በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

 ልጆቻችሁን አስተምሩ

ኢዮአስ መጥፎ ጓደኝነት በመመሥረቱ ይሖዋን ተወ

ኢዮአስ መጥፎ ጓደኝነት በመመሥረቱ ይሖዋን ተወ

የአምላክ ቤተ መቅደስ በነበረባት በኢየሩሳሌም ከተማ ሁኔታዎች አስጨናቂ የሆኑበት ጊዜ ነበር። ንጉሥ አካዝያስ ከተገደለ ብዙም አልቆየም። የአካዝያስ እናት ጎቶልያ፣ ልጇ ከተገደለ በኋላ ያደረገችው ነገር ለማሰብ እንኳ ይከብዳል። ጎቶልያ የአካዝያስ ልጆች የሆኑትን የልጅ ልጆቿን አስገደለቻቸው! ይህን ያደረገችው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— * በእነሱ ፋንታ እሷ መንገሥ ስለፈለገች ነበር።

ይሁንና ከጎቶልያ የልጅ ልጆች መካከል አንዱ የሆነው ሕፃኑ ኢዮአስ ከሞት ተርፎ ነበር፤ ይህ መሆኑን አያቱም እንኳ አላወቀችም። ኢዮአስ ከሞት የተረፈው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ?— ሕፃኑ፣ ዮሳቤት የምትባል አክስት ነበረችው፤ ይህቺ ሴት ኢዮአስን ወስዳ በአምላክ ቤተ መቅደስ ውስጥ ደበቀችው። ዮሳቤት ይህንን ማድረግ የቻለችው ባሏ ዮዳሄ ሊቀ ካህናት ስለነበር ነው። እነዚህ ባልና ሚስት ኢዮአስን ጉዳት እንዳይደርስበት ሸሸጉት።

ኢዮአስ ለስድስት ዓመታት ያህል በቤተ መቅደሱ ውስጥ ተደብቆ ቆየ። እዚያ እያለ ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ሕጎቹ ብዙ ነገር ተማረ። ኢዮአስ ሰባት ዓመት ሲሆነው ዮዳሄ እሱን ለማንገሥ አንዳንድ እርምጃዎችን ወሰደ። ዮዳሄ፣ ኢዮአስን ያነገሠው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም የኢዮአስ አያት የሆነችው ክፉዋ ንግሥት ጎቶልያ ምን እንደደረሰባት ማወቅ ትፈልጋለህ?—

ዮዳሄ፣ በወቅቱ በኢየሩሳሌም የነበሩ ነገሥታትን የሚጠብቁ ልዩ ዘብ ጠባቂዎችን በሚስጥር ጠራ። ከዚያም እሱና ሚስቱ የንጉሥ አካዝያስን ልጅ በሕፃንነቱ እንዴት እንዳዳኑት ነገራቸው። ቀጥሎም ኢዮአስን ለዘብ ጠባቂዎቹ አሳያቸው፤ እነሱም ንጉሥ መሆን የሚገባው ኢዮአስ መሆኑን ተስማሙ። ስለዚህ ምን እንደሚያደርጉ እቅድ አወጡ።

ዮዳሄ፣ ኢዮአስን ከተደበቀበት አወጣውና ዘውዱን ጫነለት። በዚህ ጊዜ ሕዝቡ “‘ንጉሡ ሺህ ዓመት ይንገሥ’ እያሉ በማጨብጨብ ደስታቸውን ከፍ ባለ ድምፅ ገለጹ።” ዘብ ጠባቂዎቹ በኢዮአስ ዙሪያ በመሆን አደጋ እንዳይደርስበት ይጠብቁት ነበር። ጎቶልያ ይህንን የደስታ ጩኸት ስትሰማ ካለችበት ሮጣ በመምጣት ተቃውሞዋን አሰማች። ይሁንና ዮዳሄ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ዘብ ጠባቂዎቹ ጎቶልያን ገደሏት።—2 ነገሥት 11:1-16

ኢዮአስ፣ ዮዳሄ የሚነግረውን መስማቱንና ትክክል የሆነውን ማድረጉን የቀጠለ ይመስልሃል?— ዮዳሄ በሕይወት እስካለ ድረስ እንዲህ አድርጎ ነበር። እንዲያውም ኢዮአስ፣ አባቱ አካዝያስና  አያቱ ኢዮራም ችላ ያሉት የአምላክ ቤተ መቅደስ እንዲታደስ ሕዝቡ ገንዘብ እንዲሰጥ አድርጎ ነበር። ይሁንና ሊቀ ካህናቱ ዮዳሄ ሲሞት ኢዮአስ ምን እንዳደረገ እንመልከት።—2 ነገሥት 12:1-16

ኢዮአስ ከሞት ተረፈ

በዚህ ጊዜ ኢዮአስ 40 ዓመት ሆኖታል። ኢዮአስ፣ ይሖዋን ከሚያገለግሉ ጋር የነበረውን ወዳጅነት ከማጠናከር ይልቅ የሐሰት አማልክት ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር ወዳጅነት መሠረተ። በወቅቱ የዮዳሄ ልጅ ዘካርያስ የይሖዋ ካህን ሆኖ ያገለግል ነበር። ዘካርያስ፣ ኢዮአስ መጥፎ ድርጊት እየፈጸመ መሆኑን ሲያውቅ ምን ያደረገ ይመስልሃል?—

ዘካርያስ፣ ኢዮአስንና ሕዝቡን “እናንተ እግዚአብሔርን ስለ ተዋችሁት እርሱም ትቶአችኋል” አለው። ኢዮአስ ይህን ሲሰማ በጣም ስለተናደደ ዘካርያስ በድንጋይ ተወግሮ እንዲገደል አዘዘ። እስቲ አስበው፣ ኢዮአስ በአንድ ወቅት ከነፍሰ ገዳይ እጅ ቢያመልጥም አሁን እሱ ራሱ ዘካርያስን አስገደለው!—2 ዜና መዋዕል 24:1-3, 15-22

ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት የምናገኝ ይመስልሃል?— አንደኛ፣ በጥላቻ የተሞላችና ጨካኝ እንደነበረችው እንደ ጎቶልያ መሆን በጭራሽ አንፈልግም። ከዚህ በተቃራኒ ኢየሱስ እንዳስተማረን የእምነት ባልንጀሮቻችንን ሌላው ቀርቶ ጠላቶቻችንን እንኳ መውደድ አለብን። (ማቴ. 5:44፤ ዮሐ. 13:34, 35) ከዚህም በተጨማሪ መጀመሪያ ላይ ኢዮአስ እንዳደረገው ትክክል የሆነውን ነገር እያደረግን ከሆነ በዚሁ ጎዳና መቀጠል እንድንችል ይሖዋን የሚወዱና እሱን እንድናገለግል የሚያበረታቱ ወዳጆችን ማፍራታችንን መቀጠል እንደሚኖርብን አስታውስ።

^ አን.3 ይህን ርዕስ የምታነበው ከትንሽ ልጅ ጋር ከሆነ ይህ ሰረዝ ቆም ብለህ ልጁ ሐሳቡን እንዲገልጽ እንድታበረታታው ለማስታወስ ተብሎ የተደረገ ነው።