በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሞተ ቋንቋ ቢተረጎምም መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው ነው

በሞተ ቋንቋ ቢተረጎምም መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው ነው

 በሞተ ቋንቋ ቢተረጎምም መጽሐፍ ቅዱስ ሕያው ነው

ባለፉት ጥቂት መቶ ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ ካሉት ቋንቋዎች መካከል ቢያንስ ግማሽ የሚሆኑት ሞተዋል። አንድ ቋንቋ ሞተ የሚባለው በዚያ ቋንቋ አፋቸውን የፈቱ ሰዎች ከሌሉ ነው። ከዚህ አንጻር ላቲን በአብዛኛው “የሞተ ቋንቋ” እንደሆነ ይገለጻል። እርግጥ ነው፣ ይህ ቋንቋ መጠነ ሰፊ ጥናት የሚደረግበት ከመሆኑም በላይ የቫቲካን ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ ያገለግላል።

ከዚህም በተጨማሪ ከመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች መካከል አንዳንዶቹ የተዘጋጁት በላቲን ነው። ታዲያ በሞተ ቋንቋ የተዘጋጁት እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በዛሬው ጊዜ “ሕያው” ሊሆኑና በአንባቢያኑ ሕይወት ላይ ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ? አስገራሚ የሆነው የእነዚህ ትርጉሞች ታሪክ ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ያስችለናል።

ጥንታዊ የሆኑት የላቲን ትርጉሞች

ላቲን የመጀመሪያው የሮም ቋንቋ ነበር። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚኖሩት ክርስቲያኖች ደብዳቤውን የጻፈው በግሪክኛ ነበር። * በሮም የሚኖሩ ሰዎች ሁለቱንም ቋንቋዎች ይናገሩ ስለነበር ጳውሎስ በግሪክኛ መጻፉ ችግር አልነበረውም። አብዛኞቹ የሮም ነዋሪዎች ግሪክኛ ተናጋሪ ከሆነው የእስያ ክፍል የመጡ በመሆናቸው ከተማዋ የግሪካውያን ከተማ እንደሆነች ይነገርላት ነበር። በሮም ግዛቶች የሚነገረው ቋንቋ እንደየአካባቢው ይለያይ ነበር፤ ሆኖም የሮም ግዛት እየተስፋፋ ሲሄድ ላቲን የሚናገሩ ሰዎችም እየበዙ ሄዱ። በዚህም ምክንያት በግሪክኛ የተጻፉት ቅዱሳን መጻሕፍት ወደ ላቲን ተተረጎሙ። ይህ የትርጉም ሥራ የተጀመረው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሰሜን አፍሪካ እንደሆነ ይታሰባል።

ወደ ላቲን የተተረጎሙት የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ዌተስ ላቲና ወይም ጥንታዊው የላቲን ትርጉም በመባል ይታወቃሉ። ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የያዘ ጥንታዊ የላቲን ትርጉም በአሁኑ ጊዜ አይገኝም። ጥንታዊ ጸሐፊዎች የሚጠቅሷቸውም ሆኑ በአሁኑ ጊዜ የሚገኙት የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች እንደሚጠቁሙት ዌተስ ላቲና በአንድ ጥራዝ የተዘጋጀ መጽሐፍ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ይህ ትርጉም የተዘጋጀው በተለያየ ጊዜና አካባቢ በኖሩ በርካታ ተርጓሚዎች እንደሆነ ይታሰባል። ስለዚህ ይህ ትርጉም በአንድ ጥራዝ የተዘጋጀ መጽሐፍ ሳይሆን ከግሪክኛ ወደ ላቲን የተተረጎሙ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ስብስብ ነው።

የተለያዩ ሰዎች አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን ለየብቻቸው ወደ ላቲን ለመተርጎም ያደረጉት ጥረት የተወሰነ ትርምስ እንዲፈጠር አድርጓል። ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአራተኛው መቶ ዘመን መገባደጃ አካባቢ ኦገስቲን እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ጥንታዊውን የግሪክኛ ቅጂ ያገኘና በመጠኑም ቢሆን ሁለቱንም ቋንቋዎች እንደሚያውቅ የተሰማው ማንኛውም ሰው ግሪክኛውን [ወደ ላቲን] ይተረጉም ነበር።” ኦገስቲንም ሆነ ሌሎች ሰዎች በወቅቱ በጣም ብዙ ትርጉሞች እንደተዘጋጁና ትክክለኛነታቸውም አጠራጣሪ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር።

ጀሮም ያዘጋጀው ትርጉም

ብዙ ትርጉሞች መኖራቸው ያስከተለውን ትርምስ ለማስቀረት ጥረት ያደረገው፣ በ382 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሮም ጳጳስ ለነበሩት ዳማሰስ አልፎ አልፎ ጸሐፊ ሆኖ ይሠራ የነበረው ጀሮም ነው። ጳጳሱ በላቲን የተተረጎሙትን ወንጌሎች እንዲያርም ጀሮምን የጠየቁት ሲሆን እሱም በጥቂት ዓመታት ውስጥ ይህን ሥራ አጠናቀቀ። ከዚያም በላቲን የተተረጎሙትን ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች የማረሙን ሥራ ተያያዘው።

በኋላ ላይ ቩልጌት ተብሎ የተጠራው የጀሮም ትርጉም የተለያዩ ምንጮችን መሠረት ያደረገ ነው። ጀሮም የመዝሙር መጽሐፍን ያዘጋጀው በሁለተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት በተጠናቀቀውና የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ግሪክኛ ትርጉም በሆነው በሰብዓ ሊቃናት ትርጉም  ላይ ተመሥርቶ ነው። ጀሮም ወንጌሎችን አርሞ ከማዘጋጀቱም በላይ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ብዙውን ክፍል በመጀመሪያዎቹ የዕብራይስጥ ቅጂዎች ላይ ተመሥርቶ ወደ ላቲን ተርጉሟል። የተቀሩት የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች የታረሙት በሌሎች ሰዎች ሳይሆን አይቀርም። ከጊዜ በኋላ የዌተስ ላቲና ትርጉም የተወሰኑ ክፍሎች ከጀሮም ቩልጌት ጋር እንዲቀላቀሉ ተደርጓል።

መጀመሪያ ላይ የጀሮም ትርጉም ብዙም ተቀባይነት አላገኘም። ኦገስቲንም እንኳ ይህን የትርጉም ሥራ ተችቶት ነበር። ውሎ አድሮ ግን ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም፣ በአንድ ጥራዝ ለሚዘጋጁ መጽሐፍ ቅዱሶች ሞዴል እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ጀመር። በስምንተኛውና በዘጠነኛው መቶ ዘመን እንደ ኣልክዊንና ቲዮደልፍ ያሉ ምሑራን፣ የጀሮም ትርጉም በተደጋጋሚ ጊዜያት በእጅ ሲገለበጥ የተፈጠሩ የቋንቋ ስህተቶችንና የቃላት ግድፈቶችን ማረም ጀመሩ። ሌሎች ምሑራን ደግሞ የትርጉም ሥራውን በምዕራፍ በመከፋፈል ጥቅሶችን ማውጣት ቀላል እንዲሆን አደረጉ። የኅትመት ሥራ ሲፈለሰፍ መጀመሪያ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ የጀሮም ትርጉም ነው።

የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የጀሮምን ትርጉም ለመጀመሪያ ጊዜ ቩልጌት በማለት የጠራችው በ1546 በትሬንት ጉባኤ ላይ ነው። ጉባኤው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ “ትክክለኛ” እንደሆነ በመጥቀስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምበት እትም እንደሚሆን ገለጸ። በዚሁ ጉባኤ ላይ መጽሐፍ ቅዱሱ እንዲታረም ተወሰነ። ይህን ሥራ ልዩ ኮሚቴዎች በበላይነት እንዲከታተሉት ታስቦ የነበረ ቢሆንም ጳጳስ ሲክስተስ አምስተኛ ሥራው ቶሎ እንዲጠናቀቅ ስለጓጉ እንዲሁም በራሳቸው ችሎታ ከልክ በላይ ስለተማመኑ ሥራውን ራሳቸው ጨረሱት። ጳጳሱ በ1590 ሲሞቱ የታረመው መጽሐፍ ቅዱስ ኅትመት ገና መጀመሩ ነበር። ብዙም ሳይቆይ ካርዲናሎቹ የጳጳሱ የትርጉም ሥራ  ብዙ ስህተት እንዳለው ስለተሰማቸው መጽሐፍ ቅዱሱ ተቀባይነት እንደሌለው የወሰኑ ከመሆኑም ሌላ የተሠራጩት ቅጂዎች እንዲሰበሰቡ አደረጉ።

በ1592 በጳጳስ ክሌመንት ስምንተኛ መሪነት የተዘጋጀው አዲሱ እትም የሲክስተስና የክሌመንት እትም ተብሎ ተጠራ። ለተወሰነ ጊዜ ያህል የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በዋነኝነት የምትጠቀመው በዚህ እትም ነበር። በተጨማሪም የሲክስተስና የክሌመንት ቩልጌት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌሎች ቋንቋዎች ለምትተረጉማቸው መጽሐፍ ቅዱሶች መሠረት ሆኖ አገልግሏል፤ በ1781 የተጠናቀቀውን የአንቶኒዮ ማርቲኒን የጣሊያንኛ ትርጉም ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል።

በላቲን ቋንቋ የተዘጋጀ ዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱስ

በ20ኛው መቶ ዘመን የኖሩ ምሑራን ቩልጌትን ከጥንታዊ ጽሑፎች ጋር ካመሣከሩ በኋላ የሰጡት ሂስ፣ እንደ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ እትሞች ሁሉ ቩልጌትም መታረም እንዳለበት በግልጽ አሳየ። ይህን ለመተግበርም በ1965 የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የአዲሱ ቩልጌት ኮሚሽን የተባለ አንድ ቡድን ያደራጀች ሲሆን ኮሚሽኑ ዘመናዊ እውቀትን መሠረት በማድረግ የላቲኑን ትርጉም እንዲያሻሽል ኃላፊነት ተሰጠው። ተሻሽሎ የሚወጣው አዲሱ መጽሐፍ ቅዱስ በካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በላቲን ቋንቋ ለሚከናወን የሃይማኖት ሥነ ሥርዓት እንዲያገለግል ታስቦ ነበር።

የአዲሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የመጀመሪያ ክፍል በ1969 የወጣ ሲሆን በ1979 ጳጳስ ጆን ፖል ሁለተኛ፣ ኖቫ ቩልጋታ ለተባለው ለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ እውቅና ሰጡ። የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ እትም በተለያዩ ቦታዎች ላይ ያዋ የሚለውን መለኮታዊ ስም አስገብቷል፤ ከእነዚህም መካከል ዘፀአት 3:15 እና ዘፀአት 6:3 ይገኙበታል። ሆኖም ከኮሚቴው አባላት አንዱ እንደተናገሩት፣ ኮሚሽኑ በመጀመሪያው እትም ላይ መለኮታዊውን ስም በማስገባቱ “ስለተጸጸተ” በ1986 በወጣው ሁለተኛ እትም ላይ “ያዋ የሚለው ቃል ወጥቶ ዶሚነስ [‘ጌታ’] የሚለው ቃል እንደገና እንዲገባ ተደረገ።”

ከዘመናት በፊት ቩልጌት ትችት እንደተሰነዘረበት ሁሉ ኖቫ ቩልጋታ የተባለው እትምም በካቶሊክ ምሑራን እንኳ ሳይቀር ተተችቷል። መጀመሪያ ላይ ይህ እትም ሲወጣ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት አንድነት እንዲኖራቸው አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ የተገለጸ  ቢሆንም ብዙዎች የተለያየ ሃይማኖታዊ እምነት ያላቸውን ተርጓሚዎች የሚያስማማ እንዳልሆነ ተሰምቷቸዋል። ለዚህም ዋነኛ ምክንያት የሆነው ጳጳሱ በዘመናዊ ቋንቋ ለሚዘጋጁ እትሞች መሠረት የሚሆነው የጥንቱ ቅጂ ሳይሆን ኖቫ ቩልጋታ እንደሆነ መናገራቸው ነው። በጀርመን አገር በካቶሊኮችና በፕሮቴስታንቶች ዘንድ ተቀባይነት ያለው የታረመ መጽሐፍ ቅዱስ ለማዘጋጀት በተደረገ ጥረት ኖቫ ቩልጋታ በሁለቱ ወገኖች መካከል ውዝግብ እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል። ካቶሊኮቹ አዲስ የሚዘጋጀው ትርጉም ከኖቫ ቩልጋታ ጋር መመሳሰል አለበት ማለታቸውን በመግለጽ ፕሮቴስታንቶቹ ቅሬታቸውን አሰምተው ነበር።

ላቲን በአሁኑ ጊዜ በሰፊው የሚነገር ቋንቋ ባይሆንም በዚህ ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። በብዙ ቋንቋዎች ሃይማኖታዊ ቃላትን ለመፍጠር መሠረት ሆኗል። የአምላክ ቃል በየትኛውም ቋንቋ ቢተረጎምም፣ በውስጡ የሚገኙትን ውድ ትምህርቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚጥሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት በመለወጥ ኃይል ያለው መሆኑን አሳይቷል።—ዕብራውያን 4:12

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.5 የክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍት በግሪክኛ የተጻፉበትን ምክንያት በተመለከተ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በገጽ 13 ላይ የሚገኘውን “ይህን ያውቁ ኖሯል?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ጳጳስ ጆን ፖል ሁለተኛ፣ ኖቫ ቩልጋታ ለተባለው መጽሐፍ ቅዱስ እውቅና ሰጡ። የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያ እትም “ያዋ” የሚለውን መለኮታዊ ስም ይዟል

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ትልቅ ለውጥ ያመጣ አተረጓጎም

ከግሪክኛ በተተረጎመው ዌተስ ላቲና በተባለው ትርጉም ላይ ያሉ በርካታ ቃላት የተተረጎሙበት መንገድ በታሪክ ውስጥ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። ከእነዚህ ቃላት አንዱ ዲያቴኬ (ቃል ኪዳን) የሚለው የግሪክኛ ቃል ነው። (2 ቆሮንቶስ 3:14 አ.መ.ት) በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን ብሉይ ኪዳን፣ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ደግሞ አዲስ ኪዳን ብለው ይጠሯቸዋል።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ብዙዎችን ያወዛገበ ፖሊሲ

አምልኮንና የሃይማኖት ሥነ ሥርዓቶችን በተመለከተ መመሪያ የሚያወጣው የቫቲካን ጉባኤ፣ አራት ዓመት ከፈጀ ሥራ በኋላ በ2001 ሊቱርጂአም ኦውቴንቲካም (ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥርዓት) የተሰኘውን ጽሑፍ አሳተመ። በርካታ የካቶሊክ ምሑራን ይህን ጽሑፍ ክፉኛ ተችተውታል።

ይህ መመሪያ፣ ኖቫ ቩልጋታ በቤተ ክርስቲያኒቱ ተቀባይነት ያገኘ መጽሐፍ ቅዱስ በመሆኑ በጥንቶቹ ቅጂዎች ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ቢለውጥም እንኳ ሌሎች ትርጉሞች በሙሉ በዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ሊሆኑ እንደሚገባ ይናገራል። አንድ መጽሐፍ ቅዱስ በካቶሊክ ባለሥልጣናት ተቀባይነት ማግኘት የሚችለው ይህን መመሪያ የተከተለ ከሆነ ብቻ ነው። መመሪያው እንደገለጸው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በተዘጋጁት መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ “በዕብራይስጥ ቴትራግራማተን (የሐወሐ) የሚወከለው ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ስም . . . በማንኛውም ቋንቋ” ዶሚነስ ወይም “ጌታ” ከሚለው ቃል ጋር ተመጣጣኝ በሆነ ቃል መተካት ይኖርበታል። ይህም የኖቫ ቩልጋታ የመጀመሪያው እትም “ያዌ” የሚለውን ስም የያዘ ቢሆንም በሁለተኛው እትም ላይ “ዶሚነስ” በሚለው ቃል ከመተካቱ ጋር የሚስማማ እንደሚሆን መመሪያው ገልጿል። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.29 “ቫቲካን መለኮታዊው ስም ጥቅም ላይ እንዳይውል ትከላከላለች” የሚለውን በገጽ 30 ላይ የሚገኘውን ርዕስ ተመልከት።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ800 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በላቲን ቋንቋ የተዘጋጀው የአልክዊን መጽሐፍ ቅዱስ

[የሥዕል ምንጭ]

From Paléographìe latine, by F. Steffens (www.archivi.beniculturali.it)

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሲክስተስና የክሌመንት “ቩልጌት” 1592

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዘፀአት 3:15 በኖቫ ቩልጋታ መጽሐፍ ቅዱስ፣ 1979

[ምንጭ]

© 2008 Libreria Editrice Vaticana