በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘አንድ ባለ ሥልጣን አንድ ነገር እንድታደርግ ቢያስገድድህስ?’

‘አንድ ባለ ሥልጣን አንድ ነገር እንድታደርግ ቢያስገድድህስ?’

‘አንድ ባለ ሥልጣን አንድ ነገር እንድታደርግ ቢያስገድድህስ?’

 “ስማ አንተ! የያዝከውን ሥራ አሁኑኑ አቁምና ይህን እቃ ተሸከምልኝ።” በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ በሥራ የተጠመደ አይሁዳዊ ከአንድ ሮማዊ ወታደር ይህ ጥያቄ ቢቀርብለት ምን ይሰማዋል ብለህ ትገምታለህ? ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ “አንድ ሰው [“አንድ ባለ ሥልጣን፣” NW] አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ” በማለት አሳስቧል። (ማቴዎስ 5:41) ኢየሱስን ሲያዳምጡ የነበሩ ሰዎች ይህን ምክር እንዴት ተረዱት? በዛሬው ጊዜ ለምንገኘውስ ምን ትምህርት ይዟል?

መልሱን ለማግኘት በጥንት ዘመን ሰዎች ተጥሎባቸው ስለነበረው የግዴታ አገልግሎት ማወቅ ያስፈልገናል። በኢየሱስ ዘመን የእስራኤል ነዋሪዎች እንዲህ ያለ አገልግሎት መስጠታቸው የተለመደ ነበር።

የግዴታ አገልግሎት

በመካከለኛው ምሥራቅ ከ18ኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ የግዴታ አገልግሎት ይሰጥ እንደነበር ማስረጃዎች ያሳያሉ። ኧለለክ ከተባለች ጥንታዊት የሶርያ ከተማ የተገኙት አስተዳደራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ጽሑፎች እንደሚያመለክቱት ግለሰቦችን ያለ ክፍያ እንዲያገለግሉ በመንግሥት የተመለመሉ ቡድኖች ነበሩ። በሶርያ የባሕር ጠረፍ ላይ በምትገኘው በኡጋሪት የሚኖሩ ጭሰኞችም እንዲሁ ንጉሡ ነፃነት ካልሰጣቸው በስተቀር የግዳጅ ሥራ ይሠሩ ነበር።

ብዙውን ጊዜ ድል የተደረጉ ወይም ግብር የተጣለባቸው ሕዝቦች የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ ይደረጉ ነበር። ግብጻውያን አስገባሪዎች እስራኤላውያንን አስገድደው ባሮቻቸው በማድረግ ጡብ ያሠሯቸው ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር ይኖሩ የነበሩ ከነዓናውያንን አስገድደው የጉልበት ሥራ ያሠሯቸው የነበረ ሲሆን ዳዊትና ሰሎሞንም ተመሳሳይ ሁኔታ ፈጽመዋል።—ዘፀአት 1:13, 14፤ 2 ሳሙኤል 12:31፤ 1 ነገሥት 9:20, 21

ሳሙኤል እስራኤላውያን ንጉሥ እንዲያነግሥላቸው በጠየቁት ጊዜ ንጉሡ ተገዢዎቹን ሰረገለኞችና ፈረሰኞች፣ አራሾችና አጫጆች እንዲሆኑ እንዲሁም የጦር መሣሪያና ሌሎች ነገሮችን እንዲሠሩ እንደሚያደርጋቸው ገልጾላቸዋል። (1 ሳሙኤል 8:4-17) ይሁን እንጂ የይሖዋ ቤተ መቅደስ በተሠራበት ወቅት እስራኤላውያን ያልሆኑ ሌሎች ሕዝቦች አድካሚ የጉልበት ሥራ እንዲሠሩ የተገደዱ ቢሆንም “ሰሎሞን ከእስራኤላውያን ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ወታደሮቹ፣ ሹማም[ን]ቱ፣ የጦር አለቆቹ፣ ሻምበሎቹ፣ ባልደራሶቹ ነበሩ።”—1 ነገሥት 9:22

አንደኛ ነገሥት 5:13, 14 በግንባታ ሥራው ላይ የተሰማሩ እስራኤላውያንን በተመለከተ እንዲህ ይላል:-“ንጉሥ ሰሎሞን ከመላው እስራኤል የጕልበት ሠራተኞችን መለመለ፤ ቊጥራቸውም ሠላሳ ሺህ ነበር። እነዚህንም አንድ ወር በሊባኖስ እንዲሠሩ፣ ሁለት ወር በቤታቸው እንዲያርፉ በማድረግ፣ ዐሥር ዐሥር ሺውን ወር ተራ አግብቶ ላካቸው።” አንድ ምሑር “የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት ለሚያከናውኑት የሕንጻ ግንባታና የራሳቸውን መሬት ለማሳረስ ገንዘብ እንዳይከፍሉ ሰዎችን በግዳጅ ያሠሩ እንደነበር ምንም አያጠራጥርም” ብለዋል።

ሰሎሞን በተገዢዎቹ ላይ ከባድ ቀንበር ጭኖባቸው ነበር። ሮብዓም ሸክሙን ይበልጥ እንደሚያከብድባቸው በዛተ ጊዜ እስራኤላውያን በሙሉ ዓምጸው የጉልበት ሠራተኞች አለቃ ተደርጎ የተሾመውን ባለ ሥልጣን ወግረው ገደሉት፤ ይህም ቀንበሩ ምን ያህል ከብዷቸው እንደነበር ያሳያል። (1 ነገሥት 12:12-18) ይሁን እንጂ የግዳጅ ሥራው አልቀረላቸውም ነበር። የሮብዓም የልጅ ልጅ የሆነው አሳ፣ ጌባና ምጽጳ የሚባሉትን ከተሞች ለመገንባት ከይሁዳ ‘አንድም ሰው ሳይቀር’ እንዲወጣ አዝዞ ነበር።—1 ነገሥት 15:22

በሮም አገዛዝ ሥር

የኢየሱስ የተራራ ስብከት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አይሁዳውያን ‘አንድ ነገር እንዲያደርጉ መገደዳቸው’ የተለመደ እንደነበር ያሳያል። በስብከቱ ላይ በተገለጸው አንድ ሐሳብ ውስጥ፣ አጋሬቮ የሚለው ግሪክኛ ቃል ትርጉም የሚገኝ ሲሆን ቃሉ ከፋርስ መልእክተኞች ተግባር ጋር በተያያዘ ይጠቀስ ነበር። እነዚህ መልእክተኞች ሕዝባዊ ጉዳይ ለማከናወን ሰዎችን አስገድዶ የማሠራትና ፈረሶችን፣ መርከቦችን ወይም ሌላ ማንኛውንም ነገር በግድ ወስደው የመጠቀም ሥልጣን ነበራቸው።

እስራኤል በኢየሱስ ዘመን ከላይ ከተጠቀሰው ጋር የሚመሳሰል አሠራር በነበራቸው ሮማውያን ቁጥጥር ሥር ነበረች። በምሥራቃዊው የሮም ግዛት ውስጥ የነበሩ ነዋሪዎች የተለመደውን ቀረጥ ከመክፈል በተጨማሪ በቋሚነት ወይም ደግሞ አልፎ አልፎ የግዳጅ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸው ነበር። ሕዝቡ እነዚህን የመሰሉ ሥራዎች መሥራት በጣም ይጠላ ነበር። ከዚህም በላይ ሕገወጥ በሆነ መንገድ እንስሳትን፣ ባለጋሪዎችን ወይም ሰረገሎችን በመቀማት ከቦታ ቦታ መጓጓዝ የተለመደ ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ማይክል ረስቶፍሲፍ እንደገለጹት አስተዳዳሪዎቹ “[አሠራሩን] ለመቆጣጠርና ደንብ ለማውጣት ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፤ ሁኔታው በቀጠለ መጠን ደግሞ መጥፎ ውጤቶችን እንደሚያስከትል የተረጋገጠ ነው። ሥልጣናቸውን ለጭካኔ ተግባራቸው ማራመጃ የሚጠቀሙ ሰዎችንና የጉልበት ሥራ በማሠራት ይደረግ የነበረውን ሥር የሰደደ ጭቆና ለመቆጣጠር ከልባቸው ይጣጣሩ የነበሩ ሹማምንት በርካታ ዐዋጆችን ያውጁ ነበር። . . . ይሁን እንጂ አሠራሩ ከጭቆና ነፃ ሊሆን አልቻለም።”

አንድ ግሪካዊ ምሑር “ማንኛውም ሰው የአንዱን ወታደር ጓዝ የተወሰነ መንገድ ድረስ እንዲሸከምና ሮማውያን ያዘዙትን ማንኛውንም አገልግሎት እንዲፈጽም ሊገደድ ይችላል” ብለዋል። ኢየሱስ የተሰቀለበትን የመከራ እንጨት እንዲሸከም ‘የተገደደው’ ስምዖን የተባለ የቀሬና ሰው ያጋጠመው ይኸው ነበር።—ማቴዎስ 27:32

በረቢዎች የተዘጋጁ ጽሑፎች በሕዝብ ዘንድ ይጠላ ስለነበረው ስለዚህ አሠራር ይጠቅሳሉ። ለምሳሌ አንድ ረቢ ባርሰነት (የአደስ እንጨት) ወደ ቤተ መንግሥት እንዲያጓጉዝ ተገድዶ ነበር። የቀን ሠራተኞች ከቀጣሪዎቻቸው ተነጥቀው ሊወሰዱና ሌላ ሥራ ሊሰጣቸው ይችላል፤ ደመወዝ የሚከፍሏቸው ግን የቀጠሯቸው ሰዎች ናቸው። የጭነት እንስሶች ወይም በሬዎች ከባለቤቶቻቸው ተነጥቀው ሊወሰዱ ይችሉ ነበር። ምናልባት ቢመለሱ እንኳን ከመጎዳታቸው የተነሳ በማያገለግሉበት ሁኔታ ላይ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚያን ጊዜ የነበሩ ሰዎች ንብረትም ሆነ እንስሳ ሲወሰድባቸው እንደተወረሱ የሚቆጥሩት ለምን እንደሆነ ከዚህ ማየት ትችላለህ። እንዲያውም አይሁዳውያን “አጋሪያ ልክ እንደ ሞት ነው” የሚል ምሳሌያዊ አባባል አላቸው። አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዳሉት “በሕግ በተፈቀደው መሠረት በጭነት እንስሳት ፋንታ የእርሻ በሬዎች መወሰዳቸው አንድ መንደር ችግር ላይ እንዲወድቅ ሊያደርግ ይችላል።”

ሕዝቡ ከሚደርስበት ግፍና በማናለብኝነት ከሚፈጸምበት በደል የተነሳ የግዳጅ ሥራዎችን መሥራት ምን ያህል ይጠላ እንደነበር መገመት ትችላለህ። አይሁዳውያን ለሚገዟቸው የአሕዛብ ኃይሎች የታመቀ ጥላቻ ስለነበራቸው ለውርደት የሚዳርጋቸውን እንዲህ ያለ የግዳጅ ሥራ በእጅጉ ይጠሉት ነበር። የአገሪቱ ነዋሪዎች ለምን ያህል ርቀት እንዲሸከሙ ይገደዱ እንደነበር የሚገልጽ ሕግ አሁን አናገኝም። አብዛኞቹ ግን ሕጉ ከሚጠይቅባቸው አንዲት እርምጃ እንኳን አልፈው ለመሄድ ፈቃደኞች አልነበሩ ይሆናል።

ሆኖም ኢየሱስ “አንድ ሰው [“አንድ ባለ ሥልጣን፣” NW] አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል የሚያህል ርቀት እንድትሄድ ቢያስገድድህ ዕጥፉን መንገድ አብረኸው ሂድ” በማለት የተናገረው እንዲህ ያለውን ሕግ በአእምሮው በመያዝ ነበር። (ማቴዎስ 5:41) አንዳንዶች ኢየሱስ ያለውን ካዳመጡ በኋላ ፍርደ ገምድል ነው ብለው አስበው መሆን አለበት። ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር?

ክርስቲያኖች ምን ማድረግ ይገባቸዋል?

በቀላል አነጋገር ኢየሱስ አድማጮቹ አንድ ባለ ሥልጣን ሕጋዊ በሆነ መንገድ አንድ ዓይነት ሥራ እንዲያከናውኑ ካስገደዳቸው በፈቃደኝነትና ምንም ቅር ሳይላቸው ማከናወን እንዳለባቸው እየነገራቸው ነበር። ስለዚህ “የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር” የመስጠት ግዴታቸውን ችላ ሳይሉ “የቄሳርን ለቄሳር” መክፈል ይኖርባቸዋል።—ማርቆስ 12:17 a

ከዚህም በላይ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ክርስቲያኖችን አጥብቆ አሳስቧል:- “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምንት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ፣ በባለ ሥልጣን ላይ የሚያምፅ በእግዚአብሔር ሥርዐት ላይ ማመፁ ነው፤ . . . ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ምክንያቱም ሰይፉን በከንቱ አልታጠቀም።”—ሮሜ 13:1-4

ኢየሱስና ጳውሎስ ነገሥታት ወይም አስተዳዳሪዎች፣ የሚፈለግባቸውን የማይፈጽሙ ተገዢዎቻቸውን የመቅጣት መብት እንዳላቸው አረጋግጠዋል። ቅጣቱ ምን ሊሆን ይችላል? ከክርስቶስ ልደት በኋላ በአንደኛውና በሁለተኛው ክፍለ ዘመን የኖረው ኤፒክቲተስ የተባለ ግሪካዊ ፈላስፋ መልስ ይሰጠናል:- “ያልታሰበ አጋጣሚ ተከስቶ አንድ ወታደር ውርንጭላህን ቢወስድብህ ተውለት። እንዳትዋረድና ጨርሶ አህያህን እንዳታጣ አትቃወመው ወይም አታጉረምርም።”

ይሁን እንጂ በጥንት ጊዜም ሆነ በዘመናችን ያሉ ክርስቲያኖች መንግሥት የሚጠብቅባቸውን መፈጸማቸው ኅሊናቸውን እንደሚያቆሽሽባቸው የተሰማቸው ጊዜ አለ። ይህም አንዳንድ ከባድ ችግሮች አስከትሏል። ጥቂት ክርስቲያኖች ሞት ተፈርዶባቸዋል። ሌሎች ደግሞ የገለልተኝነት አቋማቸውን እንደሚያስጥሷቸው ባሰቧቸው ድርጊቶች ውስጥ ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት በርካታ ዓመታት በእስር ቤት አሳልፈዋል። (ኢሳይያስ 2:4፤ ዮሐንስ 17:16፤ 18:36) በሌላ ወቅት ደግሞ ክርስቲያኖች የሚፈለግባቸውን መፈጸም እንዳለባቸው ተሰምቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ክርስቲያኖች በሕዝብ አስተዳዳሪዎች አዛዥነት ለኅብረተሰቡ የሚጠቅም ከውትድርና ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው ሕዝባዊ አገልግሎት ቢፈጽሙ ኅሊናቸውን እንደማይረብሻቸው ይሰማቸዋል። ይህም አረጋውያንን ወይም የአካል ጉዳተኞችን መርዳት፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ውስጥ ማገልገል፣ የባሕር ዳርቻዎችን ማጽዳት፣ እንዲሁም በመናፈሻዎች፣ በጫካዎች ወይም በቤተ መጻሕፍት ውስጥ እና በመሳሰሉት ቦታዎች መሥራት ሊሆን ይችላል።

ሁኔታዎች ከአገር አገር እንደሚለያዩ ምንም ጥርጥር የለውም። ስለዚህ እያንዳንዱ ክርስቲያን የሚፈለግበትን ለመፈጸም ወይም ላለመፈጸም ውሳኔ በሚያደርግበት ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ኅሊናው የሚለውን ማዳመጥ ይገባዋል።

እጥፉን መንገድ መጓዝ

ሕጋዊ በሆነ መንገድ የቀረቡ ትእዛዞችን መፈጸምን በተመለከተ ኢየሱስ ያስተማረው መሠረታዊ ሥርዓት መንግሥታዊ ለሆኑ ጉዳዮች ብቻ ሳይሆን ለዕለት ተዕለት የሰዎች ግንኙነትም የሚጠቅም መመሪያ ይዟል። ለምሳሌ በአንተ ላይ ሥልጣን ያለው ሰው የአምላክን ሕግ የማያስጥስ ሆኖም አንተ መሥራት የማትወደውን አንድ ነገር እንድትፈጽም ያዝህ ይሆናል። በዚህን ጊዜ ምን ይሰማሃል? ጊዜህንና ጉልበትህን የሚያባክን አላስፈላጊ ትእዛዝ እንደታዘዝክ ተሰምቶህ ትበሳጭ ይሆናል። ይህም እንድትጠላ ያደርግህ ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ቅር እያለህ ሥራውን የምትፈጽም ከሆነ ውስጣዊ ሰላምህን ልታጣ ትችላለህ። ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው? ኢየሱስ እንዳዘዘው እጥፉን መንገድ ተጓዝ። የተጠየቅከውን ብቻ ሳይሆን ከዚያም በላይ ጨምረህ ፈጽም። ሥራውን በፈቃደኝነት አከናውን። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ከያዝክ እንደተበደልክ ሆኖ አይሰማህም፤ እንዲያውም የራስህ አዛዥ ራስህ እንደሆንክ ስለሚሰማህ ደስ ይልሃል።

አንድ ደራሲ እንዲህ ብለዋል:- “በርካታ ሰዎች መላ ሕይወታቸውን ሌሎች እንዲሠሩ የሚያስገድዷቸውን ነገሮች ብቻ በመፈጸም ያሳልፋሉ። እነዚህ ሰዎች በኑሯቸው ካለመደሰታቸውም በላይ ሁልጊዜ እንደታከቱ ነው። ሌሎች ደግሞ ከግዴታቸው አልፈው በመሄድ ይሠራሉ እንዲሁም ሌሎችን በፈቃደኝነት ያገለግላሉ።” ብዙውን ጊዜ እያንዳንዱ ሰው የግዱን አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል ብቻ ወይም የዚህን እጥፍ እንዲሄድ ምርጫ ይቀርብለታል ለማለት ይቻላል። ሰውየው አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል ብቻ ከሄደ መብቱ እንዲከበርለት እየፈለገ ሊሆን ይችላል። እጥፉን ከሄደ ደግሞ አስደሳች የሕይወት ተሞክሮ ያገኛል። አንተስ እንደ የትኛው ሰው ነህ? ሥራህን እንደ ግዴታ ወይም ማድረግ እንዳለብህ ብቻ ሳይሆን በፍላጎትህ እንደምታከናውነው አድርገህ የምትመለከተው ከሆነ ይበልጥ ደስተኛና ውጤታማ መሆን ትችላለህ።

በሥልጣን ላይ ያለኸው አንተ ብትሆንስ ምን ታደርጋለህ? ሥልጣንን ተጠቅሞ ሌሎችን ያለፈቃዳቸው አንድ ነገር እንዲያከናውኑ ማስገደድ ፍቅራዊ እንዲሁም ክርስቲያናዊ ባሕርይ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። “የአሕዛብ ገዢዎች በሕዝባቸው ላይ ጌቶች እንደሚሆኑ፣ ባለ ሥልጣኖቻቸውም በኀይል እንደሚገዟቸው” ኢየሱስ ተናግሯል። ይሁን እንጂ እንዲህ ማድረግ ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ አይደለም። (ማቴዎስ 20:25, 26) ጥብቅና ኮስታራ መሆን ውጤት ሊያስገኝ ይችል ይሆናል፤ ሆኖም ትእዛዛቸውን በደግነትና በትክክለኛው መንገድ በሚያቀርቡ ሰዎች እንዲሁም ሥራቸውን በትሕትናና በደስታ በሚፈጽሙ ሰዎች መካከል በጣም ጥሩ ግንኙነት ይመሠረታል! አዎን፣ አንድ ኪሎ ሜትር ተኩል ብቻ ሳይሆን እጥፉን ለመሄድ መዘጋጀት የተባረከ ሕይወት እንድትመራ ሊያደርግህ ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ክርስቲያኖች ‘የቄሳርን ለቄሳር፣ የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ይስጡ’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በይበልጥ ለመረዳት የግንቦት 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ እትም ከገጽ 15-20⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ጥንት ይሰጥ የነበረ የግዳጅ አገልግሎት

ጥንት የነበረውን የሥልጣን ብልግና ለመቆጣጠር ከወጡት ደንቦች መገንዘብ እንደሚቻለው ብዙውን ጊዜ በግዳጅ ሥራ ሰበብ ተገቢ ያልሆነ አገልግሎት እንዲሰጥ ይጠየቅ ነበር ። የግብጹ ዳግማዊ ቶሎሚ ዩዌርጀቲዝ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ118 ሹማምንቱ “ማንኛውንም የአገሪቱን ነዋሪ የግላቸውን ሥራ እንዲሠራ ማስገደድም ሆነ ከብቶቹን ለራሳቸው መጠቀሚያ ብለው መጠየቅ (አጋሬቮ) አይኖርባቸውም” የሚል ሕግ ደንግጎ ነበር። በተጨማሪም “ማንም ሰው ቢሆን በምንም ምክንያት አሳብቦ ለገዛ ጥቅሙ ጀልባዎችን ለመውሰድ . . . መጠየቅ የለበትም” የሚል ሕግ ወጥቶ ነበር። በግብጽ ባለው ታላቁ የበረሃ ገነት ቤተ መቅደስ ውስጥ የተገኘና በ49 ከክርስቶስ ልደት በኋላ እንደተጻፈ የሚገልጽ አንድ ጽሑፍ እንደሚናገረው ቨርጂሊየስ ከፒቶ የተባለ ሮማዊ ባለ ሥልጣን፣ ወታደሮች የሰዎችን ንብረት ሕገወጥ በሆነ መንገድ ለመጠቀም እንደሚጠይቁ ካረጋገጠ በኋላ “ማንም ሰው እኔ የጽሑፍ ፈቃድ ካልሰጠሁት በስተቀር ምንም ነገር . . . መውሰድም ሆነ መጠየቅ አይችልም” በማለት አስታውቆ ነበር።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቀሬናው ስምዖን የግዳጅ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ ነበር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በክርስቲያናዊ አቋማቸው በመጽናታቸው ምክንያት ታስረዋል