ድህነትን ለማስወገድ የተደረጉ ጥረቶች
ድህነትን ለማስወገድ የተደረጉ ጥረቶች
ሀብታሞች ድህነትን አስወግደዋል፤ እርግጥ ያስወገዱት የራሳቸውን ድህነት ብቻ ነው። ይሁን እንጂ የሰውን ዘር በጠቅላላ ከድህነት አረንቋ ለማውጣት የተደረጉት ጥረቶች በሙሉ ያለ ውጤት ቀርተዋል። ለምን? ምክንያቱም በጥቅሉ ሲታይ ሀብታሞች ማንም ሰው ወይም ምንም ነገር ምቾታቸውንና ጥቅማቸውን እንዲነካባቸው አይፈልጉም። የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ የነበረው ሰለሞን “የተገፉትን ሰዎች እንባ ተመለከትሁ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ ኀይል በሚገፏቸው ሰዎች እጅ ነበረ” በማለት ጽፏል።—መክብብ 4:1
ታዲያ ተደማጭነትና ሥልጣን ያላቸው ሰዎች ከዓለም ላይ ድህነትን ለማስወገድ የሚያስችል ለውጥ በኅብረተሰቡ ውስጥ መፍጠር ይችላሉ? ሰለሞን በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ “ሁሉም ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው። የተጣመመው ሊቃና አይችልም” በማለት ጽፏል። (መክብብ 1:14, 15) በዘመናችን ድህነትን ለማስወገድ የተደረጉትን አንዳንድ ጥረቶች መመልከት ሰለሞን የጻፈው ሐሳብ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
ለሰው ሁሉ ብልጽግናን ለማጎናጸፍ የተፀነሱ ንድፈ ሐሳቦች
በ19ኛው መቶ ዘመን የንግዱና የኢንዱስትሪው ዘርፍ ጥቂት አገራት ከፍተኛ ሀብት እንዲያከማቹ አስችሏቸው ነበር፤ በዚህ ወቅት ተደማጭነት ያላቸው አንዳንድ ሰዎች ስለ ድህነት በቁም ነገር ማሰብ ጀመሩ። ታዲያ ሁሉም ሰው የምድርን ሀብት ከበፊቱ በተሻለ በእኩል ደረጃ መጠቀም ይችል ይሆን?
አንዳንዶች ሶሻሊዝም ወይም ኮሚኒዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሀብት በእኩል መጠን የሚከፋፈልበት ከመደብ ልዩነት ነፃ የሆነ ኅብረተሰብ ለመገንባት እንደሚያስችል አስበው ነበር። እርግጥ ነው፣ በወቅቱ ይህ ሐሳብ ሀብታሞችን እንቅልፍ ነስቷቸው ነበር። እንደዛም ሆኖ “እያንዳንዱ ሰው የሚችለውን ያህል ይስጥ፤ የሚያስፈልገውን ያህል ይውሰድ” የሚለው መፈክር የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር። ብዙ ሰዎች ሁሉም አገራት የሶሻሊዝምን ርዕዮተ ዓለም እንደሚቀበሉና ዓለማችንም “ገነት” እንደምትሆን ተስፋ አድርገው ነበር። አንዳንድ የበለጸጉ አገራት ሶሻሊዝምን በከፊል በመቀበል ለዜጎቻቸው መሠረታዊ ነገሮችን በነፃ ማዳረስ የሚቻልበትን ሥርዓት ዘርግተው ነበር፤ ይህም የዜጎቻቸውን ፍላጎት “ከልደት እስከ ሕልፈት” ለማሟላት እንደሚያስችላቸው ተሰምቷቸው ነበር። እነዚህ አገራት በሕዝባቸው ዘንድ የነበረውን ለሕይወት አስጊ የሆነ ድህነት እንዳስወገዱ ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ሶሻሊዝም እንደታሰበው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ኅብረተሰብ መፍጠር አልቻለም። ዜጎች ከራሳቸው መክብብ 7:20, 29
ጥቅም ይልቅ ለማኅበረሰቡ ጥቅም ይቆማሉ የሚለው እቅዳቸውም መና ሆኖ ቀረ። አንዳንድ ሰዎች ለድሆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደ ልብ ማቅረብ የአንዳንዶችን የሥራ ተነሳሽነት እንዳጠፋው ስላስተዋሉ ለድሆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማቅረቡ ጉዳይ አበሳጭቷቸዋል። በመሆኑም ‘ትክክለኛውን ነገር የሚያደርግና ፈጽሞ ኃጢአት የማይሠራ፣ ጻድቅ ሰው በምድር ላይ የለም። አምላክ ሰውን ቅን አድርጎ ሠርቶታል፤ ሰዎች ግን ውስብስብ ዘዴ ቀየሱ’ የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እውነት መሆኑ ተረጋግጧል።—ተስፋ ተደርጎበት የነበረው ሌላው ጽንሰ ሐሳብ ደግሞ የአሜሪካ ሕልም (ዚ አሜሪካን ድሪም) በመባል የሚጠራው ነው፤ ሰዎች ይህን ጽንሰ ሐሳብ ያፈለቁት ጠንክሮ ለመሥራት ፈቃደኛ የሆነ ሁሉ ባለጸጋ የሚሆንበትን ዓለም ለመፍጠር አልመው ነው። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ አገራት ዩናይትድ ስቴትስን ባለጸጋ እንዳደረጓት የሚታሰቡትን የአሠራር ደንቦች ይኸውም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትና ነፃ ገበያ ማራመድን የመሳሰሉ መርሆዎች ተቀበሉ። ይሁን እንጂ የሰሜን አሜሪካ ሀብት የተገኘው አገሪቱ በምትከተለው የፖለቲካ ሥርዓት ብቻ ባለመሆኑ “የአሜሪካ ሕልም” የተባለውን ጽንሰ ሐሳብ በመኮረጅ መበልጸግ የቻሉት ሁሉም አገራት አይደሉም። አሜሪካ ተዝቆ የማያልቅ የተፈጥሮ ሀብት ያላት እንዲሁም ዓለም አቀፍ የንግድ መስመሮችን ለመዘርጋት ምቹ መሆኗ አገሪቱ እንድትበለጽግ ካስቻሏት ምክንያቶች መካከል በዋነኝነት የሚጠቀሱ ናቸው። በተጨማሪም በውድድር የሚመራው የዓለም የኢኮኖሚ ሥርዓት፣ አሸናፊ የሆኑ ሰዎች በሀብት መሰላል ላይ እንዲወጡ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ከጨዋታው ውጪ የሆኑ ሰዎች ለሥቃይ እንዲዳረጉም ምክንያት ሆኗል። ታዲያ የበለጸጉ አገራት ከድህነት ቀንበር ያልተላቀቁትን ለመርዳት ይነሳሱ ይሆን?
የማርሻል እቅድ—ድህነትን ለማስወገድ ይረዳ ይሆን?
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአውሮፓ አገራት ክፉኛ ከመጎዳታቸውም በላይ አብዛኞቹ ሰዎች ለረሃብ እንጋለጣለን የሚል ስጋት አድሮባቸው ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሶሻሊዝም በአውሮፓ ሰፊ ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ አሳስቦት ነበር። በመሆኑም የአሜሪካ መንግሥት የእሱን መርሆዎቹ በሚቀበሉ የአውሮፓ አገራት ውስጥ የኢንዱስትሪውንና የግብርናውን መስክ መልሶ ለማቋቋም ለአራት ዓመታት ያህል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ሰጠ። የማርሻል እቅድ በመባል የሚታወቀው ይህ አውሮፓን መልሶ የማቋቋም ፕሮግራም ስኬታማ እንደሆነ ብዙዎች ይሰማቸዋል። ዩናይትድ ስቴትስ በምዕራብ አውሮፓ ላይ የምታሳድረው ተጽዕኖ እየጨመረ በመምጣቱ በእነዚህ አገራት ውስጥ የተከሰተው ለሕይወት አስጊ የሆነ ድህነት ቀስ በቀስ እየተወገደ መጣ። ታዲያ ይህ ዘዴ ድህነትን ከምድረ ገጽ ለማስወገድ አስችሏል?
የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የማርሻል እቅድ ስኬታማ መሆኑን ሲመለከት በመላው ዓለም የሚገኙ ድሃ አገራት በእርሻ፣ በጤና፣ በትምህርትና በትራንስፖርት ዘርፍ እድገት እንዲያደርጉ እርዳታ መስጠት ጀመረ። ዩናይትድ ስቴትስ ራሷ በግልጽ እንደምትናገረው ይህን እርዳታ የምትሰጠው የራሷን ጥቅም ለማስጠበቅ ብላ ነው። ሌሎች አገራትም እርዳታ በመስጠት በብዙ አገራት ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር ሞክረዋል። ከስልሳ ዓመታት በኋላ የተደረገው ግምገማ እንደሚያሳየው ለማርሻል እቅድ ከወጣው በብዙ እጥፍ የሚበልጥ መዋዕለ ንዋይ ቢፈስም የሚፈለገው ውጤት አልተገኘም። እውነት ነው፣ ቀደም ሲል ድሃ የነበሩ በተለይም በምሥራቅ እስያ የሚገኙ አንዳንድ አገራት በጣም ሀብታም መሆን ችለዋል። በሌሎች አገራት ግን የውጭ እርዳታ፣ የሕፃናት ሞት በጣም እንዲቀንስና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ልጆች የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ ያስቻለ ቢሆንም አብዛኞቹ አሁንም ቢሆን የሚገኙት በአስከፊ ድህነት ውስጥ ነው።
የውጭ እርዳታ ድህነትን ማስወገድ ያልቻለው ለምንድን ነው?
ድሃ አገራትን ከድህነት እንዲወጡ ከመርዳት ይልቅ የበለጸጉ አገራትን ጦርነት ካስከተለው ጉዳት እንዲያገግሙ መርዳት የበለጠ ቀላል ሆኖ ተገኝቷል። የአውሮፓ አገራት ቀደም ብሎም በኢንዱስትሪው፣ በንግዱና በመጓጓዣው ዘርፍ በደንብ የተደራጁ ነበሩ። የሚያስፈልገው ኢኮኖሚያቸው እንዲያንሰራራ ማድረግ ብቻ ነው። በሌላ በኩል ግን ድሃ አገራት በውጭ እርዳታ አማካኝነት መንገዶችን ቢሠሩም እንዲሁም ትምህርት ቤቶችንና ክሊኒኮችን ቢገነቡም አገራቱ የተፈጥሮ ሀብት፣ ጥሩ የሆነ የንግድ ሥርዓት ብሎም ምቹ የሆነ የንግድ መስመር ስለሌላቸው ሕዝቦቻቸው እስከ አሁን ድረስ በአስከፊ ድህነት ውስጥ ይገኛሉ።
ድህነት የሚወልዳቸው ችግሮች መልሰው ለድህነት መንስኤ ስለሚሆኑ ችግሮቹ በጣም የተወሳሰቡ ናቸው፤ እንዲሁም ከዚህ እሽክርክሪት መውጣት ቀላል አይደለም። ለምሳሌ በሽታ ለድህነት መንስኤ ሊሆን፣ ድህነት ደግሞ ለበሽታ መንስኤ ሊሆን ይችላል። በምግብ እጥረት የተጎዱ ሕፃናት አካላዊና አእምሯዊ እድገታቸው ስለሚቀጭጭ ሲያድጉ የራሳቸውን ልጆች መንከባከብ የማይችሉ ይሆናሉ። በተጨማሪም የበለጸጉ አገራት የተረፋቸውን ምግብ በእርዳታ ስም ወደ ድሃ አገራት ወስደው ሲያራግፉ የአገሬው ገበሬና የችርቻሮ ነጋዴ ኪሳራ ላይ ይወድቃሉ፤ ይህም ድህነትን ያባብሳል። ለድሃ አገራት ገንዘብ መለገስም ቢሆን ሌላ እሽክርክሪት ሊፈጥር ይችላል፤ ይኸውም በእርዳታ የተገኘ ገንዘብ ለስርቆት የተጋለጠ በመሆኑ ሙስናን ይፈጥራል፤ ሙስና ደግሞ አንድ አገር ይበልጥ በድህነት ውስጥ እንዲዘፈቅ ያደርጋል። የውጭ እርዳታ የታለመለትን ዒላማ የማይመታበት ዋነኛ ምክንያት የድህነት መንስኤ የሆነውን ነገር ስለማያጠፋ ነው።
የድህነት መንስኤ
ለአስከፊ ድህነት መንስኤው አገራት፣ መንግሥታትና ግለሰቦች የራሳቸውን ጥቅም ብቻ ለማራመድና ለማስጠበቅ መሯሯጣቸው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በበለጸጉ አገራት መሪዎች የሚመረጡት በዲሞክራሲያዊ መንገድ ስለሆነና መሪዎቹም የመረጣቸውን ሕዝብ ፍላጎት የማሟላት ግዴታ ስላለባቸው ድህነትን ከዓለም ላይ ለማስወገድ ቅድሚያ ሰጥተው አይንቀሳቀሱም። ከዚህ ይልቅ በአገራቸው ያሉ ገበሬዎች ለኪሳራ እንዳይዳረጉ ለመከላከል ሲሉ በድሃ አገራት ያሉ ገበሬዎች ምርታቸውን በበለጸጉ አገራት እንዳይሸጡ ይከለክላሉ። ከዚህም በላይ በበለጸጉ አገራት የሚገኙ ገበሬዎች ምርታቸውን በድሃ አገራት ውስጥ ካሉት ገበሬዎች ባነሰ ዋጋ በማቅረብ ተወዳዳሪ ሆነው መቀጠል እንዲችሉ መንግሥት ከፍተኛ ድጎማ ያደርግላቸዋል።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ለድህነት መንስኤው ሕዝቦችና መንግሥታት የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ የመሯሯጥ ዝንባሌ ያላቸው መሆኑ ነው፤ በሌላ አባባል ችግሩን የሚፈጥሩት ሰዎች ራሳቸው ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስን ከጻፉት ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ሰለሞን ጉዳዩን እንዲህ በማለት ገልጾታል፦ “ሰው ሰውን ለመጕዳት ገዥ የሚሆንበት ጊዜ አለ።”—መክብብ 8:9
ታዲያ ድህነት ሊወገድ አይችልም ማለት ነው? የሰዎችን ባሕርይ መለወጥ የሚችል መንግሥትስ ይኖራል?
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ድህነትን ለመከላከል የሚረዳ ሕግ
ይሖዋ አምላክ ለጥንቶቹ እስራኤላውያን ቢታዘዟቸው ኖሮ ብዙ ሰዎች ድህነት ውስጥ እንዳይገቡ መታደግ የሚችሉ ሕግጋትን ሰጥቷቸው ነበር። በሕጉ መሠረት፣ ካህን በመሆን ከሚያገለግለው የሌዊ ነገድ በስተቀር እያንዳንዱ ቤተሰብ ርስት ተሰጥቶት ነበር። መሬት ለዘለቄታው ስለማይሸጥ የቤተሰቡ ርስት አስተማማኝ ነበር። በሌላ ሰው እጅ የሚገኝ መሬት በሙሉ በየ50 ዓመቱ ለባለቤቱ ወይም ለቤተሰቡ ይመለስ ነበር። (ዘሌዋውያን 25:10, 23) ማንም ሰው በሕመም ወይም በአደጋ ሳቢያ አሊያም በስንፍና መሬቱን ለመሸጥ ቢገደድ በኢዮቤልዩ ዓመት ላይ ክፍያ ሳይጠየቅ ይመለስለት ነበር። ይህ ሕግ ቤተሰቦች ከትውልድ ወደ ትውልድ በሚተላለፍ የድህነት ማጥ ውስጥ ከመዘፈቅ እንዲድኑ ይረዳቸው ነበር።
በአምላክ ሕግ ውስጥ የተካተተው ምሕረት የሚንጸባረቅበት ሌላው ዝግጅት ደግሞ ችግር ላይ የወደቀ ሰው ራሱን ለባርነት መሸጥ መቻሉ ነው። ዕዳውን መክፈል እንዲችል ራሱን የሸጠበትን ዋጋ በቅድሚያ ይቀበል ነበር። እስከ ሰባተኛው ዓመት ድረስ ራሱን መዋጀት ካልቻለ በዚህ ዓመት ላይ ነፃ እንዲወጣ ይደረጋል እንዲሁም የግብርና ሥራውን እንደገና እንዲጀምር ለመቋቋሚያ የሚሆን ዘርና ከብት ይሰጠው ነበር። በተጨማሪም ድሃ የሆነ አንድ እስራኤላዊ ገንዘብ መበደር ቢያስፈልገው ወገኖቹ በወለድ እንዳያበድሩት ሕጉ ይከለክል ነበር። ከዚህም በላይ በአጨዳ ወቅት ድሆች መቃረም እንዲችሉ ሕዝቡ የእርሻቸውን ዳር ዳር ሳያጭዱ እንዲያስተርፉላቸው ሕጉ ያዝዝ ነበር። በመሆኑም ማንኛውም እስራኤላዊ ለልመና አይጋለጥም ነበር።—ዘዳግም 15:1-14፤ ዘሌዋውያን 23:22
ይሁን እንጂ ታሪክ እንደሚያሳየው አንዳንድ እስራኤላውያን ለድህነት ተዳርገው ነበር። ይህ ሁኔታ የተከሰተው ለምንድን ነው? እስራኤላውያን የይሖዋን ሕግ ባለመታዘዛቸው ነው። በዚህም የተነሳ በአብዛኞቹ አገራት እንደነበረው አንዳንዶች የመሬት ከበርቴዎች ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ መሬታቸውን በማጣት ለድህነት ተዳረጉ። በመሆኑም በእስራኤላውያን ዘንድ ድህነት ሊከሰት የቻለው አንዳንድ ግለሰቦች የአምላክን ሕግ ችላ በማለታቸውና ከሌሎች ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም ማስቀደም በመጀመራቸው ነው።—ማቴዎስ 22:37-40