በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የክርስቲያኖች ትምህርት ማኅበረሰቡን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

የክርስቲያኖች ትምህርት ማኅበረሰቡን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

የክርስቲያኖች ትምህርት ማኅበረሰቡን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

እውነተኛ ክርስቲያኖች በፖለቲካ ውስጥ የማይገቡት ለምን እንደሆነ ቀደም ባሉት ርዕሶች ላይ ተመልክተናል። ታዲያ ክርስቲያኖች የሚኖሩበት ማኅበረሰብ እንዲሻሻል ለማድረግ እንደሚፈልጉ የሚያሳዩት እንዴት ነው? ይህን የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን ትእዛዝ በመፈጸም ነው፦ “ሂዱና ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ አስተምሯቸው።”​—ማቴዎስ 28:19, 20

ኢየሱስ፣ ሰዎችን ‘ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ’ ለተከታዮቹ የሰጠውን ትእዛዝ መፈጸም የምድር ጨውና የዓለም ብርሃን እንዲሆኑ የሰጠውን መመሪያ ከመታዘዝ ጋር የተያያዘ ነው። (ማቴዎስ 5:13, 14) እንዴት? ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ በሰዎች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል?

የክርስቶስ መልእክት​ከብክለት ይጠብቃል እንዲሁም ብርሃን ይፈነጥቃል

ጨው ብክለትን የመከላከል ኃይል አለው። በተመሳሳይም ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ለሁሉም ብሔራት እንዲሰብኩ ያዘዛቸው መልእክት ብክለትን የመከላከል ኃይል አለው። የኢየሱስን ትምህርት ተቀብለው ተግባራዊ የሚያደርጉ ሰዎች በዛሬው ጊዜ በዓለም ላይ የተስፋፋው የሥነ ምግባር ውድቀት እንዳይበክላቸው መከላከል ይችላሉ። እንዴት? እንደ ማጨስ ካሉ ጤናን የሚጎዱ ልማዶች እንዴት መራቅ እንደሚችሉ የሚማሩ ከመሆኑም በላይ እንደ ፍቅር፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት እና ጥሩነት የመሳሰሉትን ባሕርያት ያዳብራሉ። (ገላትያ 5:22, 23) እነዚህን ባሕርያት ማዳበራቸው ጠቃሚ የማኅበረሰቡ አባላት እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ከብክለት የሚከላከለውን ይህን መልእክት ለሌሎች የሚያካፍሉ ክርስቲያኖች፣ ለሚኖሩበት ማኅበረሰብ ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ።

ስለ ብርሃን የሚገልጸውን ዘይቤ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? ጨረቃ ከፀሐይ የምታገኘውን ብርሃን እንደምታንጸባርቅ ሁሉ የክርስቶስ ተከታዮችም ከይሖዋ አምላክ የሚመነጨውን “ብርሃን” ያንጸባርቃሉ። ብርሃን በሚፈነጥቀው የሚሰብኩት መልእክትና በሚያከናውኗቸው መልካም ተግባራት አማካኝነት የአምላክን ብርሃን ያንጸባርቃሉ።​—1 ጴጥሮስ 2:12

ኢየሱስ ብርሃን በመሆንና ደቀ መዝሙር በመሆን መካከል ያለውን ተመሳሳይነት ጎላ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ሰዎች መብራት አብርተው እንቅብ አይደፉበትም፤ ከዚህ ይልቅ በመቅረዝ ላይ ያስቀምጡታል፣ በቤት ውስጥ ላሉትም ሁሉ ያበራል። በተመሳሳይም . . . ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ።” በመቅረዝ ላይ የተቀመጠ መብራት በአካባቢው ላሉ ሰዎች ሁሉ በግልጽ ይታያል። በተመሳሳይም እውነተኛ ክርስቲያኖች የሚያከናውኑት የስብከት ሥራም ሆነ መልካም ተግባራቸው በአካባቢያቸው ለሚኖሩ ሰዎች በግልጽ ሊታይ ይገባል። ለምን? ክርስቲያኖች የሚያከናውኑትን መልካም ተግባር ያዩ ሰዎች ለእነሱ ሳይሆን ለአምላክ ክብር እንደሚሰጡ ኢየሱስ ተናግሯል።​—ማቴዎስ 5:14-16

የጋራ ኃላፊነት

ኢየሱስ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” እንዲሁም “ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሎ የተናገረው ለሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ነበር። በተለያዩ ሃይማኖቶች ውስጥ ተበታትነው የሚገኙ ጥቂት ግለሰቦች ኢየሱስ የሰጠውን ይህን ተልእኮ ሊፈጽሙ አይችሉም። ከዚህ ይልቅ “ብርሃን” የሚሆኑት ሁሉም ተከታዮቹ ናቸው። ከ235 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ሰባት ሚሊዮን የይሖዋ ምሥክሮች፣ ክርስቶስ እንዲያውጁ ያዘዛቸውን መልእክት ወደ ሰዎች እየሄዱ የመናገር የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት መልእክት ጭብጥ ምንድን ነው? ኢየሱስ ለተከታዮቹ የስብከት ተልእኮ ሲሰጣቸው ማኅበራዊ ወይም ፖለቲካዊ ለውጥ ስለማምጣት፣ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ጥምረት ስለመፍጠር ወይም ከሃይማኖት ጋር ግንኙነት ስለሌለው ማንኛውም ዓይነት ርዕዮተ ዓለም እንዲሰብኩ አላዘዛቸውም። ከዚህ ይልቅ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:14) በመሆኑም በዛሬው ጊዜ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች የኢየሱስን መመሪያ በመከተል ስለ አምላክ መንግሥት ይኸውም የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት በማጥፋት ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም ማምጣት ስለሚችለው ብቸኛ መንግሥት ለሰዎች ይሰብካሉ።

የወንጌል ዘገባዎችን ስናነብ ኢየሱስ ካከናወነው አገልግሎት ውስጥ ጎላ ብለው የሚታዩ ሁለት ነገሮችን እናገኛለን፤ እነዚህ ነገሮች ዛሬ ያሉ እውነተኛ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ምግባር ሊኖራቸው እንደሚገባ ይጠቁማሉ። የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህን ነጥቦች ያብራራል።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የክርስቲያኖች መልእክት እንደ ጨው የሆነው እንዴት ነው?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የክርስቶስ መልእክት በጨለማ ውስጥ እንደ መብራት የሆነው እንዴት ነው?