በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | ወደ አምላክ መቅረብ ትችላለህ

አምላክን እንደምትቀርበው ይሰማሃል?

አምላክን እንደምትቀርበው ይሰማሃል?

“ከአምላክ ጋር መቀራረብ የደህንነትና የመረጋጋት ስሜት እንዲያድርብህ ያደርጋል። አምላክ ምንጊዜም አንተን የሚጠቅም ነገር እንደሚያደርግ ይሰማሃል።”—ክሪስቶፈር፣ በጋና የሚኖር ወጣት

“በምታዝንበት ጊዜ አምላክ ይመለከትሃል፤ ከዚያም ከምታስበው የበለጠ ፍቅርና ትኩረት ይሰጥሃል።”—የ13 ዓመቷ ሐና፣ አላስካ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“የአምላክ የቅርብ ወዳጅ እንደሆንክ ማወቅ እጅግ በጣም ልዩና ደስ የሚል ስሜት ይፈጥራል!”—ጂና፣ በ40ዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ ጃማይካዊት ሴት

እንዲህ የሚሰማቸው ክሪስቶፈር፣ ሐናና ጂና ብቻ አይደሉም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ሰዎች አምላክ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ እንደሚመለከታቸው እርግጠኞች ናቸው። አንተስ? ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዳለህ ይሰማሃል? ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ ትፈልጋለህ? ምናልባትም እንዲህ ብለህ ታስብ ይሆናል፦ ‘በእርግጥ አንድ ተራ ሰው ሁሉን ቻይ ከሆነው አምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ይችላል? ከሆነ ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው?’

ወደ አምላክ መቅረብ ይቻላል

መጽሐፍ ቅዱስ፣ እያንዳንዱ ሰው ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት እንደሚችል ይናገራል። አምላክ ዕብራዊ የእምነት አባት የነበረውን አብርሃምን “ወዳጄ” በማለት እንደጠራው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። (ኢሳይያስ 41:8) እንዲሁም በያዕቆብ 4:8 ላይ የሚገኘውን “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” የሚለውን አስደሳች ግብዣ ልብ በል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ወደ አምላክ መቅረብ ማለትም ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ይቻላል። ይሁን እንጂ አምላክ አይታይም፤ ታዲያ ወደ እሱ ‘መቅረብ’ እና ከእሱ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የሚቻለው እንዴት ነው?

ይህን ጥያቄ ለመመለስ፣ ሰዎች ወዳጅነት የሚመሠርቱት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በአብዛኛው መጀመሪያ ላይ ሁለቱም ሰዎች ስማቸውን ይተዋወቃሉ። አዘውትረው የሚነጋገሩ እንዲሁም ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን አንዳቸው ለሌላው የሚያካፍሉ ከሆነ ጓደኝነታቸው ይጠናከራል። አንዳቸው ለሌላው ጥሩ ነገር ሲያደርጉ ደግሞ ወዳጅነታቸው እየጠበቀ ይሄዳል። ከአምላክ ጋር ዝምድና የምንመሠርተውም ተመሳሳይ በሆነ መንገድ ነው። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።