህ ብለዋል፦ “ይህ ፍልስፍና ቁም ነገር የሌለው ቢመስልም አንዳንዶች ጥበብ ያዘለ ሚስጥር እንደሆነ አድርገው ይመለከቱት ነበር።”
እርግጥ ነው፣ ሮማውያን ቀደም ሲልም ቢሆን እንዲህ ዓይነት ሕይወት ይመሩ ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ክርስቲያን የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ” የሚል የሕይወት ፍልስፍና ስለነበራቸው ሰዎች ጠቅሷል። ሮማውያን ሃይማኖተኞች የነበሩ ቢሆንም ሕይወታቸው ያተኮረው ተድላንና ጊዜያዊ ደስታን በማግኘት ላይ ነበር፤ ‘የሕይወት ትርጉምና ዓላማ ምንድን ነው?’ የሚለው ጉዳይ ያን ያህል አያሳስባቸውም ነበር። ጳውሎስ “አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል” በማለት የእምነት አጋሮቹ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካላቸው ሰዎች እንዲርቁ አስጠንቅቋል።—1 ቆሮንቶስ 15:32, 33
የቲምጋድ ሕዝቦች የኖሩት ከ1,500 ዓመታት ገደማ በፊት ቢሆንም በዘመናችን ሰዎች ስለ ሕይወት ያላቸው አመለካከት ከእነሱ ብዙም አይለይም። በዛሬው ጊዜም ብዙ ሰዎች የሚፈልጉት ጊዜያዊ ደስታን ማግኘት ብቻ ነው። እነዚህ ሰዎች፣ መዘዙ ምንም ይሁን ምን ሮማውያን ለሕይወት የነበራቸው አመለካከት ጥሩ እንደሆነ ይሰማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን “የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነው” በማለት እውነቱን ግልጽና አጭር በሆነ መንገድ ያስቀምጣል። በመሆኑም ‘በዓለም ሙሉ በሙሉ ከመጠቀም’ እንድንቆጠብ ይመክረናል።—1 ቆሮንቶስ 7:31
ደስተኛና ትርጉም ያለው ሕይወት ለመኖር ሚስጥሩ በሰሜን አፍሪካ በአሸዋ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ተቀብሮ በኖረው ድንጋይ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ ላይ የተገለጸውን ዓይነት ሕይወት መምራት እንዳልሆነ የቲምጋድ ፍርስራሽ ይመሠክራል። ከዚህ ይልቅ እንዲህ ዓይነቱ ሕይወት የሚገኘው “ዓለምም ሆነ ምኞቱ በማለፍ ላይ ናቸው፤ የአምላክን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ማሳሰቢያ በመከተል ነው።—1 ዮሐንስ 2:17