በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በእናቱ ማህፀን ውስጥ የሞተ ሕፃን የትንሣኤ ተስፋ አለው?

እንዲህ ያለ አሳዛኝ ሁኔታ ያልደረሰባቸው ሰዎች፣ ሕፃናት ልጆቻቸውን በዚህ መንገድ ያጡ ወላጆች የሚሰማቸውን ስሜት መረዳት አዳጋች ሊሆንባቸው ይችላል። አንዳንድ ወላጆች እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲደርስባቸው ከባድ ሐዘን ላይ ይወድቃሉ። አንዲት እናት በዚህ መንገድ አምስት ልጆቿን አጥታለች። ከጊዜ በኋላ፣ ጤናማ የሆኑ ሁለት ወንዶች ልጆችን መውለድ በመቻሏ እንደተባረከች ተሰምቷታል። ሆኖም በሞት ያጣቻቸውን ልጆቿን ዘወትር ታስታውሳለች። ሞተው የተወለዱና የጨነገፉ ልጆቿ በሕይወት ቢኖሩ ኖሮ ስንት ዓመት ሊሆናቸው እንደሚችል ሁልጊዜ ታስባለች። እንዲህ ያለ ሐዘን የደረሰባቸው ክርስቲያኖች ልጆቻቸውን በትንሣኤ እንደሚያገኙ ተስፋ ማድረግ ይችላሉ?

በአጭሩ የዚህ ጥያቄ መልስ ‘ማወቅ አንችልም’ የሚል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሞተው ስለተወለዱ ወይም ስለጨነገፉ ሕፃናት ትንሣኤ በቀጥታ የሚናገረው ነገር የለም። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል ከዚህ ጥያቄ ጋር ግንኙነት ያላቸው መሠረታዊ ሥርዓቶችን የያዘ ሲሆን እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች በተወሰነ ደረጃ ማጽናኛ ሊሰጡ ይችላሉ።

ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጋር የተያያዙ ሁለት ጥያቄዎችን እስቲ እንመልከት። አንደኛው ጥያቄ ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ሲታይ የአንድ ሰው ሕይወት ጀመረ የሚባለው ሲጸነስ ነው ወይስ ሲወለድ? የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ይሖዋ በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ የሚመለከተው የራሱ የሆነ ስብዕና እንዳለው አንድ ግለሰብ አድርጎ ነው ወይስ የሴልና የሕብረ ሕዋስ ስብስብ እንደሆነ አድርጎ? የሚለው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ሁለት ጥያቄዎች ግልጽ መልስ ይሰጣል።

የሙሴ ሕግ፣ የአንድ ሰው ሕይወት ጀመረ የሚባለው ሲወለድ ሳይሆን ከዚያ ቀደም ብሎ እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። ይህን የሚያመለክተው እንዴት ነው? ሕጉ፣ በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ እንዲጨነግፍ የሚያደርግ ሰው በሞት እንደሚቀጣ ይገልጻል። ሕጉ ምን እንደሚል ልብ በል፦ “ሕይወት በሕይወት [ይከፈል]።” * (ዘፀ. 21:22, 23) በመሆኑም በማህፀን ውስጥ ያለ ፅንስ ሕያው ነፍስ ነው። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ጊዜ የማይሽረውን ይህን ሐቅ መገንዘባቸው በአምላክ ዘንድ ከባድ ኃጢአት የሆነውን ውርጃን ከመፈጸም እንዲቆጠቡ ረድቷቸዋል።

በማህፀን ውስጥ ያለ ፅንስ ሕያው ነፍስ እንደሆነ እሙን ነው፤ ይሁንና ይሖዋ ይህን ሕይወት ምን ያህል ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል? ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሕግ በማህፀን ያለን ፅንስ ያጨናገፈ ሰው በሞት መቀጣት እንዳለበት ይናገራል። ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አምላክ በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ ሕይወት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ጥቅሶች፣ ይሖዋ በማህፀን ያለን ፅንስ የራሱ የሆነ ስብዕና እንዳለው አንድ ግለሰብ አድርጎ እንደሚመለከተው ያሳያሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ ዳዊት በመንፈስ ተመርቶ ስለ ይሖዋ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “በእናቴም ማሕፀን ውስጥ አበጃጅተህ ሠራኸኝ። . . . ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ ገና አንዳቸው ወደ መኖር ሳይመጡ፣ በመጽሐፍ ተመዘገቡ።”—መዝ. 139:13-16፤ ኢዮብ 31:14, 15

ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ፣ በማህፀን ውስጥ ያለ ፅንስ የራሱ የሆኑ ባሕርያት እንዳሉትና ወደፊት የተለያዩ ችሎታዎችን ሊያዳብር እንደሚችል ያውቃል። የይስሐቅ ሚስት ርብቃ መንታ ልጆች በፀነሰች ጊዜ ይሖዋ በማህፀኗ ውስጥ ይገፋፉ የነበሩትን ሁለት ወንዶች ልጆች አስመልክቶ አንድ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ይህ ትንቢት፣ ይሖዋ በብዙዎች ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያስከትሉ ባሕርያትን በእነዚህ ልጆች ላይ አስቀድሞ እንደተመለከተ ይጠቁማል።—ዘፍ. 25:22, 23፤ ሮም 9:10-13

የመጥምቁ ዮሐንስ ታሪክም ትኩረት የሚስብ ነው። የወንጌል ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “ኤልሳቤጥ የማርያምን ሰላምታ በሰማች ጊዜ በማህፀኗ ውስጥ ያለው ፅንስ ዘለለ፤ ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተሞላች።” (ሉቃስ 1:41) ሐኪሙ ሉቃስ ይህን ሁኔታ አስመልክቶ ሲጽፍ የተጠቀመበት የግሪክኛ ቃል በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ ወይም የተወለደን ልጅ ሊያመለክት ይችላል። በግርግም ተኝቶ የነበረውን ሕፃኑን ኢየሱስን ለማመልከትም የተጠቀመው በዚሁ ቃል ነው።—ሉቃስ 2:12, 16፤ 18:15

እስከ አሁን ከተመለከትናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦች አንጻር ሲታይ በማህፀን ውስጥ ባለ ፅንስና ገና በተወለደ ሕፃን መካከል ልዩነት አለ ሊባል ይችላል? እንደዚያ ሊባል አይችልም። ይህ ደግሞ ዘመናዊው ሳይንስ ከደረሰባቸው ግኝቶች ጋር ይስማማል። ለምሳሌ ያህል፣ ተመራማሪዎች በማህፀን ውስጥ ያለ ሕፃን ከእናቱ ማህፀን ውጭ የሚከናወኑ ነገሮችን መረዳትና ምላሽ መስጠት እንደሚችል ደርሰውበታል። ስለሆነም ነፍሰ ጡር የሆነች አንዲት እናት በማህፀኗ ውስጥ ካለው ልጅ ጋር የጠበቀ ትስስር ያላት መሆኑ ምንም አያስደንቅም።

ሕፃናት የሚወለዱበት ጊዜ ሊለያይ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት እናት ቀኗ ከመድረሱ በፊት ልትወልድና ከጥቂት ቀናት በኋላ ልጁ ሊሞት ይችላል። ሌላዋ እናት ደግሞ የመውለጃዋ ጊዜ ቢደርስም ሕፃኑ ከመወለዱ በፊት ይሞት ይሆናል። የመጀመሪያው ልጅ በሕይወት ስለተወለደ ብቻ የትንሣኤ ተስፋ ሲኖረው ሁለተኛው ልጅ ግን ሞቶ ስለተወለደ ይህ ተስፋ አይኖረውም ሊባል ይችላል?

ለማጠቃለል ያህል፣ መጽሐፍ ቅዱስ የአንድ ሰው ሕይወት የሚጀምረው ሲፀነስ እንደሆነ በግልጽ ያስተምራል። ከዚህም በላይ ይሖዋ በማህፀን ውስጥ ያለን ፅንስ የራሱ ስብዕና እንዳለው አድርጎ እንደሚመለከተውና ገና ላልተወለደ ሕፃን ትልቅ ግምት እንደሚሰጥ ይገልጻል። አንዳንዶች ከመወለዱ በፊት የሚሞት ሕፃን የትንሣኤ ተስፋ አይኖረውም ብሎ መደምደም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት ከእነዚህ እውነቶች ጋር እንደሚጋጭ ይሰማቸዋል። እንዲያውም እንዲህ ብሎ ማሰብ ከውርጃ ጋር በተያያዘ በእነዚህ እውነቶች ላይ በተመሠረተው ቅዱስ ጽሑፋዊ አቋማችን ላይ ጥያቄ እንደሚያስነሳ ሊሰማቸው ይችላል።

ከዚህ ቀደም ይህ መጽሔት፣ ከመወለዳቸው በፊት የሞቱ ልጆች ትንሣኤ የማግኘታቸውን ነገር አጠራጣሪ የሚያደርጉ የሚመስሉ አንዳንድ ጥያቄዎችን አንስቶ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ገና የተፀነሰ ልጅ ቢጨነግፍ አምላክ በገነት ውስጥ ያንን ልጅ በአንዲት ሴት ማህፀን መልሶ ያስቀምጣል?’ የሚል ጥያቄ ቀርቦ ነበር። ይሁን እንጂ የበላይ አካሉ ተጨማሪ ምርምር ካደረገ እንዲሁም በጉዳዩ ላይ ከጸለየና ካሰላሰለ በኋላ እንዲህ ያሉ ሐሳቦች በትንሣኤ ተስፋ ላይ የሚያመጡት ለውጥ የለም የሚል መደምደሚያ ላይ ደርሷል። ኢየሱስ “በአምላክ ዘንድ ሁሉ ነገር ይቻላል” ብሏል። (ማር. 10:27) በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተፈጸመው ነገርም የዚህን አባባል እውነተኝነት ያረጋግጣል። የኢየሱስ ሕይወት ወደ አንዲት ድንግል ማህፀን እንዲዛወር ተደርጓል፤ ይህ ደግሞ ከሰው አመለካከት አንጻር ፈጽሞ የሚቻል ነገር አይደለም።

ታዲያ ይህ ሲባል መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከመወለዳቸው በፊት የሞቱ ልጆች በሙሉ ትንሣኤ እንደሚያገኙ ያስተምራል ማለት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ እንደማይሰጥ ልብ ማለት ይገባናል፤ ስለሆነም ሰዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ድርቅ ያለ አቋም ለመያዝ የሚያስችል ምንም መሠረት የላቸውም። ይህ ርዕሰ ጉዳይ ደግሞ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጥያቄዎችን ሊያስነሳ ይችላል። በመሆኑም ግምታዊ አስተሳሰብ ከመሰንዘር መቆጠብ የተሻለ ነው። ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ ይህ ጉዳይ በፍቅራዊ ደግነቱና በምሕረቱ ተወዳዳሪ በሌለው በይሖዋ አምላክ እጅ ላይ ያለ ነው። (መዝ. 86:15) ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን በትንሣኤ አማካኝነት ወደ ሕይወት የመመለስ ልባዊ ፍላጎት እንዳለው ምንም አያጠያይቅም። (ኢዮብ 14:14, 15) ምንጊዜም ቢሆን የሚያደርገው ትክክል የሆነውን እንደሆነ መተማመን እንችላለን። ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ልጁ ‘የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርስ’ በማድረግ በዚህ ክፉ ሥርዓት በሕይወታችን ውስጥ የደረሱብንን ቅስም የሚሰብሩ በርካታ ችግሮች ያስወግድልናል።—1 ዮሐ. 3:8

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.6 አንዳንድ ጊዜ ይህ ጥቅስ፣ አንድ ሰው በሞት የሚቀጣው እናትየው ከሞተች ብቻ እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ ይተረጎማል። ይሁንና የዕብራይስጡ በኩረ ጽሑፍ፣ እዚህ ጥቅስ ላይ ሕጉ እየተናገረ ያለው በእናትየውም ሆነ በማህፀን ውስጥ ባለው ፅንስ ላይ ሞት ስለሚያስከትል ጉዳት እንደሆነ ያሳያል።

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የደረሱብንን ቅስም የሚሰብሩ ችግሮች በሙሉ ያስወግድልናል