በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ጦርነት የሚያከትምበት ጊዜ

ጦርነት የሚያከትምበት ጊዜ

ጦርነት የሚያከትምበት ጊዜ

‘ገና የ12 ዓመት ልጆች ነን። በፖለቲካም ሆነ በጦርነት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር አንችልም፤ ሆኖም መኖር እንፈልጋለን! ሰላምን ለማግኘት እንናፍቃለን። በሕይወት እያለን ሰላም ሰፍኖ ለማየት እንበቃ ይሆን?’—የአምስተኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ ልጆች

‘እንታፈሳለን ብለን ሳንሰጋ ትምህርት ቤት መሄድ እንዲሁም ጓደኞቻችንንና ቤተሰቦቻችንን መጠየቅ እንፈልጋለን። መንግሥት ለዚህ ጉዳይ ትኩረት ይሰጣል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። የተሻለ ሕይወት እንዲኖረን እንሻለን። በሰላም መኖር እንፈልጋለን።—የ14 ዓመቱ አልሃጂ

እነዚህ ልብ የሚነኩ ቃላት በእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ለዓመታት የተሰቃዩ ልጆችን ልባዊ ፍላጎት ያስተጋባሉ። የእነዚህ ልጆች ፍላጎት በሰላም መኖር ነው። ሆኖም ተስፋን እውን ማድረግ ቀላል አይደለም። ጦርነት የሌለበት ዓለም ለማየት እንበቃ ይሆን?

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተፋላሚ አንጃዎች የሰላም ስምምነት እንዲፈራረሙ ጫና በማሳደር አንዳንድ የእርስ በርስ ጦርነቶችን ለማስቆም ዓለም አቀፋዊ ጥረቶች ተደርገዋል። አንዳንድ አገሮች እንዲህ ዓይነት ስምምነቶችን ተግባራዊ ማድረግ እንዲቻል ሰላም አስከባሪ ኃይል ልከዋል። ሆኖም ሥር የሰደደ ጥላቻና መፈራራት በሰፈነባቸው ርቀው በሚገኙ አገሮች ውስጥ ያሉ ተፋላሚ አንጃዎች ስምምነቱን እንዲያከብሩ ተቆጣጣሪ ለመላክ የገንዘብ አቅሙ ወይም ፍላጎቱ ያላቸው ጥቂት አገሮች ስለሆኑ ጥረቱ መና ይሆናል። የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈረመ ከጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት በኋላ እንደገና ውጊያ ማገርሸቱ የተለመደ ሆኗል። የስቶክሆልሙ ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም እንዳለው “ተፋላሚዎቹ ኃይሎች ውጊያውን የመቀጠል ፍላጎቱና አቅሙ ሲኖራቸው ሰላም ማስፈን አስቸጋሪ ይሆናል።”

በርካታ የምድር ክፍሎችን እያናወጡ ያሉት እነዚህ መፍትሔ የሌላቸው ግጭቶች ክርስቲያኖች አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲያስታውሱ ያደርጓቸዋል። የራእይ መጽሐፍ በታሪክ ዘመን አስጨናቂ ወቅት እንደሚመጣና በምሳሌያዊ መንገድ የተገለጸ አንድ ፈረስ ጋላቢ ‘ሰላምን ከምድር እንደሚወስድ’ ይናገራል። (ራእይ 6:4) የማያባራ ጦርነት እንደሚኖር የሚያሳየው ይህ ሥዕላዊ መግለጫ መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻው ቀን’ ብሎ በሚጠራው ጊዜ ውስጥ እንደምንኖር ከሚጠቁሙት ጥምር ምልክቶች አንዱ ነው። a (2 ጢሞቴዎስ 3:1) ሆኖም የአምላክ ቃል የመጨረሻው ቀን ሰላም ለሚመጣበት ዘመን ዋዜማ እንደሆነ ያረጋግጥልናል።

መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 46:9 ላይ እውነተኛ ሰላም እንዲሰፍን በተወሰነ የምድር ክፍል ብቻ ሳይሆን በዓለም ዙሪያ ጦርነት መወገድ እንዳለበት ይገልጻል። በተጨማሪም ይኸው መዝሙር በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩት እንደ ቀስትና ጦር የመሳሰሉ የጦር መሣሪያዎች እንደሚጠፉ ለይቶ ይጠቅሳል። በተመሳሳይም የሰው ልጅ በሰላም እንዲኖር ከተፈለገ ዛሬ እንደ አሸን የሚፈሉት የጦር መሣሪያዎች መወገድ ይኖርባቸዋል።

ይሁንና ከጥይትና ከጠመንጃ ይልቅ የጦርነትን እሳት የሚያራግበው ጥላቻና ስግብግብነት ነው። ስግብግብነት ወይም አልጠግብ ባይነት የጦርነት ዋና መንስዔ ሲሆን ጥላቻ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ወደ ኃይል እርምጃ ይመራል። እነዚህን መጥፎ ስሜቶች ለማስወገድ ሰዎች አስተሳሰባቸውን መቀየር ያስፈልጋቸዋል። ሰላማውያን ሆነው መኖርን መማር ይኖርባቸዋል። በመሆኑም በጥንት ዘመን የኖረው ነቢዩ ኢሳይያስ ጦርነት የሚቀረው ሰዎች ‘ሰልፍ መማር ሲያቆሙ’ እንደሆነ መናገሩ ትክክል ነው።—ኢሳይያስ 2:4

ይሁን እንጂ የምንኖረው አዋቂዎችም ሆኑ ልጆች የሰላምን ጥቅም ሳይሆን ጦርነትን ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ በሚያደርግ ዓለም ውስጥ ነው። ልጆችም እንኳ ሳይቀር መግደልን እየተማሩ መሆናቸው ያሳዝናል።

መግደልን ተምረዋል

አልሃጂ በ14 ዓመቱ ከሠራዊቱ ተሰናበተ። የአማጺያን ኃይሎች የያዙትና ሥልጠና ሰጥተው ክላሺንኮቭ ያስታጠቁት ገና የአሥር ዓመት ልጅ እያለ ነበር። አስገድደው ወታደር ካደረጉት በኋላ ምግብ በመዝረፍና ቤቶችን በማቃጠል ተግባር አሠማሩት። ከዚህም በላይ ሰዎችን ገድሏል፤ የአንዳንዶችንም የሰውነት ክፍሎች ቆራርጧል። ዛሬ አልሃጂ በጦርነት ያሳለፈውን ሕይወት ከአእምሮው ማውጣትና ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀላቅሎ መኖር ከብዶታል። በልጅነቱ በውትድርና የተሰማራው አብርሃምም ሰዎችን እንዲገድል የሰለጠነ ሲሆን መሣሪያውን እንዲያስረክብ ሲጠየቅ ፈቃደኛ አልሆነም። “መሣሪያዬን ከወሰዱብኝ ምን እንደማደርግና ራሴን እንዴት እንደማኖር አላውቅም” ብሏል።

በውትድርና የተሰማሩ ከ300,000 በላይ ወንዶችና ሴቶች ልጆች ዓለማችንን እያመሷት ባሉት ማቆሚያ የለሽ የእርስ በርስ ግጭቶች እየተዋጉና ሕይወታቸውን እያጡ ነው። አንድ የአማጺያን መሪ እንዲህ ብሏል:- “በውትድርና የተሰማሩ ልጆች የሚሰጣቸውን መመሪያ ያከብራሉ፤ ትቼ የመጣሁት ሚስት ወይም ቤተሰብ አለኝ ብለው አይጨነቁም እንዲሁም ፍርሃት የሚባል ነገር አያውቁም።” ሆኖም እነዚህ ልጆች የተሻለ ሕይወት ማግኘት ይፈልጋሉ፤ ማግኘትም ይገባቸዋል።

በበለጸጉ አገሮች ውስጥ ልጆችን በውትድርና ማሰማራት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው። ያም ሆኖ በምዕራባውያን አገሮች የሚኖሩ በርካታ ልጆች ከቤታቸው ሳይወጡ ጦርነት እየተማሩ ነው። እንዴት?

በደቡብ ምሥራቅ ስፔይን የሚኖረውን ሆሴን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። የ16 ዓመቱ ሆሴ ካራቴ ይማር ነበር። አባቱ ለገና ስጦታ የገዛለትን ረጅም የጃፓን ጎራዴ በጣም ይወደው ነበር። ከዚህም በላይ የቪዲዮ ጨዋታዎች በተለይም ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን ማየት ያስደስተዋል። ሚያዝያ 1, 2000፣ በቪዲዮ የተመለከተው የፊልም ተዋናይ የሚያሳየውን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት በእውን ፈጸመ። በከፍተኛ የጭካኔ ስሜት ተነሳስቶ አባቱ በሰጠው በዚያው ጎራዴ አባቱን፣ እናቱንና እህቱን ገደላቸው። ለፖሊስ በሰጠው ቃል “በዓለም ላይ ብቻዬን መሆን እፈልጋለሁ፤ ወላጆቼ እንዲቆጣጠሩኝ አልፈልግም” ብሏል።

ደራሲና የጦር መኮንን የሆኑት ዴቭ ግሮስማን ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸው መዝናኛዎች የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “በሌሎች ላይ ሥቃይና መከራ ማድረስ መዝናኛ ተደርጎ በሚታይበት እንዲሁም የሰዎች የርኅራኄ ስሜት በጠፋበት ደረጃ ላይ ደርሰናል። ሰዎች በሁኔታው ከመዘግነን ይልቅ እነርሱ ራሳቸው በድርጊቱ እየተካፈሉ እንዳሉ በማሰብ ይደሰታሉ። መግደልንና በመግደል መደሰትን እየተማርን ነው።”

አልሃጂም ሆነ ሆሴ መግደልን ተምረዋል። ሁለቱም ነፍሰ ገዳይ የመሆን ዓላማ አልነበራቸውም፤ ሆኖም በተለያየ መልኩ ያገኙት ስልጠና አስተሳሰባቸውን አዛብቶታል። እንዲህ ያለው ስልጠና ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች ለዓመፅና ለጦርነት እንዲነሳሱ ያደርጋል።

ከጦርነት ይልቅ ሰላምን መማር

ሰዎች መግደልን እየተማሩ ዘላቂ ሰላም ፈጽሞ ሊገኝ አይችልም። ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ “[የአምላክን ትእዛዝ] ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ . . . በሆነ ነበር” ሲል ጽፏል። (ኢሳይያስ 48:17, 18) ሰዎች ስለ አምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት ሲያገኙና ሕግጋቱን መውደድ ሲማሩ ለዓመፅና ለጦርነት ጥላቻ ያሳድራሉ። አሁንም እንኳ ወላጆች ልጆቻቸው የሚጫወቱት ጨዋታ ዓመፅን የሚያበረታታ እንዳይሆን ክትትል ማድረግ አለባቸው። ትልልቆችም ቢሆኑ ጥላቻንና ስግብግብነትን ማስወገድን መማር ይኖርባቸዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ቃል የሰዎችን ባሕርይ የመለወጥ ኃይል እንዳለው በተደጋጋሚ ተመልክተዋል።—ዕብራውያን 4:12

የኦርቴንሲዮን ሁኔታ ተመልከት። ለውትድርና በግዳጅ የተመለመለው በወጣትነቱ ነበር። የተሰጣቸውን ወታደራዊ ሥልጠና በተመለከተ “ሰዎችን የመግደል ፍላጎት እንዲኖረንና መግደል እንዳንፈራ” ለማድረግ የተዘጋጀ ነው ብሏል። አፍሪካ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት ተዋግቷል። “ጦርነቱ ባሕርዬን ቀይሮታል። ያደረግሁት ነገር ሁሉ ዛሬም ከአእምሮዬ አልጠፋም። ተገድጄ ስላደረግሁት ነገር ሳስብ በጣም ይጸጽተኛል” ሲል በግልጽ ተናግሯል።

አብሮት የነበረ አንድ ወታደር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሲነግረው ኦርቴንሲዮ ልቡ ተነካ። መዝሙር 46:9 ላይ የሚገኘው አምላክ ጦርነትን በአጠቃላይ ለማስወገድ የገባው ቃል ትኩረቱን ሳበው። መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ ባጠና መጠን ከጦርነት የመራቅ ፍላጎቱ እያየለ መጣ። ብዙም ሳይቆይ እርሱና ሁለት ጓደኞቹ ከጦር ሠራዊቱ ተባረሩ፤ ከዚያም ሕይወታቸውን ለይሖዋ አምላክ ወሰኑ። ኦርቴንሲዮ እንዲህ ይላል:- “የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጠላቴን እንድወድድ ረድቶኛል። አምላክ ባልንጀራችንን መግደል እንደሌለብን ስለሚናገር በጦርነት የምሳተፍ ከሆነ በይሖዋ ላይ ኃጢአት መሥራት እንደሚሆንብኝ ተገነዘብኩ። የዚህ ዓይነት ፍቅር ለማሳየት አስተሳሰቤን መቀየርና ሰዎችን ጠላት አድርጌ መመልከቴን ማቆም ነበረብኝ።”

እንደነዚህ ያሉት እውነተኛ የሕይወት ታሪኮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በእርግጥም ሰዎች ሰላማዊ እንዲሆኑ እንደሚረዳ ያሳያሉ። ይህም የሚያስገርም አይደለም። ነቢዩ ኢሳይያስ በመለኮታዊ ትምህርትና በሰላም መካከል ቀጥተኛ ተዛምዶ እንዳለ ትንቢት ተናግሯል:- “ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ፣ የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል።” (ኢሳይያስ 54:13) ይኸው ነቢይ ከሁሉም ዘሮች የተውጣጡ ሰዎች የይሖዋ አምላክን ሕግ ለመማር ወደ ንጹሑ አምልኮ የሚጎርፉበት ጊዜ እንደሚመጣ አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። ውጤቱ ምን ይሆናል? “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”ኢሳይያስ 2:2-4

ከዚህ ትንቢት ጋር በሚስማማ መልኩ የይሖዋ ምሥክሮች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለጦርነት ዋና መንስዔ የሆነውን ጥላቻን እንዲያሸንፉ ባስቻለው ዓለም አቀፋዊ የማስተማር ዘመቻ እየተሳተፉ ናቸው።

ዓለም አቀፋዊ ሰላም እንደሚመጣ የተሰጠ ዋስትና

አምላክ ትምህርት ከመስጠትም በተጨማሪ ዓለም አቀፋዊ ሰላም ማስፈን የሚችል መስተዳድር ወይም “መንግሥት” አቋቁሟል። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የመረጠውን ገዢ ኢየሱስ ክርስቶስን “የሰላም አለቃ” ብሎ መጥራቱ ትልቅ ትርጉም አለው። ከዚህም በላይ “በመንግሥቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል፣ ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም” የሚል ማረጋገጫ ሰጥቶናል።—ኢሳይያስ 9:6, 7

የክርስቶስ አገዛዝ ማንኛውንም ዓይነት ጦርነት ሙሉ በሙሉ እንደሚያስወግድ ምን ማረጋገጫ አለን? ነቢዩ ኢሳይያስ በመቀጠል “የእግዚአብሔር ቅንዓት ይህን ያደርጋል” ብሏል። (ኢሳይያስ 9:7) አምላክ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ፍላጎቱም ሆነ ችሎታው አለው። ኢየሱስ ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነው። ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና ፈቃዱ በምድር እንዲሆን እንዲጸልዩ ያስተማራቸው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 6:9, 10) ይህ ልባዊ ልመና በመጨረሻ መልስ ሲያገኝ ጦርነት በምድር ላይ የሚያደርሰው ጥፋት ያበቃል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የምንኖረው በመጨረሻው ቀን ውስጥ ስለመሆኑ ማስረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 11 ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ሰላማዊ መሆንን ያበረታታል