ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ
ወደ አምላክ ቅረብ
ልባቸው ለተሰበረ ሰዎች የሚሆን መጽናኛ
‘ይሖዋ ፈጽሞ ሊወደኝ አይችልም ብዬ አስብ ነበር።’ ይህን ያለችው ለብዙ ዓመታት ከመንፈስ ጭንቀት ጋር ስትታገል የኖረች አንዲት ክርስቲያን ነች። ይህች ሴት ይሖዋ ከእሷ እንደራቀ ሆኖ ይሰማት ነበር። በእርግጥ ይሖዋ በመንፈስ ጭንቀት ከሚሠቃዩ አገልጋዮቹ ይርቃል? መዝሙራዊው ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ መዝሙር 34:18 ላይ ያሰፈረው ሐሳብ የሚያጽናና መልስ ይዟል።
ዳዊት፣ ከባድ ጭንቀት በአንድ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ ላይ ምን ስሜት ሊያሳድር እንደሚችል ያውቅ ነበር። ወጣት በነበረበት ጊዜ እሱን ለመግደል ቆርጦ የተነሳ አንድ ቀናተኛ ንጉሥ ቀን ከሌት ያሳድደው ስለነበር ከቦታ ወደ ቦታ እየተንከራተተ ለመኖር ተገዶ ነበር። ዳዊት በፍልስጥኤም ምድር ወደምትገኘው ጌት ወደተባለች የጠላት ከተማ ሄዶ ጥገኝነት ጠየቀ፤ ይህን ያደረገው ሳኦል በማይገምተው ስፍራ ለመደበቅ በማሰብ ሳይሆን አይቀርም። ይሁንና ማንነቱ ሲታወቅ እብድ እንደሆነ በማስመሰል ከሞት መንጋጋ ለጥቂት አመለጠ። ዳዊት ከዚህ አደጋ ስለታደገው አምላክን አመስግኗል፤ መዝሙር 34ንም እንዲጽፍ ያነሳሳው ይህ ሁኔታ ነበር።
ዳዊት፣ አምላክ ባደረባቸው ጭንቀት የተነሳ በሐዘን ከተዋጡ ወይም የእሱን እርዳታ ለማግኘት ብቁ እንዳልሆኑ ከሚሰማቸው ሰዎች የራቀ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር? እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተሰበረውንም ያድናቸዋል።” (ቁጥር 18) እነዚህ ቃላት የሚያጽናኑትና ተስፋ የሚፈነጥቁት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
ይሖዋ ‘ቅርብ ነው።’ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህ ሐረግ “ጌታ በትኩረት የሚከታተልና ንቁ እንዲሁም ሕዝቡን ለመርዳትና ለማዳን ምንጊዜም ዝግጁ እንደሆነ የሚገልጽ ጥሩ አባባል ነው” ብሏል። ይሖዋ የሕዝቡን ሁኔታ በትኩረት እንደሚከታተል ማወቅ የሚያጽናና ነው። በዚህ “በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ሕዝቡ ምን ዓይነት ችግር እንደሚደርስበት ያያል፤ እንዲሁም የሕዝቡን ውስጣዊ ስሜት ይረዳል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ የሐዋርያት ሥራ 17:27
‘ልባቸው የተሰበረ።’ አንዳንድ ማኅበረሰቦች “የተሰበረ ልብ” የሚለውን አባባል አፍቅሮ ምላሽ ያጣ ሰው የሚሰማውን ስሜት ለማመልከት ይጠቀሙበታል። ይሁንና መዝሙራዊው የተናገራቸው ቃላት “በሌላ ምክንያት የሚመጣ ሐዘንንም ጭምር” እንደሚያመለክት አንድ ምሑር ገልጸዋል። አዎን፣ አንዳንድ ጊዜ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ ልባቸውን የሚሰብር ከባድ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል።
‘መንፈሳቸው የተሰበረ።’ ተስፋ የቆረጡ ሰዎች ለራሳቸው ያላቸው ግምት በጣም ስለሚቀንስ ለጊዜው ሁሉም ነገር ጭልምልም ይልባቸዋል። ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ መጽሐፍ ይህ አገላለጽ “የወደፊቱ ጊዜ የጨለመባቸው” ተብሎ ሊተረጎም እንደሚችል ይናገራል።
ታዲያ ይሖዋ ‘ልባቸውና መንፈሳቸው ለተሰበረ’ ሰዎች ምን አመለካከት አለው? ፍቅርና አሳቢነት ሊያሳያቸው እንደማይገባ አድርጎ በመቁጠር ከእነሱ ይርቃል? በፍጹም! ችግር የገጠመውን ልጁን አቅፎ እንደሚያጽናና አፍቃሪ ወላጅ ይሖዋም የእሱን እርዳታ ለማግኘት የሚጮኹ አገልጋዮቹን ለመርዳት ዝግጁ ነው። የተሰበረ ልባቸውንና የተደቆሰ መንፈሳቸውን ለመጠገን ልባዊ ፍላጎት አለው። ያጋጠማቸውን ማንኛውንም አስቸጋሪ ሁኔታ ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ጥበብና ጥንካሬ ሊሰጣቸው ይችላል።—2 ቆሮንቶስ 4:7፤ ያዕቆብ 1:5
ታዲያ ወደ ይሖዋ መቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ለምን ጥረት አታደርግም? ሩኅሩኅ የሆነው አምላክ እንዲህ የሚል ቃል ገብቷል፦ “የተዋረዱትን መንፈሳቸውን ለማነሣሣት፣ የተሰበረ ልብ ያላቸውን ለማነቃቃት . . . የተሰበረ ልብ ካለውና በመንፈሱ ከተዋረደው ጋር እሆናለሁ።”—ኢሳይያስ 57:15
በሰኔ ወር የሚነበብ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦
▪ ከመዝሙር 26 እስከ 59