በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

 ይህን ያውቁ ኖሯል?

ኢየሱስ ሲጸልይ ይሖዋን “አባ፣ አባት” ብሎ የጠራው ለምንድን ነው?

“አባ” የሚለው የአረማይክ ቃል “አባት” ወይም “አባት ሆይ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል። ይህ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኝባቸው በሦስቱም ቦታዎች ላይ የተሠራበት ከጸሎት ጋር በተያያዘ ሲሆን “አባ” የተባለውም በሰማይ የሚኖረው አባታችን ይሖዋ ነው። ይህ ቃል ምን ትርጉም አለው?

ዚ ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ባይብል ኢንሳይክሎፒዲያ እንዲህ ይላል፦ “በኢየሱስ ዘመን የኖሩ ሰዎች በዕለታዊ ሕይወታቸው ይጠቀሙበት በነበረው ቋንቋ፣ ‘አባ’ የሚለው ቃል በዋነኝነት የሚያገለግለው ልጆች ከአባታቸው ጋር ያላቸውን ቅርርብ እንዲሁም ለአባታቸው ያላቸውን አክብሮት ለመግለጽ ነበር።” ቃሉ፣ አንድ ልጅ አባቱን በፍቅር የሚጠራበት መንገድ ከመሆኑም ሌላ ሕፃናት መጀመሪያ ከሚያውቋቸው ቃላት አንዱ ነው። ኢየሱስ ይህንን ቃል የተጠቀመው አባቱን በጸሎት በተማጸነበት ጊዜ ነበር። ከመሞቱ ከተወሰኑ ሰዓታት በፊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ሆኖ ወደ ይሖዋ ሲጸልይ “አባ፣ አባት” በማለት ጠርቶታል።—ማርቆስ 14:36

ከላይ የተጠቀሰው ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚከተለው ብሏል፦ “የግሪካውያንና የሮማውያን ባሕል ተዋሕዶ በነበረበት ዘመን፣ በአይሁዳውያን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ውስጥ አምላክን ለመጥራት ‘አባ’ የሚለውን ቃል መጠቀም ፍጹም ያልተለመደ ነገር ነበር፤ ይህም የሆነው ቅርበትን በሚያመለክተው በዚህ ቃል አምላክን መጥራት አክብሮት አለማሳየት እንደሆነ ተደርጎ ስለሚቆጠር መሆን አለበት።” ይኸው መጽሐፍ እንደገለጸው “ኢየሱስ በጸሎቱ ላይ . . . ይህንን ቃል መጠቀሙ ከአባቱ ጋር በጣም እንደሚቀራረቡ የተናገረውን ሐሳብ በተዘዋዋሪ መንገድ የሚደግፍ ነው።” ጳውሎስ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ የሚገኙት “አባ” የሚለው ቃል የገባባቸው ሌሎች ሁለት ጥቅሶች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩት ክርስቲያኖችም ይህንን ቃል በጸሎታቸው ውስጥ ይጠቀሙበት እንደነበረ ይጠቁማሉ።—ሮም 8:15፤ ገላትያ 4:6

የተወሰነው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በግሪክኛ የተጻፈው ለምንድን ነው?

ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቅዱስ ቃል” በአደራ የተሰጠው ለአይሁዳውያን እንደሆነ ተናግሯል። (ሮም 3:1, 2) በመሆኑም በተለምዶ “ብሉይ ኪዳን” ተብሎ የሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በአብዛኛው የተጻፈው የአይሁዳውያን ቋንቋ በሆነው በዕብራይስጥ ነው። ይሁንና የክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍት የተጻፉት በግሪክኛ ነው። * ይህ የሆነው ለምንድን ነው?

በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የታላቁ እስክንድር ወታደሮች ጥንታዊውን ግሪክኛ ሲናገሩ በተለያዩ ቀበሌኛዎች ይጠቀሙ ነበር። እነዚህ ቀበሌኛዎች በመቀላቀላቸው ኮይኔ ወይም ተራው ሕዝብ የሚጠቀምበት ግሪክኛ ተፈጠረ፤ እስክንድር የተለያዩ አካባቢዎችን መውረሩ ኮይኔ የዘመኑ ዓለም አቀፍ ቋንቋ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል። በእስክንድር ዘመን አይሁዳውያን በብዙ ቦታዎች ተበትነው ይኖሩ ነበር። አይሁዳውያን ከባቢሎን ነፃ ከወጡ በርካታ መቶ ዓመታት ቢያልፉም ወደ ፓለስቲና ምድር ያልተመለሱ ብዙ አይሁዳውያን ነበሩ። በዚህም ምክንያት እያደር አብዛኞቹ አይሁዳውያን ጥርት ያለ ዕብራይስጥ መናገር ይቸገሩ ጀመር፤ በምትኩ ግሪክኛ መናገር ጀመሩ። (የሐዋርያት ሥራ 6:1) እነዚህን አይሁዳውያን ለመርዳት ሲባል የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ይኸውም ተራው ሕዝብ በሚጠቀምበት በኮይኔ ቋንቋ የተተረጎመ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ትርጉም ተዘጋጀ።

ዲክሲዮናር ደ ላ ቢብል የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የግሪክኛን ያህል በጣም ብዙ ቃላት የነበሩትና ሐሳብን እንደልብ ለመግለጽ የሚያስችል እንዲሁም በተለያየ የዓለም ክፍል የሚኖሩ ሰዎች የሚወዱት” ቋንቋ አልነበረም። የግሪክኛ ቋንቋ፣ ሐሳብን በትክክል የሚገልጹ ብዙ ቃላትና ዝርዝር የሰዋስው ሕግጋት እንዲሁም አንድ ቃል የሚያስተላልፈውን መልእክት በተሟላ መንገድ መግለጽ የሚችሉ ግሶች የነበሩት መሆኑ “በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች በስፋት የሚጠቀሙበትና የሚረዱት እንዲሁም መረጃን በትክክል ለማስተላለፍ የሚያስችል ቋንቋ እንዲሆን አድርጎታል፤ ለክርስትና መስፋፋት የሚያስፈልገው እንዲህ ዓይነት ቋንቋ ነበር።” ከዚህ አንጻር የክርስትናን መልእክት በጽሑፍ ለማስፈር የግሪክኛ ቋንቋ መመረጡ ተገቢ ነው ቢባል አትስማማም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ጥቂቶቹ የተጻፉት በአረማይክ ቋንቋ ነው። የማቴዎስ ወንጌል በመጀመሪያ የተጻፈው በዕብራይስጥ ሳይሆን አይቀርም፤ ከዚያም ማቴዎስ ራሱ ወደ ግሪክኛ እንደተረጎመው ይታመናል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የግሪክኛ የሰብዓ ሊቃናት ትርጉም ቁራጭ

[የሥዕል ምንጭ]

Courtesy of Israel Antiquities Authority