በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ . . .

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ይሳተፉ ነበር?

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ይሳተፉ ነበር?

▪ ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት፣ ደቀ መዛሙርቱ አገልግሎታቸውን እንዴት እንደሚያከናውኑ ግልጽ መመሪያዎችን ሰጥቷቸው ነበር፤ ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ምክር ግን አልሰጣቸውም። (ማቴዎስ 28:18-20) በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱ “የቄሳር የሆነውን ነገር ለቄሳር የአምላክ የሆነውን ነገር ደግሞ ለአምላክ መልሳችሁ ስጡ” በማለት አስቀድሞ የሰጣቸውን መመሪያ መከተላቸውን ቀጠሉ።​—ማርቆስ 12:17

ይህ መመሪያ የኢየሱስ ተከታዮች በዓለም ውስጥ እየኖሩም የዓለም ክፍል እንዳይሆኑ የረዳቸው እንዴት ነው? ለመንግሥት ማለትም ለቄሳር መስጠት የሚገባቸውንና ለአምላክ መስጠት የሚገባቸውን ነገር የሚለዩትስ እንዴት ነበር?

ሐዋርያው ጳውሎስ በፖለቲካ ውስጥ መግባት ኢየሱስ ከሰጠው መመሪያ ጋር እንደሚጋጭ ተሰምቶት ነበር። ቢዮንድ ጉድ ኢንቴንሽንስ​ኤ ቢብሊካል ቪው ኦቭ ፖለቲክስ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ጳውሎስ የሮም ዜጋ መሆኑ ያስገኘለትን መብት በመጠቀም የሕግ ከለላ ለማግኘት ጠይቋል፤ በሌላ በኩል ግን በወቅቱ የነበረው መንግሥት ያወጣቸውን ፖሊሲዎች ለማስቀየር ጥረት አላደረገም።”

ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹስ ምን መመሪያ ሰጥቷቸዋል? ከላይ የተጠቀሰው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “እንደ ቆሮንቶስ፣ ኤፌሶንና ሮም ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ ለነበሩ አማኞች የጻፋቸው ደብዳቤዎች ስለ ፖለቲካዊ ውዝግቦች አይጠቅሱም።” ይኸው መጽሐፍ አክሎ እንደሚገልጸው ጳውሎስ “ለመንግሥት መገዛትን ቢያበረታታም ከጻፋቸው በርካታ ደብዳቤዎች ውስጥ በአንዱም ላይ ቢሆን ቤተ ክርስቲያን የፖሊሲ ለውጥ ለማምጣት በመንግሥት ተቋማት ላይ ጫና እንድታሳድር የሚያበረታታ ምንም ዓይነት ሐሳብ አላሰፈረም።”​—ሮም 12:18፤ 13:1, 5-7

ጳውሎስ ከሞተ ከአሥርተ ዓመታት በኋላ የነበሩ ክርስቲያኖችም ለአምላክና ለመንግሥት መስጠት ያለባቸው ነገር እንዲቀላቀል አላደረጉም። ለመንግሥታት አክብሮት የነበራቸው ቢሆንም በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ አልተሳተፉም። ቢዮንድ ጉድ ኢንቴንሽንስ የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የመንግሥት ባለሥልጣናትን የማክበር ግዴታ እንዳለባቸው ቢያምኑም በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ አይገቡም ነበር።”

ይሁንና ክርስቶስ ከሞተ ወደ 300 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ሁኔታዎች ተለወጡ። ቻርልስ ቪላ ቪሴንሲዮ የተባሉት የሃይማኖት ምሁር እንዲህ ብለዋል፦ “በቆስጠንጢኖስ አገዛዝ ወቅት የፖለቲካው ሁኔታ ሲቀየር በርካታ ክርስቲያኖች ሕዝባዊ አገልግሎት መስጠት፣ በውትድርና ውስጥ መግባትና ከፖለቲካ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ማከናወን የጀመሩ ይመስላል።” (ቢትዊን ክራይስት ኤንድ ሲዛር) ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ሃይማኖትንና ፖለቲካን በማዋሃድ የተፈጠረው ሃይማኖት በአራተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. መገባደጃ ላይ በሮም ግዛት ውስጥ የመንግሥት ሃይማኖት ሆነ።

በዛሬው ጊዜ ክርስቶስን እንከተላለን የሚሉ በርካታ ሃይማኖቶች አባሎቻቸው በፖለቲካ ውስጥ እንዲገቡ ያበረታታሉ። ሆኖም እነዚህ ሃይማኖቶች ክርስቶስም ሆነ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች የተዉትን ምሳሌ እየተከተሉ አይደለም።