አስከፊ ድህነት ሲባል ምን ማለት ነው?
አስከፊ ድህነት ሲባል ምን ማለት ነው?
አስከፊ ድህነት ለሕይወት አስጊ ነው። በአስከፊ ድህነት ውስጥ መኖር ሲባል በቂ ምግብ፣ ውኃና ማገዶ አለማግኘት አልፎ ተርፎም በቂ መጠለያ፣ የጤና አገልግሎትና የትምህርት ዕድል ማጣት ማለት ነው። በአሁኑ ጊዜ አንድ ቢሊዮን የሚያህሉ ሰዎች እንዲህ ባለ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን ይህ ቁጥር ከአፍሪካ ሕዝብ ብዛት ጋር እኩል ነው። ያም ሆኖ በምዕራብ አውሮፓና በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች በአስከፊ ድህነት ውስጥ መኖር ሲባል ምን ማለት እንደሆነ አያውቁም። እስቲ እንዲህ ባለ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ የሦስት ቤተሰቦችን ሕይወት እንመልከት።
አምባሩሺማ ባለትዳርና የአምስት ልጆች አባት ሲሆን የሚኖረው አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በሩዋንዳ ነው። ስድስተኛ ልጁ በወባ በሽታ ሞቶበታል። እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “አባቴ መሬቱን፣ እኔን ጨምሮ ለስድስት ልጆቹ ማከፋፈል ነበረበት። የእኔ ድርሻ በጣም ትንሽ ስለነበር ቤተሰቤን ይዤ ከተማ ገብቼ መኖር ግድ ሆነብኝ። እኔና ባለቤቴ ድንጋይና አሸዋ በመሸከም ቤተሰባችን እናስተዳድራለን። ቤታችን መስኮት የለውም። ውኃ የምንቀዳው ፖሊስ ጣቢያው አጠገብ ከሚገኝ ጉድጓድ ነው። ብዙውን ጊዜ የምንመገበው በቀን አንዴ ሲሆን ሥራ ከሌለ ግን ጦማችንን እናድራለን። የሚላስ የሚቀመስ በሌለበት ቀን ልጆቹ ርቧቸው ሲያለቅሱ ማየት ስለማያስችለኝ ከቤት ወጥቼ እሄዳለሁ።”
ቪክቶርና ካርመን የሚተዳደሩት ጫማ በማደስ ነው። እነዚህ ባልና ሚስት ከአምስት ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት ቦሊቪያ ውስጥ በሚገኝ የገጠር ከተማ ነው። የተከራዩት አንድ ክፍል ቤት ጣራው የሚያፈስ ከመሆኑም በላይ መብራት የለውም። ትምህርት ቤቱ በተማሪዎች የተጨናነቀ ከመሆኑ የተነሳ ቪክቶር ልጁ ከትምህርት ገበታ ላይ እንዳትቀር ዴስክ መሥራት ግድ ሆኖበታል። ባልና ሚስቱ ምግብ ለማብሰልና የመጠጥ ውኃ ለማፍላት የሚያስፈልጋቸውን ማገዶ ለመልቀም 10 ኪሎ ሜትር በእግር መጓዝ አለባቸው። ካርመን እንዲህ ብላለች፦ “መጸዳጃ ቤት የለንም። ስለዚህ ወደ ወንዙ መውረድ ይኖርብናል፤ ሰዎችም ገላቸውን የሚታጠቡትና ቆሻሻ የሚጥሉት እዚህ ወንዝ ላይ ነው። በዚህ የተነሳ ልጆቹ ብዙ ጊዜ ይታመማሉ።”
ፍራንሲስኮና ኤሌዲያ የሚኖሩት ሞዛምቢክ ውስጥ በሚገኝ አንድ ገጠራማ አካባቢ ነው። ከአምስት ልጆቻቸው ውስጥ አንዱ ወባ ይዞት ስለነበር ተኝቶ ለመታከም የሄደበት ሆስፒታል ሳይቀበለው በመቅረቱ ሞተ። ባልና ሚስቱ ባለቻቸው አነስተኛ መሬት ላይ ሩዝና ስኳር ድንች ያመርታሉ፤ ሆኖም ይህ የሚያቆያቸው ለሦስት ወር ያህል ብቻ ነው። ፍራንሲስኮ እንዲህ ይላል፦ “አንዳንድ ጊዜ ዝናብ ሳይጥል ይቀራል ወይም ሌቦች ምርታችንን ከማሳው ላይ ይሰርቁብናል፤ ስለዚህ ትንሽ ገንዘብ ለማግኘት ቀርከሃ እሸጣለሁ። በተጨማሪም በእግር ሁለት ሰዓት ከሚያስኬድ ጫካ
ለማገዶ የሚሆን እንጨት እንቆርጣለን። እኔና ባለቤቴ እያንዳንዳችን አንድ አንድ ሸክም ይዘን በመምጣት አንዱን ለሳምንት ያህል ምግብ ለማብሰል እንጠቀምበታለን፤ ሌላውን ደግሞ እንሸጠዋለን።”ከሰባት ሰዎች መካከል አንዱ ከአምባሩሺማ፣ ከቪክቶርና ከፍራንሲስኮ ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ሲኖር በቢሊዮን የሚቆጠሩ ሌሎች ሰዎች ግን የተንደላቀቀ ሕይወት ይመራሉ፤ ብዙዎች በዓለም ላይ የሚታየው ይህ ሁኔታ ግራ የሚያጋባቸው ከመሆኑም በላይ ፍትሕ እንዳልሆነም ይሰማቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች ሁኔታውን ለማስተካከል የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገዋል። የሚቀጥለው ርዕስ እነዚህ ሰዎች ያደረጓቸውን ጥረቶችና ተስፋ የጣሉባቸውን ነገሮች ያብራራል።
[በገጽ 2 እና 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ካርመን ከሁለት ልጆቿ ጋር ከወንዝ ውኃ ስትቀዳ