በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ማርያም በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያላት ድርሻ

ማርያም በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያላት ድርሻ

 ማርያም በአምላክ ዓላማ ውስጥ ያላት ድርሻ

ኢየሱስ አገልግሎቱን እያከናወነ በነበረበት ወቅት ከሕዝቡ መካከል አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “አንተን የተሸከመ ማህፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ደስተኞች ናቸው!” አለችው። ኢየሱስ፣ እናቱ አምልኮታዊ አክብሮት እንዲሰጣት ቢፈልግ ኖሮ ሰዎች እንዲህ እንዲያደርጉ ለማበረታታት ይህ ጥሩ አጋጣሚ ይሆንለት ነበር። ኢየሱስ ግን “ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!” ሲል መለሰላት።—ሉቃስ 11:27, 28

ኢየሱስ ለእናቱ የተለየ ክብር ያልሰጣት ከመሆኑም ሌላ ተከታዮቹም ቢሆኑ እንዲህ እንዲያደርጉ ፈጽሞ አላስተማረም። ይህ ታዲያ ቅን የሆኑ በርካታ ምእመናን ለማርያም ከሚሰጧት አምልኮታዊ አክብሮት ጋር የሚጋጭ አይሆንም? የኢየሱስን እናት አስመልክቶ በአሁኑ ጊዜ ተስፋፍተው ስለሚገኙት አንዳንድ ትምህርቶች መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል እስቲ እንመርምር።

“ጸጋ የሞላብሽ፣” “ከሴቶች መካከል የተባረክሽ”

መልአኩ ገብርኤል፣ ማርያም በአምላክ ዓላማ ውስጥ ምን ድርሻ እንደሚኖራት ነግሯታል። በዚህ ወቅት “እጅግ የተወደድሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ይሖዋ ከአንቺ ጋር ነው” ብሏት ነበር። (ሉቃስ 1:28) አንድ ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ገብርኤል ለማርያም ያቀረበውን ይህን ሰላምታ “ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፣ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” በማለት ተርጉሞታል። ትንሽ ቆየት ብሎ ኤልሳቤጥ ማርያምን “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ፤ የማህፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው!” ብላታለች። (ሉቃስ 1:42) ታዲያ እነዚህ አባባሎች ማርያም አምልኮታዊ አክብሮት ሊሰጣት እንደሚገባ አያሳዩም?

እንደ እውነቱ ከሆነ አያሳዩም። እነዚህ አባባሎች የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ለማርያም በሚያቀርቡት ጸሎት ውስጥ የተካተቱ ቢሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ለማርያም ጸሎት ማቅረብ እንዳለብን አያስተምርም።  ገብርኤልና ኤልሳቤጥ፣ ማርያም መሲሑን የመውለድ ልዩ መብት እንዳገኘች የገለጹ ቢሆንም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ለእሷ መጸለይ እንዳለብን የሚጠቁም ምንም ሐሳብ አናገኝም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ እንዴት መጸለይ እንዳለባቸው እንዲያስተምራቸው በጠየቁት ጊዜ ጸሎት መቅረብ የሚገባው ለአባቱ እንደሆነ አመልክቷል። እንዲያውም በብዙዎች ዘንድ የሚታወቀው የኢየሱስ የናሙና ጸሎት የሚጀምረው “በሰማያት የምትኖር አባታችን” በሚሉት ቃላት ነው።—ማቴዎስ 6:9

ከሌሎች ጋር የመግዛት መብት አግኝታለች

በብዙዎች ዘንድ የሚታመንበት ሌላው ትምህርት ደግሞ በአሁኑ ጊዜ ማርያም “የሰማይ ንግሥት” እንደሆነች የሚገልጸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ማርያምን እንዲህ ባለ የማዕረግ ስም ፈጽሞ ጠርቷት አያውቅም። ይሁንና በአምላክ ሰማያዊ መስተዳድር ውስጥ ልዩ ቦታ እንዳላት ይናገራል። ማርያም በዚህ መስተዳድር ውስጥ ያላት ቦታ ምንድን ነው?

ኢየሱስ ከታማኝ ደቀ መዛሙርቱ መካከል የተወሰኑት በመንግሥቱ ከእሱ ጋር ገዥዎች እንደሚሆኑ ጠቁሟል። (ሉቃስ 22:28-30) ከእሱ ጋር እንዲገዙ የተመረጡት እነዚህ ሰዎች ‘ለአምላካችን ካህናት እንዲሆኑና በምድር ላይ ነገሥታት ሆነው እንዲገዙ’ ሥልጣን ይሰጣቸዋል። (ራእይ 5:10) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ማርያም ይህ ታላቅ መብት ከተሰጣቸው ሰዎች መካከል አንዷ እንደሆነች እንድንገነዘብ ይረዳናል። እንዴት?

ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ማርያም ከደቀ መዛሙርቱና ከወንድሞቹ ጋር ሆና ‘ተግታ ትጸልይ’ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገር ሳታስታውስ አትቀርም። በወቅቱ 120 የሚያህሉ ሰዎች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ መካከል “አንዳንድ ሴቶች” ይገኙበት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 1:12-15) መጽሐፍ ቅዱስ፣ “በጴንጤቆስጤ በዓል ቀን ሁሉም በአንድ ቦታ ተሰብስበው” ሳለ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እንደወረደባቸውና በተለያዩ ልሳኖች እንደተናገሩ ይገልጻል።—የሐዋርያት ሥራ 2:1-4

ማርያም መንፈስ ቅዱስ ከወረደባቸው ሰዎች መካከል አንዷ መሆኗ በሰማያዊ መንግሥቱ ከኢየሱስ ጋር እንድትገዛ እንደተመረጠች ያሳያል። ስለሆነም ማርያም በአሁኑ ጊዜ ሰማያዊ ክብር ተጎናጽፋ ከኢየሱስ ጋር በመግዛት ላይ እንደምትገኝ የሚያረጋግጥ በቂ ማስረጃ አለን። (ሮም 8:14-17) ማርያምም ሆነች ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚገዙ ሁሉ የአምላክ ዓላማ ፍጻሜውን እንዲያገኝ በማድረግ ረገድ የሚኖራቸውን ድርሻ እስቲ እንመልከት።

ለመላው የሰው ዘር አስደናቂ በረከቶችን ማዳረስ

የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የራእይ መጽሐፍ 144,000 ሰዎች ከኢየሱስ ጋር ካህናት፣ ፈራጆችና ነገሥታት ሆነው ለማገልገል ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ክብር እንደሚጎናጸፉ ይገልጻል። (ራእይ 14:1, 4፤ 20:4, 6) ካህናት እንደመሆናቸው መጠን የኢየሱስ መሥዋዕት የሚያስገኘውን በረከት ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ በማዳረሱ ሥራ ላይ የሚካፈሉ ሲሆን በመንፈሳዊ፣ በሥነ ምግባራዊና በአካላዊ ሁኔታ ፍጽምና ደረጃ ላይ እንዲደርሱ ይረዷቸዋል። (ራእይ 21:1-4) ታማኝ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ ለዚህ በረከት መብቃታቸው እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! *

ማርያም ከይሖዋ ዓላማዎች አፈጻጸም ጋር በተያያዘ ትልቅ ሚና የተጫወተች ሲሆን አሁንም የበኩሏን ድርሻ በማበርከት ላይ ትገኛለች። ማርያም የተጣለባትን የእናትነት ኃላፊነት ስትወጣ ያሳየችውን ትሕትና፣ እምነት፣ ታዛዥነትና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ብሎም ፈተናን በመቋቋም ያሳየችውን ጽናት ልንኮርጅ ይገባል። መሲሑን በመውለድ የተጫወተችው ሚና እንዲሁም ለሰው ልጆች ዘላለማዊ በረከቶችን በማዳረስ ረገድ ያላት ድርሻ ከፍተኛ አክብሮት እንድንሰጣት ይገፋፋናል።

ይሁን እንጂ ከማርያም ልናገኝ የሚገባው ከሁሉ የላቀ ትምህርት፣ ከሌሎች ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ጋር ሆና ይሖዋን ብቻ የምታመልክ መሆኗ ነው። “በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና [ለይሖዋ አምላክ] ለበጉ [ለኢየሱስ ክርስቶስ] በረከት፣ ክብር፣ ግርማና ኃይል ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን” ብለው ከሚያውጁት በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ከሚነግሡት ገዥዎች መካከል ማርያምም ትገኝበታለች።—ራእይ 5:13፤ 19:10

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.13 እነዚህን በረከቶች አስመልክቶ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ማርያም ያሳየችውን ትሕትና፣ እምነትና ታዛዥነት ልንኮርጅ ይገባል