በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኢየሱስ አምላክ ነው?

ኢየሱስ አምላክ ነው?

ብዙ ሰዎች፣ የሥላሴ ትምህርት “የክርስትና ሃይማኖት ዋነኛ መሠረተ ትምህርት” እንደሆነ ይሰማቸዋል። በዚህ ትምህርት መሠረት አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ በሦስት አካል ውስጥ የሚኖሩ አንድ አምላክ ናቸው። ካርዲናል ጆን ኦኮነር፣ የሥላሴ ትምህርት “ለመረዳት የሚከብድ እጅግ ጥልቅ ሚስጥር እንደሆነ እናውቃለን” ብለዋል። የሥላሴን ትምህርት መረዳት ይህን ያህል የሚከብደው ለምንድን ነው?

ዚ ኢለስትሬትድ ባይብል ዲክሽነሪ አንደኛውን ምክንያት ይጠቁመናል። ይህ መጽሐፍ ስለ ሥላሴ ሲናገር “በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሥላሴን የሚያብራራ አንድም ጥቅስ ስለማይገኝ ይህ መሠረተ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አይደለም” ብሏል። ሥላሴ ‘በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ትምህርት ስላልሆነ’ የሥላሴ አማኞች ይህን ትምህርት የሚደግፉ የሚመስሉ ጥቅሶችን ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት አንዳንድ ጥቅሶችን ወደማጣመም መርቷቸዋል።

ስለ ሥላሴ የሚያስተምር ጥቅስ ነው?

የሥላሴ አማኞች ብዙውን ጊዜ አላግባብ ከሚጠቅሷቸው ጥቅሶች አንዱ የሆነውን ዮሐንስ 1:1⁠ን እንደ ምሳሌ እንመልከት። በአዲሱ መደበኛ ትርጉም ይህ ጥቅስ እንዲህ ይላል፦ “በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም ከእግዚአብሔር [ግሪክኛ፣ ቶን ቴኦን] ጋር ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር [ግሪክኛ፣ ቴኦስ] ነበረ።” በዚህ ጥቅስ ላይ ቴኦስ (አምላክ) የሚለው የግሪክኛ ስም በሁለት መንገዶች ተቀምጧል። ከመጀመሪያው ስም በፊት ቶን የሚል የግሪክኛ ጠቃሽ አመልካች ገብቷል፤ በመሆኑም በዚህ ቦታ ላይ ቴኦን የሚለው ቃል ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ያመለክታል። ከሁለተኛው ስም በፊት ግን ምንም ዓይነት ጠቃሽ አመልካች አልገባም። እዚህ ቦታ ላይ ጠቃሽ አመልካች ያልገባው በስህተት ነው?

የሥላሴን ትምህርት መረዳት ይህን ያህል የሚከብደው ለምንድን ነው?

የዮሐንስ ወንጌል የተጻፈው ኮይኔ ተብሎ በሚጠራው ተራው ሕዝብ በሚግባባበት ግሪክኛ ነበር፤ ይህ ዓይነቱ ግሪክኛ የጠቃሽ አመልካችን አጠቃቀም በተመለከተ ግልጽ የሆነ የሰዋስው ሥርዓት አለው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር የሆኑት ኣርኪባልድ ሮበርትሰን እንደተናገሩት የአንድ ዓረፍተ ነገር ባለቤትም ሆነ ተሳቢው ጠቃሽ አመልካች ካላቸው “ሁለቱም  የታወቁ፣ አንድ ዓይነትና ምንም ልዩነት የሌላቸው ናቸው፤ እንዲሁም አንዱ ሌላውን ሊተካና ሊወክል ይችላል።” ሮበርትሰን ማቴዎስ 13:38⁠ን እንደ ምሳሌ ይጠቅሳሉ፤ ጥቅሱ በአዲሱ መደበኛ ትርጉም “ዕርሻውም [በግሪክኛ፣ ሆ አግሮስ] ይህ ዓለም [በግሪክኛ፣ ሆ ኮስሞስ] ነው” ይላል። ከሰዋስው ሕግ አንጻር ይህን ዓረፍተ ነገር ‘ይህ ዓለም ዕርሻው ነው’ ብሎ ማስቀመጥም ይቻላል።

ይሁንና በ⁠ዮሐንስ 1:1 ላይ እንደምናገኘው የአንድ ዓረፍተ ነገር ባለቤት ጠቃሽ አመልካች ኖሮት ተሳቢው ጠቃሽ አመልካች ባይኖረውስ? ጄምስ አለን ሂዩት የተባሉ አንድ ምሑር ይህንን ጥቅስ እንደ ምሳሌ በመውሰድ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “እንዲህ ባለው ዓረፍተ ነገር ውስጥ ባለቤቱና ተሳቢው አንድ ዓይነት፣ እኩል እንዲሁም ምንም ልዩነት የሌላቸው አይደሉም።”

ሂዩት ሐሳባቸውን በምሳሌ ለማስረዳት “አምላክ ብርሃን ነው” የሚለውን 1 ዮሐንስ 1:5⁠ን ይጠቅሳሉ። እዚህ ጥቅስ ላይ ያለው “አምላክ” በግሪክኛ ሆ ቴኦስ ሲሆን ጠቃሽ አመልካች አለው። ይሁን እንጂ “ብርሃን” ተብሎ የተተረጎመው ፎስ የሚለው የግሪክኛ ቃል ጠቃሽ አመልካች አልገባለትም። ሂዩት እንዲህ ብለዋል፦ “ምንጊዜም ቢሆን አንድ ሰው፣ . . . አምላክ ብርሃን እንደሆነ መናገር ይችላል፤ ብርሃን አምላክ እንደሆነ መናገር የሚቻለው ግን ሁልጊዜ አይደለም።” ሌሎች ምሳሌዎችንም “አምላክ መንፈስ ነው” በሚለው በ⁠ዮሐንስ 4:24 ላይ እና “አምላክ ፍቅር ነው” በሚለው በ⁠1 ዮሐንስ 4:16 ላይ ማግኘት ይቻላል። በሁለቱም ጥቅሶች ላይ የዓረፍተ ነገሩ ባለቤት ጠቃሽ አመልካች ያለው ሲሆን “መንፈስ” እና “ፍቅር” የሚሉት ተሳቢዎች ግን ጠቃሽ አመልካች አልገባላቸውም። ስለዚህ የዓረፍተ ነገሮቹ ባለቤትና ተሳቢዎቹ እርስ በርስ ሊተካኩ አይችሉም። እነዚህ ጥቅሶች “መንፈስ አምላክ ነው” ወይም “ፍቅር አምላክ ነው” ተብለው ሊቀመጡ አይችሉም።

ስለ “ቃል” ማንነት የሚናገር ጥቅስ ነው?

በርካታ የግሪክኛ ቋንቋ ምሑራንና የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች፣ ዮሐንስ 1:1 የሚያጎላው ‘የቃልን’ ማንነት ሳይሆን የእሱን አንድ ባሕርይ እንደሆነ ያምናሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ የሆኑት ዊልያም ባርክሌይ እንዲህ ብለዋል፦ “[ሐዋርያው ዮሐንስ] ከቴኦስ በፊት ጠቃሽ አመልካች ስላልተጠቀመ ቴኦስ በዚህ አገባቡ ገላጭ ቃል ይሆናል። . . . እዚህ ላይ ዮሐንስ ቃልና አምላክ ምንም ልዩነት የላቸውም ማለቱ አልነበረም። በቀላል አነጋገር ኢየሱስ አምላክ ነው አላለም።” በተመሳሳይም የሃይማኖት ምሑር የሆኑት ጄሰን ቤዱን እንደተናገሩት በግሪክኛ የሰዋስው ሕግ ቴኦስ ከሚለው ስም በፊት ጠቃሽ አመልካች ካልገባ (በ⁠ዮሐንስ 1:1ሐ ላይ እንዳለው) አንባቢያን ይህን ቃል የሚረዱት ‘የመለኮትነት ባሕርይ የተላበሰ’ እንደሚል አድርገው ነው። ቤዱን እንዲህ ብለዋል፦ “ቴኦስ ጠቃሽ አመልካች ያልገባለት መሆኑ ሆ ቴኦስ ከሚለው ጠቃሽ አመልካች ከገባለት ስም የተለየ እንዲሆን ያደርገዋል። . . . ዮሐንስ 1:1 ላይ የተጠቀሰው ‘ቃል’ የሚያመለክተው ብቻውን አምላክ የሆነውን አካል ሳይሆን . . . የመለኮትነት ባሕርይ የተላበሰን አካል ነው።” አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርዥን የተሰኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ካዘጋጁት ምሑራን መካከል አንዱ የሆኑት ጆሴፍ ሄንሪ ታየር እንደተናገሩት “ሎጎስ [ወይም፣ ቃል] መለኮታዊ ባሕርይ የተላበሰ እንጂ ራሱ መለኮት አይደለም።”

ኢየሱስ በእሱና በአባቱ መካከል ግልጽ ልዩነት እንዳለ አሳይቷል

የአምላክ ማንነት “እጅግ ጥልቅ ሚስጥር” ሊሆን ይገባዋል? ኢየሱስ እንደዚህ አልተሰማውም። ኢየሱስ እንደሚከተለው በማለት ወደ አባቱ ሲጸልይ በእሱና በአባቱ መካከል ግልጽ ልዩነት እንዳለ አሳይቷል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።” (ዮሐንስ 17:3) ኢየሱስን የምናምንና ግልጽ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የምንገነዘብ ከሆነ ኢየሱስን የመለኮትነት ባሕርይ ያለው የአምላክ ልጅ እንደሆነ አድርገን በመቀበል እናከብረዋለን። ይሖዋን ደግሞ “ብቸኛው እውነተኛ አምላክ” እንደሆነ በማመን እናመልከዋለን።