አንዳንድ ጸሎቶች መልስ የማያገኙት ለምንድን ነው?
አንባቢያን የሚያነሱት ጥያቄ
ይሖዋ የሚቀረብ አምላክ ነው። አንድ አፍቃሪ አባት ልጆቹ የልባቸውን አውጥተው በነፃነት ሲነግሩት እንደሚደሰት ይሖዋም ወደ እሱ መጸለያችን ያስደስተዋል። ይሁን እንጂ ጥበበኛ የሆነ አባት ልጆቹ የሚጠይቁትን ነገር በሙሉ እንደማያደርግላቸው ሁሉ አምላክም ለአንዳንድ ጸሎቶች መልስ የማይሰጥበት በቂ ምክንያት አለው። አምላክ ለአንዳንድ ጸሎቶች መልስ የማይሰጥበት ምክንያት አይታወቅም ወይስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የሚናገረው ነገር አለ?
ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይህ ነው፤ የምንጠይቀው ነገር ምንም ይሁን ምን ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ ሁኔታ እስከለመንን ድረስ ይሰማናል።” (1 ዮሐንስ 5:14) የምናቀርበው ጸሎት ከአምላክ ፈቃድ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት። አንዳንዶች ከአምላክ ፈቃድ ጋር በቀጥታ የሚጋጩ ጸሎቶችን ያቀርባሉ፤ ለምሳሌ ያህል፣ ሎተሪ እንዲደርሳቸው ወይም በውርርድ እንዲያሸንፉ ይጸልያሉ። ሌሎች ደግሞ የሚጸልዩት ለተሳሳተ ዓላማ ነው። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ፣ ጸሎትን በዚህ መንገድ ልንጠቀምበት እንደማይገባ ሲያስጠነቅቅ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ትጠይቃላችሁ ግን አታገኙም፤ ምክንያቱም የምትጠይቁት ለተሳሳተ ዓላማ ይኸውም ኃይለኛ ሥጋዊ ፍላጎታችሁን ለማርካት ነው።”—ያዕቆብ 4:3
ለምሳሌ ያህል፣ በእግር ኳስ ጨዋታ ሁለቱም ተጋጣሚ ቡድኖች ማሸነፍ እንዲችሉ ይጸልያሉ። አምላክ እንዲህ ላሉት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ጸሎቶች መልስ ይሰጣል ብሎ መጠበቅ የማይመስል ነገር ነው። በዘመናችን በሚደረጉ ጦርነቶች፣ ሁለት ተጻራሪ ወገኖች አንዳቸው በሌላው ላይ ድል ለመቀዳጀት የሚያቀርቡትን ጸሎት በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።
የአምላክን ሕግ ለመከተል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የሚያቀርቡት ጸሎት ምላሽ አያገኝም። በአንድ ወቅት ይሖዋ ግብዝ የነበሩትን አምላኪዎቹን “አብዝታችሁ ብትጸልዩም እንኳ አልሰማችሁም፤ እጆቻችሁ በደም ተበክለዋል” ብሏቸው ነበር። (ኢሳይያስ 1:15) መጽሐፍ ቅዱስ “ሕግን ላለመስማት ጆሮውን የሚደፍን፣ ጸሎቱ እንኳ አስጸያፊ ነው” ይላል።—ምሳሌ 28:9
በሌላ በኩል ይሖዋ እሱን እንደ ፈቃዱ ለማገልገል አቅማቸው የፈቀደውን ያህል የሚጥሩ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡትን ልባዊ ጸሎት ለመስማት ዝግጁ ነው። ይህ ሲባል ግን ለሚያቀርቡት ጸሎት ሁሉ መልስ ይሰጣቸዋል ማለት ነው? በፍጹም። እስቲ አንዳንድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምሳሌዎችን እንመልከት።
ሙሴ ከአምላክ ጋር እጅግ የተቀራረበ ዝምድና የነበረው ቢሆንም “[ከአምላክ ፈቃድ] ጋር በሚስማማ ሁኔታ” መጸለይ ይጠበቅበት ነበር። ሙሴ “ከዮርዳኖስ ማዶ ያለችውን ያችን መልካሚቱን ምድር፣ . . . እንዳይ ፍቀድልኝ” በማለት ወደ ከነዓን ምድር መግባት እንዲፈቀድለት በመጠየቅ ከአምላክ ዓላማ ጋር የማይስማማ ልመና አቅርቦ ነበር። ይሁንና ሙሴ በሠራው ኃጢአት ምክንያት ወደዚህች ምድር እንደማይገባ ቀደም ሲል ተነግሮት ነበር። ስለሆነም ይሖዋ፣ ሙሴ የጠየቀውን ነገር ከመፍቀድ ይልቅ “ይበቃል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ስለዚህ ነገር አታንሣብኝ” ብሎታል።—ዘዳግም 3:25, 26፤ 32:51
ሐዋርያው ጳውሎስ “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” ብሎ ከጠራው ችግር እንዲገላግለው ወደ አምላክ ጸልዮ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 12:7) እዚህ ላይ “እሾህ” ብሎ የገለጸው ችግር ሥር የሰደደ የዓይን ሕመም አሊያም ተቃዋሚዎችና “ሐሰተኛ ወንድሞች” የሚሰነዝሩበት ዘለፋ ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮንቶስ 11:26፤ ገላትያ 4:14, 15) ጳውሎስ “ይህ ነገር ከእኔ እንዲርቅ ጌታን ሦስት ጊዜ ለመንኩት” በማለት ጽፏል። ይሁን እንጂ ይሖዋ፣ ጳውሎስ “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” ብሎ የገለጸውን ይህን እረፍት የሚነሳ ችግር ተቋቁሞ መስበኩን መቀጠሉ የአምላክን ኃይልም ሆነ ጳውሎስ በእሱ ላይ ያለውን ጠንካራ እምነት በግልጽ እንደሚያሳይ ያውቅ ነበር። በመሆኑም አምላክ፣ ጳውሎስ የጠየቀውን ነገር ከመፈጸም ይልቅ “ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በድካም ጊዜ ነው” ብሎታል።—2 ቆሮንቶስ 12:8, 9
አዎን፣ አምላክ የሚጠቅመንን ነገር ከእኛ በተሻለ ያውቃል። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙት ፍቅራዊ ዓላማዎቹ ጋር በሚስማማ ሁኔታና ለእኛ በሚጠቅመን መንገድ ለምናቀርበው ጸሎት ምንጊዜም መልስ ይሰጠናል።