በተሽከርካሪ እየዞርኩ ለመኖር የነበረኝ ምኞት
በተሽከርካሪ እየዞርኩ ለመኖር የነበረኝ ምኞት
ዞያ ዲሚትሮቫ እንደተናገረችው
በ15 ዓመቴ፣ ስመኘው የነበረው ነገር እውን ሆኖልኝ በደስታ የሰርከስ ትርኢት እያሳየሁ ከቡድኑ ጋር ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወር ጀመርኩ። ከዚያም መስከረም 4, 1970 አሳዛኝ አደጋ ደረሰብኝ። ለቅጽበት ማራኪ በሆነ ሁኔታ አየር ላይ ከተንሳፈፍኩ በኋላ ድንገት ተምዘግዝጌ መሬት ላይ ተፈጠፈጥኩ።
የተወለድኩት ታኅሣሥ 16, 1952 ሲሆን ከወላጆቼና ከአንዲት እህቴ ጋር በቡልጋሪያ፣ ሶፊያ ከተማ ውስጥ እኖር ነበር። በዚያን ጊዜ ቡልጋሪያ ኮሚኒስት አገር ነበረች፤ በወቅቱ ሃይማኖት ሙሉ በሙሉ የተወገዘ ባይሆንም የሚደገፍ ነገር አልነበረም። አብዛኛው ሕዝብ በአምላክ አያምንም ነበር፤ የሚያምኑትም ቢሆኑ ብዙዎቹ እምነታቸውን በድብቅ መያዝ ይመርጡ ነበር። ቤተሰቦቼ ለስሙ ኦርቶዶክስ ቢሆኑም ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ትምህርት ስላላስተማሩኝ ስለ አምላክ አስቤ አላውቅም።
ገና ከትንሽነቴ ጀምሮ ለሁሉም ዓይነት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች፣ በተለይም ለጂምናስቲክ ስፖርት ከፍተኛ ፍቅር እንደነበረኝ በግልጽ ይታይ ነበር። የ13 ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ ሰው ለሰርከስ የምትሠለጥን ልጅ ሊፈልግ ወደ ትምህርት ቤታችን መጣ። የጂምናስቲክ አስተማሪዬ እኔ ለዚህ ተስማሚ እንደምሆን ሐሳብ አቀረበ። እኔም ለቃለ መጠይቅና ለሙከራ ውድድር፣ በሥራ አስኪያጁ የአሜሪካ መኪና ወደ አንድ የአሠልጣኞች ቡድን በመሄዴ በጣም ተደሰትኩ። ፈተናውን አልፌ በመመረጤ በጣም ደስ አለኝ። በዚህ ሁኔታ ከሁለት ዓመት በላይ የሚፈጀውን ኃይለኛ ሥልጠናና ልምምድ ተያያዝኩት። ከዚያም 15 ዓመት ሲሆነኝ ሥልጠናዬን ጨርሼ በተሽከርካሪ እየዞርኩ መኖር ማለትም ከሰርከስ ቡድኑ ጋር ከቦታ ቦታ መዘዋወር ጀመርኩ። መጀመሪያ ላይ በመላዋ ቡልጋሪያ የዞርኩ ሲሆን ከዚያ በኋላ ደግሞ የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት አካል ወደነበሩት አገሮች፣ አልፎ ተርፎም ወደ ሀንጋሪ፣ አልጄሪያና የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ ተጉዣለሁ።
ለሦስት አስደሳች ዓመታት ያህል ምኞቴ ተሳክቶልኝ በደስታ ኖርኩ። ከዚያ በኋላ በቲቶቭ ቬለስ፣ መቄዶንያ የሰርከስ ትርኢት እያሳየሁ ሳለሁ በመግቢያዬ ላይ የገለጽኩት አደጋ ደረሰብኝ። በወቅቱ ከተሰበሰበው ሕዝብ በላይ እየተገለባበጥኩ የአክሮባት ትርኢት በማሳየት ላይ ነበርኩ። ተዘቅዝቆ የተንጠለጠለው አብሮኝ ትርዒቱን የሚያሳየው ሰው ወደ ላይ ከወረወረኝ በኋላ ተመልሼ ስወርድ በእጁ ይቀልበኛል። በዚህ ጊዜ ግን እጆቹን የሳትኩኝ ከመሆኑም ሌላ ያሠርኩት የአደጋ መከላከያ ገመድ በመበጠሱ ቁልቁል 6 ሜትር ተምዘግዝጌ ተፈጠፈጥኩ። ከዚያም ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ተወሰድኩኝ፤ እዚያም አንድ እጄና አከርካሪዬ እንዲሁም በርካታ የጎድን አጥንቶቼ እንደተሰበሩ በምርመራ ተረጋገጠ። ለጥቂት ቀናት ራሴን ስቼ የቆየሁ ሲሆን ምን እንደደረሰብኝ እንኳ አላውቅም ነበር። በተወሰነ መጠን ካገገምኩ በኋላ ከወገቤ በታች ሽባ እንደሆንኩ ተገነዘብኩ። ይሁን እንጂ ገና ወጣት እንደመሆኔ መጠን በእሽት ወይም በቀዶ ሕክምና አማካኝነት እንደገና በእግሬ መሄድ እችላለሁ፣ ምናልባትም የሰርከስ ትርኢት ወደ ማሳየት እመለሳለሁ የሚል ብሩሕ ተስፋ ነበረኝ።
ከዚያም ለሁለት ዓመት ተኩል ያህል በተለያዩ ተቋማት የሕክምና ክትትል ሲደረግልኝ ቆየሁ፤ በዚህ ጊዜ ሁሉ እድናለሁ የሚል ከፍተኛ ተስፋ ነበረኝ። በመጨረሻ ግን
ምኞቴ ማክተሙን መቀበል ግድ ሆነብኝ። የሚገርመው ነገር ቀድሞ የነበረኝ “በተሽከርካሪ እየዞርኩ የመኖር ምኞቴ” አክትሞ ፈጽሞ ባላሰብኩት ሁኔታ በተሽከርካሪ ወንበር እየተንቀሳቀሱ መኖርን መላመድ ነበረብኝ።አዲስ ሕይወት ጀመርኩ
እንደዚያ እንደ ልቤ እንቀሳቀስ የነበርኩ ሰው አሁን እንዲህ ተሳስሮ መቀመጡን የምለምደው አልመሰለኝም ነበር። ተስፋዬ ሙሉ በሙሉ ስለተሟጠጠ በመንፈስ ጭንቀት ተዋጥኩ። ከዚያም በ1977 ስቶያን የተባለ አንድ ወጣት ወደ ቤቴ መጣ። ይህ ወጣት የቀድሞ የሥራ ባልደረባዬ ወንድም መሆኑን ሳውቅ ወዲያው ወደ ቤት እንዲገባ ጋበዝኩት። በጭውውታችን መሃል ወደ ቀድሞው ጤንነቴ የመመለስ ተስፋ እንዳለኝና እንደሌለኝ ጠየቀኝ። እኔም በሕይወቴ ግራ ተጋብቼና ቅስሜ ተሰብሮ ስለነበር ምንም ተስፋ እንደሌለኝ ነገርኩት። እሱም ሊረዳኝ የሚችለው አምላክ ብቻ መሆኑን ሲነግረኝ “ታዲያ አምላክ ካለ እንዲህ ያለ ሁኔታ የደረሰብኝ ለምንድን ነው?” ስል በምሬት መለስኩለት።
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሰርከስ ትርዒት ያሳይ የነበረውና በቅርቡ የይሖዋ ምሥክር የሆነው ስቶያን በዚህ መግቢያ ተጠቅሞ መጽሐፍ ቅዱስ የወደፊቱን ጊዜ በተመለከተ ስለያዛቸው አስደናቂ ተስፋዎች ደግነት በተሞላበት መንገድ ገለጸልኝ። እኔም በቅርቡ ምድር ገነት እንደምትሆን ሳውቅ እጅግ ደስ አለኝ። “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” የሚለው ተስፋ ልቤን ነካው። (ራእይ 21:4) አካላዊ ጤንነቴን መልሼ ለማግኘት ከፍተኛ ጉጉት አደረብኝ! ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱስን በቋሚነት ለማጥናት ተስማማሁ። በዚህ መንገድ አዲስ ሕይወት መኖር ጀመርኩ። በቃ፣ ለእውነተኛ ተስፋ መሠረት የሆነውን ነገር አገኘሁ!
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን በየሳምንቱ በጉጉት እጠባበቅ ነበር። መጀመሪያ ላይ ከስቶያን ጋር ሳጠና ከቆየሁ በኋላ በጣም ደግ ከሆነች ቶትካ ከምትባል እህት ጋር ጥናቴን ቀጠልኩ። እሷ ባደረገችልኝ እርዳታ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ያለኝ እውቀት በፍጥነት እያደገ ሄደ፤ ከዚያም ሕይወቴን ለይሖዋ አምላክ ወሰንኩ። በዚያን ጊዜ በሶፊያ ለማጥመቅ ብቃት ያለው ሰው ስላልነበረ አንድ ወንድም ከመቄዶንያ ሊጎበኘን እስኪመጣ መጠበቅ ነበረብኝ። መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከጀመርኩ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ መስከረም 11, 1978 በመኖሪያ አፓርታማዬ ባለው መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ ተጠመቅኩ። የይሖዋ ምሥክር ሆኜ መጠመቄ ታላቅ ደስታ ያመጣልኝ ሲሆን ሕይወቴም እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው አድርጓል።
የተማርኩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በውስጤ እንደ እሳት ይነድ ነበር። ስለዚህ የተማርኩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ወደ ቤቴ ለመጣው ሰው ሁሉ በቅንዓት እናገር ነበር። የሚያሳዝነው ነገር፣ የደረሰብኝ አደጋ ካስከተለብኝ የጤና ቀውስ ሙሉ በሙሉ እንዳልዳንኩ በማሰብ ሊሆን ይችላል፣ ማንም የምናገረውን ከቁም ነገር አልቆጠረውም።
አሳዛኝ ስህተት
በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች በቡልጋሪያ በእገዳ ሥር ስለነበሩ በመላው አገሪቱ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ጥቂት ነበሩ። እኔ ልካፈልበት የምችል የጉባኤ ስብሰባ
ካለመኖሩም በላይ ከእምነት አጋሮቼ ጋር የምገናኝበት አጋጣሚ በጣም ውስን ነበር። ከዚህም በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት ከማይመሩ ሰዎች ጋር መቀራረብ የሚያስከትለውን አደጋ አለማስተዋሌ አሳዛኝ ስህተት ወደ መፈጸም አመራኝ።ሕሊናዬ እረፍት ነሳኝ፤ እንዲሁም ከይሖዋ አምላክ መራቅ ምን ያህል ከባድ ሥቃይ እንደሚያስከትል በሕይወቴ አየሁ። መንፈሴ ተደቁሶና በኀፍረት ተውጬ ለይሖዋ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ምሕረት እንዲያደርግልኝ ለመንኩት። በኋላም አፍቃሪ የሆኑ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ባደረጉልኝ እርዳታ በመንፈሳዊ አገገምኩ፤ ይሖዋን በማገልገል የማገኘውም ደስታ ተመለሰልኝ። ይሖዋን በንጹሕ ሕሊና የማምለክንና ከንጹሕ ድርጅቱ ጋር አብሮ የመኖርን መብት እጅግ ከፍ አድርጌ እመለከታለሁ!
የአቅም ገደብ ቢኖርብኝም ደስተኛ ነኝ
ከ40 ዓመት በፊት የደረሰብኝ አደጋ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር የሰርከስ ትርኢት እያሳየሁ የመኖር ሕልሜን አጨልሞት በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ተወስኜ እንድቀር አድርጎኛል። ሆኖም ሕይወቴ ከንቱ ሆኖ የቀረ ይመስል ያለፈውን ጊዜ በሐዘንና በቁጭት አልመለከትም። የተማርኩት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት፣ የሰርከስ ትርዒት በማሳየት በሕይወቴ ላገኝ አስበው የነበረው ደስታና እርካታ ዘላቂ ዋጋ በሌላቸው ነገሮች ላይ የተመሠረተ መሆኑን እንድገነዘብ ረድቶኛል። በሰርከስ ትርዒት ሙያቸው የገፉበት የቀድሞ የሥራ ባልደረቦቼ በሕይወታቸው ተስፋ ቆርጠው አይቻለሁ። እኔ ግን እንደ ውድ ሀብት የሚቆጠር ከፈጣሪዬ ከይሖዋ አምላክ ጋር የግል ዝምድና የመመሥረት ልዩ መብት አግኝቻለሁ። ይህም በሰርከስ ሕይወት ብቀጥል ኖሮ ላገኘው የማልችለውን ከፍተኛ ደስታ አምጥቶልኛል።
በተጨማሪም ሌሎች ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት አግኝተው ለአፍቃሪው አምላካችን ለይሖዋ ሕይወታቸውን ሲወስኑ በማየት ደስታ አግኝቻለሁ። በ1977 መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመርኩበት ጊዜ በቡልጋሪያ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች እፍኝ አይሞሉም ነበር። የኮሚኒዝም አገዛዝ ወድቆ የይሖዋ ምሥክሮች እውቅና አግኝተው ለመጀመሪያ ጊዜ እስከተመዘገቡበት እስከ 1991 ድረስ እንኳ በመላው አገሪቱ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር ከመቶ አይበልጥም ነበር። የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ያለማቋረጥ አድጎ በአሁኑ ጊዜ 1,800 ገደማ ደርሶ ማየቴ እጅግ ያስደስተኛል!
በቡልጋሪያ ገና ብዙ የሚሠራ ሥራ አለ። ብዙዎች በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውቀት ማግኘት ይፈልጋሉ። በ2010 በተከበረው የኢየሱስ ሞት መታሰቢያ ላይ ኢሳይያስ 60:22 (የ1954 ትርጉም) ላይ በትንቢት በተነገረው መሠረት ‘ታናሽ’ የሆነው አድጎ “ብርቱ ሕዝብ” ሲሆን በገዛ ዓይኔ አይቻለሁ።
3,914 የሚያህል ከፍተኛ የተሰብሳቢዎች ቁጥር መገኘቱ ይህን በግልጽ ያሳያል። ይሖዋ በቡልጋሪያ የነበረውን አነስተኛ ጅምር እንደባረከው በሚያሳየው በዚህ ማስረጃ ላይ ሳሰላስል እጅግ ደስ ይለኛል። በሌላው በጣም ያስደሰተኝና በሕይወቴ የማልረሳው ጉልህ ክስተት የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቡልጋሪያ ቋንቋ መውጣቱ ነው። ይህ የሆነው በ2009 በሶፊያ በተደረገው “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ!” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ነበር። ይህ መጽሐፍ ቅዱስ በራሴ ቋንቋ መውጣቱ ሕልሜ እውን የሆነልኝ ያህል ነበር! በቡልጋሪያ ሌሎች ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያውቁ ለመርዳት ጠቃሚ መሣሪያ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።
ምንም እንኳን የአካል ጉዳተኛ መሆኔ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበክ ላከናውን የምችለውን ነገር ቢገድብብኝም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለጎረቤቶቼና ወደ ቤቴ ለሚመጣ ማንኛውም ሰው በማካፈል ትልቅ ደስታ አገኛለሁ። አንድ ቀን በቤቴ ሰገነት ላይ ሳለሁ አንዲት ጎረቤቴ በመንገድ ስታልፍ አይቼ ጠራኋት። እሷም ወደ ቤት እንድትገባ ያቀረብኩላትን ግብዣ ተቀብላ ገባችና ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብዙ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን አወያየኋት፤ ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ሐሳብ ሳቀርብላት ያለማንገራገር ፈቃደኛ ሆነች። በኋላም ተጠምቃ መንፈሳዊ እህቴ ስትሆን እጅግ ተደሰትኩ። አራት ሰዎች ሕይወታቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ የመርዳት መብት አግኝቻለሁ።
በተጨማሪም ለእኔ እንደ ቤተሰብ ከሆኑልኝ ከመቶ በላይ ከሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ ስገኝ ከሁሉ የላቀ ደስታና ማበረታቻ አገኛለሁ። በምኖርበት አገር ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች የተዘጋጀ ልዩ የመጓጓዣ አገልግሎት ስለሌለ ወደ ጉባኤ ስብሰባዎች መሄድ ተፈታታኝ ይሆንብኛል። ይሁን እንጂ አንድ ወጣት ወንድም ለሚያደርግልኝ ፍቅራዊ እንክብካቤ በጣም አመስጋኝ ነኝ። የጉባኤ ስብሰባ ባለ ቁጥር ከአፓርታማዬ ወደ መኪናው፣ ከመኪናው ወደ መንግሥት አዳራሹ ተሸክሞ ይወስደኛል፤ ከዚያም በዚሁ ሁኔታ ወደ ቤት ይመልሰኛል። እንዲህ ያለ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባል የመሆን መብት በማግኘቴ ይሖዋን እጅግ አመሰግነዋለሁ!
ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ በሕይወቴ ውስጥ የተከሰቱት ነገሮች በወጣትነቴ ሳልመው ከነበረው ፈጽሞ የተለዩ እንደሆኑ ማየት እችላለሁ። ይሁን እንጂ ይሖዋን ማገልገሌ በአሁኑ ጊዜ ሊገኝ የሚችለውን ከሁሉ የላቀ ደስታ ያስገኘልኝ ሲሆን የወደፊቱን ጊዜም በተመለከተ ግሩም ተስፋ እንዲኖረኝ አስችሎኛል። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የሚፈጸመውን “አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘላል” የሚለውን አምላክ የሰጠውን ተስፋ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ። (ኢሳይያስ 35:6) ፍጹም ጤንነትና ብርታት በማግኘት ከተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ ተነስቼ የምዘልበትን ቀን በእርግጠኝነት እጠባበቃለሁ።
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ መገኘቴ ከሁሉ የላቀ ደስታና ማበረታቻ ያስገኝልኛል”
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
“በሕይወቴ የማልረሳው ጉልህ ክስተት የቅዱሳን መጻሕፍት አዲስ ዓለም ትርጉም በቡልጋሪያ ቋንቋ መውጣቱ ነው”
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ15 ዓመቴ የሰርከስ ትርዒት ማሳየት ጀመርኩ