በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዕድላችን አስቀድሞ ተወስኗል?

ዕድላችን አስቀድሞ ተወስኗል?

 አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ

ዕድላችን አስቀድሞ ተወስኗል?

አንዳንድ ሰዎች የምንሞትበት ቀን አስቀድሞ እንደተወሰነ ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ አምላክ፣ እያንዳንዳችን የምንሞትበትን ጊዜ እንደሚወስን ያምናሉ። እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸው ሰዎች በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ዋና ዋና ክስተቶች መለወጥ እንደማንችልም ይሰማቸዋል። አንተስ እንደዚህ ይሰማሃል?

እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች አስብባቸው፦ ‘የወደፊት ዕጣችንን መለወጥ የማንችል ከሆነ እንዲሁም አምላክ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ነገሮች አስቀድሞ ከወሰነ መጸለያችን ምን ትርጉም አለው? ዕድላችን አስቀድሞ ከተወሰነ አደጋ እንዳያጋጥመን ጥንቃቄ ማድረጋችን ምን ፋይዳ አለው? በመኪና ስንሄድ በወንበሩ ቀበቶ መጠቀማችን ለምን አስፈለገ? መጠጥ ጠጥተን መኪና ከመንዳት መቆጠብስ ምን ጥቅም አለው?’

መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት ወደ መፈጸም የሚመራውን እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ ፈጽሞ አያበረታታም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሁሉም ነገር አስቀድሞ እንደተወሰነ በማሰብ ነገሮችን ለዕድል እንድንተው አያስተምርም። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ለአደጋ የሚያጋልጡ ነገሮችን እንዲያስወግዱ ታዝዘው ነበር። ቤት በሚሠሩበት ጊዜ በጣሪያቸው ዙሪያ መከታ እንዲያበጁ ተነግሯቸው ነበር። ይህን የሚያደርጉት አንድ ሰው ከጣሪያው ላይ ተንሸራቶ እንዳይወድቅ ለመከላከል ነው። ታዲያ አንድ ሰው ከጣሪያ ወድቆ መሞቱ አስቀድሞ የተወሰነ ነገር ከሆነ አምላክ እንዲህ ያለውን ትእዛዝ ለምን ይሰጣል?—ዘዳግም 22:8

በተፈጥሮ አደጋዎች ወይም ከሰዎች አቅም በላይ በሆኑ አሳዛኝ ገጠመኞች ምክንያት ስለሚሞቱ ሰዎችስ ምን ማለት ይቻላል? እነዚህ ሰዎች የሚሞቱበት ቀን ተቀጥሯል ማለት ነው? በፍጹም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ንጉሥ ሰለሞን ‘ሁላችንም መጥፎ ጊዜና ያልተጠበቁ ክስተቶች ያጋጥሙናል’ በማለት እውነታውን አስቀምጧል። (መክብብ 9:11 NW) በመሆኑም ሰዎች የሚያጋጥማቸው አሳዛኝ ገጠመኝ የቱንም ያህል ግራ የሚያጋባ አሊያም ለመቀበል የሚከብድ ቢሆን ሁኔታው አስቀድሞ የተወሰነ ነው ማለት አይደለም።

ይሁንና አንዳንዶች ይህ ሐሳብ ሰለሞን ቀደም ብሎ ከተናገረው ነገር ጋር እንደሚጋጭ ይሰማቸዋል። ሰለሞን እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው፤ ከሰማይ በታች ለሚከናወነው ለማንኛውም ነገር ወቅት አለው፤ ለመወለድ ጊዜ አለው፤ ለመሞትም ጊዜ አለው።” (መክብብ 3:1, 2) ሰለሞን ይህን ሲል ዕጣ ፈንታችን አስቀድሞ ስለተወሰነ ለውጥ ማምጣት አይቻልም የሚለውን አመለካከት መደገፉ ነበር? እስቲ ይህንን ጥቅስ በጥልቀት እንመርምር።

ሰለሞን ሰዎች የሚወለዱበትና የሚሞቱበት ጊዜ አስቀድሞ መወሰኑን እየተናገረ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በሕይወታችን ውስጥ እንደሚያጋጥሙን ሌሎች በርካታ ነገሮች ሁሉ መወለድና መሞትም ሁልጊዜ የሚከሰቱ መሆናቸውን መግለጹ ነበር። በሕይወት ውስጥ ጥሩም ይሁን መጥፎ ክስተቶች እንደሚያጋጥሙን የታወቀ ነው፤ ሰለሞን እንደተናገረው “ለማልቀስ ጊዜ አለው፤ ለመሣቅም ጊዜ አለው።” ሰለሞን፣ እንደነዚህ ያሉት በተደጋጋሚ የሚያጋጥሙ ነገሮችና ያልተጠበቁ አሳዛኝ ክስተቶች ‘ከሰማይ በታች ከሚከናወነው ከማንኛውም ነገር’ ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ የተለመዱ ነገሮች መሆናቸውን ገልጿል። (መክብብ 3:1-8፤ 9:11, 12) በመሆኑም ሰለሞን ሲደመድም ፈጣሪያችንን እስክንረሳ ድረስ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ከልክ በላይ መዋጥ እንደሌለብን አሳስቧል።—መክብብ 12:1, 13

ፈጣሪያችን በሕይወትም ሆነ በሞት ላይ ሥልጣን ያለው ቢሆንም የወደፊት ዕጣችንን አስቀድሞ አልወሰነም። አምላክ ለሁላችንም የዘላለም ሕይወት ተስፋ ከፊታችን እንዳስቀመጠልን መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ግብዣ እንድንቀበል አያስገድደንም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ ቃል “የሚፈልግ ሁሉ የሕይወትን ውኃ በነፃ ይውሰድ” ይላል።—ራእይ 22:17

አዎን፣ ‘የሕይወትን ውኃ የምንወስደው’ ከፈለግን ብቻ ነው። በመሆኑም የወደፊት ዕጣችን አስቀድሞ አልተወሰነም። የምናደርጋቸው ውሳኔዎች፣ አመለካከታችንና ድርጊታችን በወደፊት ሕይወታችን ላይ የጎላ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል።