በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንተ ራስህ የተመለከትካቸው ተአምራት

አንተ ራስህ የተመለከትካቸው ተአምራት

አንተ ራስህ የተመለከትካቸው ተአምራት

“ተአምር” የሚለው ቃል “ያልተለመደና በዓይነቱ ልዩ የሆነ ነገር፣ ክስተት ወይም ክንውን” የሚል ትርጉም አለው። ሁላችንም ብንሆን ያለ መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት የተፈጸሙ የዚህ ዓይነት ተአምራቶችን ተመልክተናል።

የሰው ልጆች ስለ ተፈጥሮ ሕግጋት ያላቸው እውቀት እያደገ በመሄዱ በአንድ ወቅት ፈጽሞ ሊደረጉ የማይችሉ ይመስሉ የነበሩ ነገሮችን ለማከናወን ችለዋል። ለምሳሌ ያህል በጊዜያችን በጣም የተለመዱ የሆኑት እንደ ኮምፒውተር፣ ቴሌቪዥን፣ የጠፈር ጉዞና እነዚህን የመሳሰሉ ቴክኖሎጂዎች ከመቶ ዓመት በፊት ጨርሶ የማይታሰቡ ነገሮች ነበሩ።

አንዳንድ ሳይንቲስቶች ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ያላቸው ሳይንሳዊ እውቀት በጣም ውስን እንደሆነ በመገንዘብ አንድን ነገር ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው ብለው መደምደም እንደማይችሉ አምነዋል። ግፋ ቢል ሊሆን መቻሉ ያጠራጥራል ቢሉ ነው። በዚህም ምክንያት ወደፊት “ከተአምራት” ተርታ ሊፈረጁ የሚችሉ ሳይንሳዊ ግኝቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ አምነው ይቀበላሉ።

“ተአምር” ለሚለው ቃል የተሰጠውን “ከሰው በላይ በሆኑ ኃይሎች ይፈጸማሉ የሚባሉ” ነገሮች የሚለውን የመጀመሪያ ፍቺ ብንወስድ እንኳን እያንዳንዳችን የዚህ ዓይነት ተአምር አይተናል ማለት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ “ከሰው በላይ የሆነ ኃይል” ያለው ፈጣሪ የእጅ ሥራ የሆኑትን ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን እንመለከታለን። ከዚህም በላይ የሰው አካል ወይም አእምሮ እንዴት እንደሚሠራ ወይም አንድ ሽል በማሕፀን ውስጥ እንዴት እንደሚያድግ በዝርዝር ማብራራት የሚችል ማን አለ? ዘ ቦዲ ማሺን የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “በማዕከላዊው የነርቭ ሥርዓት የሚመራው የሰው አካል የተወሳሰቡ የስሜት ሕዋሳት ያሉት መሣሪያ፣ ራሱን በራሱ መቆጣጠር የሚችል ተንቀሳቃሽ ሞተር እንዲሁም አምሳያውን መፍጠር የሚችል ኮምፒውተር ሲሆን በጣም አስገራሚና ሙሉ በሙሉ ለመረዳት የሚከብድ ፍጥረት ነው።” አምላክ ይህን “የሰው አካል” ሲፈጥር ለዘላለም በአድናቆት እንድንደመም የሚያደርገን ተአምር ፈጽሟል። ምንም እንኳን ተአምራት መሆናቸውን ልብ ባትለውም ሌሎችም በርካታ የተመለከትካቸው ተአምራቶች አሉ።

መጽሐፍ ከተአምራት ተርታ ሊመደብ ይችላል?

የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በስፋት የተሰራጨ መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ተአምር ሊቆጠር ይችላል? የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲ አንድ “ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ኃይል ነው” ለማለት እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች የተጻፈ መጽሐፍ መሆኑ አይካድም፤ ሆኖም እነዚህ ሰዎች የራሳቸውን ሳይሆን የአምላክን ሐሳብ እንደጻፉ ተናግረዋል። (2 ሳሙኤል 23:1, 2፤ 2 ጴጥሮስ 1:20, 21) እስቲ አስበው! እነዚህ 40 የሚያህሉ ሰዎች 1,600 ዓመታት በሚሸፍን የጊዜ ርዝመት ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት የኖሩ ናቸው። የተለያየ አኗኗር የነበራቸው ሲሆን ከእነርሱ መካከል እረኞች፣ ወታደሮች፣ ዓሣ አጥማጆች፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ሐኪሞች እንዲሁም ካህናትና ነገሥታት ይገኙበት ነበር። እንዲያም ሆኖ ግን ወጥነት ያለው ብሎም ሐቀኛና ትክክለኛ የሆነ የተስፋ መልእክት ለማስተላለፍ ችለዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ከመረመሩ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው ‘የሰው ቃል ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል’ መሆኑን ተቀብለዋል። (1 ተሰሎንቄ 2:13) ባለፉት ዓመታት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ ይጋጫል ለማለት የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች ከአጠቃላይ መልእክቱ ጋር እንደሚስማሙ የሚያሳዩ ሐሳቦችን በጽሑፎቻቸው ላይ ሲያሳትሙ ቆይተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እርስ በርሱ የሚስማማ መሆኑ በራሱ አምላክ እንዳስጻፈው የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። a

የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል ከፍተኛ የማጥፋት ዘመቻ የተካሄደበት መጽሐፍ የለም። እንዲያም ሆኖ ግን እስካሁን ድረስ ያለ ሲሆን ቢያንስ ከ2,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች በከፊል ታትሟል። ሳይጠፋና ይዘቱ ሳይበረዝ እስካሁን መቆየቱ የአምላክ እጅ እንዳለበት ያሳያል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ ተአምር ሊባል ይችላል!

“ሕያውና የሚሠራ” ተአምር

በጥንት ጊዜያት ይደረጉ የነበሩት እንደ ፈውስና ትንሣኤ ያሉት ተአምራት አሁን አይፈጸሙም። ሆኖም ወደፊት በሚመጣው የአምላክ አዲስ ዓለም እነዚህን የመሰሉ ተአምራቶች ዓለም አቀፋዊ በሆነ መልኩ እንደሚፈጸሙ ሙሉ እምነት ማሳደር እንችላለን። እነዚህ ተአምራት ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡልን ሲሆን አሁን ባለን የማስተዋል ችሎታ ልንረዳው ከምንችለው በላይ ብዙ ነገሮች ያደርጉልናል።

ራሱ ተአምር ሊባል የሚችለው መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ባሕርያቸውን ለውጠው መልካም ሰው እንዲሆኑ በማነሳሳት በጊዜያችንም ከተአምራት የማይተናነስ ነገር ማከናወን ይችላል። (በገጽ 8 ላይ በሚገኘው “የአምላክ ቃል ያለው ኃይል” በሚለው ሣጥን ውስጥ ያለውን ምሳሌ ተመልከት።) ዕብራውያን 4:12 እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነውና፤ በሁለት በኩል ስለት ካለው ሰይፍ ሁሉ ይልቅ ስለታም ነው፤ ነፍስንና መንፈስን ጅማትንና ቅልጥምን እስኪለያይ ድረስ ዘልቆ ይወጋል፤ የልብንም ሐሳብና ምኞት ይመረምራል።” አዎን፣ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ከስድስት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች አኗኗራቸውን በመለወጥ ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲመሩና አስደሳች የወደፊት ተስፋ እንዲኖራቸው በመርዳት ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።

አንተም በሕይወትህ ውስጥ ከተአምራት ተርታ የሚመደብ ለውጥ ለማድረግ እንድትችል ለምን መጽሐፍ ቅዱስን አትመረምርም?

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ቅዱሳን ጽሑፎች እርስ በርስ ይጋጫሉ ለማለት ሰዎች የሚጠቅሷቸው ጥቅሶች እንዴት እንደሚስማሙ ለመመርመር ከፈለግህ በይሖዋ ምሥክሮች በታተመው መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 7 ላይ በርካታ ምሳሌዎች ቀርበዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ኢየሱስ ጎኑን በጦር ሲወጉት በሕይወት ነበር ወይስ ሞቷል?

በዮሐንስ 19:33ና 34 ላይ “ከወታደሮቹ አንዱ የኢየሱስን ጐን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውሃ ፈሰሰ” ይላል። በጥቅሱ መሠረት ኢየሱስ በዚህ ወቅት ሞቶ ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በማቴዎስ 27:49, 50 ላይ ወታደሩ ጎኑን በጦር ሲወጋው ኢየሱስ በሕይወት እንደነበር የሚያሳይ ሐሳብ ይዘዋል። ይህ ልዩነት እንዴት ሊፈጠር ቻለ?

የሙሴ ሕግ በስቅላት የተቀጡ ወንጀለኞች አስከሬናቸው በእንጨት ላይ ተሰቅሎ እንዳያድር ይከለክላል። (ዘዳግም 21:22, 23) በመሆኑም በኢየሱስ ዘመን አንድ በእንጨት ላይ የተሰቀለ ወንጀለኛ እስከ ምሽት ድረስ ካልሞተ እግሮቹን በመስበር ሞቱን ማፋጠን የተለመደ ነበር። እግሮቹ ከተሰበሩ ቀጥ ብሎ መቆም ስለማይችል እንደልብ መተንፈስ ያቅተዋል። ወታደሮቹ በኢየሱስ ግራና ቀኝ የተሰቀሉትን ወንጀለኞች እግር ሰብረው የእርሱን ግን አለመስበራቸው በወቅቱ ኢየሱስ ሞቶ እንደነበር ይጠቁማል። አንደኛው ወታደር ጎኑን የወጋው ሳይሞት ቀርቶ በኋላ ላይ ትንሣኤ አግኝቶ ተነሳ የሚል የሐሰት ወሬ እንዳይስፋፋ በመፍራት መሞቱን ለማረጋገጥ ሊሆን ይችላል።

በማቴዎስ 27:49, 50 [NW] ላይ ደግሞ ጥቅሱ ድርጊቶቹ የተፈጸሙበትን ቅደም ተከተል የሚያስቀምጠው ለየት ባለ መንገድ ነው። እንዲህ ይላል:- “አንድ ሰውም ጦር ወስዶ ጎኑን ወጋው፣ ወዲያውም ደምና ውኃ ፈሰሰ። ኢየሱስ እንደ ገና ከፍ ባለ ድምፅ ጮኸ፤ መንፈሱንም አሳልፎ ሰጠ።” ይሁን እንጂ በሰያፍ የተጻፈው ዓረፍተ ነገር የሚገኘው በሁሉም ጥንታዊ የቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ላይ አይደለም። በርካታ ምሑራን ይህ ዓረፍተ ነገር ከጊዜ በኋላ ከዮሐንስ ወንጌል ተወስዶ ያለቦታው የተጨመረ ሐሳብ እንደሆነ ይሰማቸዋል። በመሆኑም በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በቅንፍ ያስቀምጡታል አሊያም በግርጌ ማስታወሻ መልክ ማብራሪያ ያክሉበታል፤ አንዳንዶቹም ከናካቴው ያወጡታል።

የአዲሲቱ ዓለም ትርጉምን ለማዘጋጀት በዋነኝነት ያገለገለው በዌስትኮትና ሆርት የተዘጋጀው የአዲስ ኪዳን የግሪክኛ ቃላት ስብስብ ዓረፍተ ነገሩን በድርብ ቅንፎች ውስጥ ያስቀምጠዋል። ይኸው ጽሑፍ ዓረፍተ ነገሩ “በገልባጮች የተጨመረ ነው የሚለው መላ ምት በጣም አሳማኝ ይመስላል” የሚል ማስታወሻም አክሎ ይዟል።

በመሆኑም ዮሐንስ 19:33, 34 ትክክል እንደሆነና ሮማዊው ወታደር በጦር ሲወጋው ኢየሱስ ሞቶ እንደነበር ማስረጃዎቹ ያረጋግጣሉ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የአምላክ ቃል ያለው ኃይል

ዴትሌፍ ገና በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ሳለ ወላጆቹ በመፋታታቸው አደገኛ ዕጾችን መውሰድ፣ አልኮል መጠጣትና ሄቪ ሜታል ሙዚቃዎችን ማዳመጥ ጀመረ። b ከዚያም በተለምዶ ስኪንሄድ ተብሎ የሚጠራ የወጣት ወሮበሎች ቡድን አባል የሆነ ሲሆን በዓመጸኝነቱ የተነሳ ብዙ ጊዜ ከፖሊሶች ጋር ይጋጭ ነበር።

በ1992 በደቡብ ምሥራቅ ጀርመን በሚገኝ አንድ ምግብ ቤት ውስጥ 60 በሚያክሉ የስኪንሄድ ቡድን አባላትና 35 በሚሆኑ የሮክ ሙዚቃ አፍቃሪዎች መካከል ከፍተኛ አምባጓሮ ይነሳል። የሮክ ሙዚቃ አፍቃሪዎች ከሆኑት ዱርዬዎች መካከል አንድ ቶማስ የሚባል ወጣት በደረሰበት ድብደባ ክፉኛ ይቆስልና ሕይወቱ ያልፋል። ጉዳዩ በፍርድ ቤት በሚታይበት ወቅት የመገናኛ ብዙኃን ከፍተኛ ትኩረት የሰጡት ሲሆን ዴትሌፍን ጨምሮ በርካታ የረብሻው ቀንደኛ ቆስቋሾች እስራት ተፈረደባቸው።

ዴትሌፍ ከእስር ከተለቀቀ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች “የሰው ሕይወት በችግር የተሞላው ለምንድን ነው?” የሚል ርዕስ ያለው በራሪ ወረቀት ይሰጡታል። በወረቀቱ ላይ ያነበበው ሐሳብ እውነት እንደሆነ በመገንዘቡ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። ከዚያም አኗኗሩን ሙሉ በሙሉ በመለወጥ ከ1996 ጀምሮ ቀናተኛ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከላይ በጠቀስነው አምባጓሮ ላይ የሞተው ቶማስ የተባለ ወጣት የቅርብ ጓደኛ የሆነ ዜክፍሬት የተባለ አንድ የሮክ ሙዚቃ አፍቃሪ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ይገናኝና ተጠምቆ ከጊዜ በኋላ የጉባኤ ሽማግሌ ይሆናል። ዜክፍሬት መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር ለመስጠት ዴትሌፍ ወደሚገኝበት ጉባኤ ሲመጣ ዴትሌፍ ምሣ ጋበዘው። (የቶማስ እናትም በዚህ ጉባኤ በሚካሄዱ ስብሰባዎች ላይ አልፎ አልፎ ትገኛለች።) ከአሥር ዓመት ገደማ በፊት ዴትሌፍና ዜክፍሬት አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ጥላቻ በጣም ከፍተኛ ነበር። አሁን ግን በመካከላቸው ያለው የወንድማማች ፍቅር በግልጽ ይታያል።

ዴትሌፍና ዜክፍሬት ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ቶማስ በትንሣኤ ሲነሳ ለማየት ይናፍቃሉ። ዴትሌፍ እንዲህ ይላል:- “ስለዚህ ተስፋ ሳስብ እንባዬ በዓይኔ ግጥም ይላል። ያን ጊዜ ባደረግሁት ነገር በጣም አዝናለሁ።” ሁለቱም በዛሬው ጊዜ ሌሎች ስለ ይሖዋ አውቀው መጽሐፍ ቅዱስ በሚሰጠው ተስፋ እንዲደሰቱ የሚረዱ ሲሆን ወደፊት ቶማስም ይሖዋን እንዲያውቅ ለመርዳት የጋራ ፍላጎት አላቸው።

አዎን፣ የአምላክ ቃል ሰዎችን የመለወጥ ኃይል አለው!

[የግርጌ ማስታወሻ]

b ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሰው አካል አፈጣጠር እጅግ አስገራሚ ነው

[ምንጭ]

Anatomy Improved and Illustrated, London, 1723, Bernardino Genga