በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጊልያድ 108ኛ ክፍል ተመራቂዎች ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ማበረታቻ ተሰጣቸው

የጊልያድ 108ኛ ክፍል ተመራቂዎች ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ማበረታቻ ተሰጣቸው

የጊልያድ 108ኛ ክፍል ተመራቂዎች ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ማበረታቻ ተሰጣቸው

መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ የሚቀርበውን አምልኮ ብዙውን ጊዜ “ቅዱስ አገልግሎት” ሲል ይጠራዋል። ይህ ስያሜ የተገኘው ለአምላክ የሚቀርበውን አገልግሎት ከሚያመለክት ግሪክኛ ቃል ነው። (ሮሜ 9:​4 NW ) ጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የ108ኛ ክፍል ተማሪዎቹን ሲያስመርቅ 5, 562 ሰዎች ሥነ ሥርዓቱን የተከታተሉ ሲሆን ተመራቂዎቹ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርቡ የሚያነሳሳውን በተናጋሪዎቹ የቀረበ ተግባራዊ ምክር አዳምጠዋል። a

ፕሮግራሙን በሊቀ መንበርነት የመራው የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራዝ ነበር። ፕሮግራሙ “የአባታችን ስም” የሚል ርዕስ ያለውን መዝሙር ቁጥር 52 በመዘመር ተጀመረ። የዚህ መዝሙር ሁለተኛ አንቀጽ “በማንኛውም አጋጣሚ ሁሉ አቻ የማይገኝለት ስምህን ለመቀደስ እንጣጣራለን” የሚል ስንኝ አለው። ይህ በእርግጥም ተማሪዎቹ (ከ10 አገሮች የተውጣጡት ናቸው።) በሚስዮናዊነት በሚመደቡባቸው 17 አገሮች ውስጥ የተማሩትን በተግባር ለማዋል ያላቸውን ልባዊ ፍላጎት የሚገልጽ መዝሙር ነው።

በፕሮግራሙ መክፈቻ ላይ ወንድም ጃራዝ ተማሪዎቹ በባዕድ አገሮች ለሚያቀርቡት አገልግሎት ዝግጁ የሚያደርጋቸውን የአምስት ወር ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማግኘታቸውን ተናገረ። ይህ ደግሞ ከዚህ ቀደም የተማሯቸውን ነገሮች የአምላክ ቃል በሚፈነጥቀው ብርሃን በመመርመር ‘ሁሉን ነገር ፈትነው መልካም የሆነውን እንዲይዙ’ አስችሏቸዋል። (1 ተሰሎንቄ 5:​21) በይሖዋ፣ በቃሉና ስልጠና አግኝተው በተመደቡበት ሥራ ላይ ያለማወላወል የሙጥኝ እንዲሉ አበረታታቸው። ይህን ሲያደርጉ ምን ሊረዳቸው ይችላል?

ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ የሚረዳ ተግባራዊ ምክር

የቤቴል ሥራዎች አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆነው ሎን ሺሊ “ምክንያታዊነትን የሚጠይቀውን ፈተና ታልፉ ይሆን?” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። የአምላካዊ ጥበብ ውጤት የሆነውን ምክንያታዊነትን ማሳየት የሚያስገኘውን ጥቅም ጎላ አድርጎ ተናገረ። (ያዕቆብ 3:​17 NW ) ምክንያታዊነት ግትር አለመሆንን፣ ከአድሎአዊነት መራቅን፣ ልከኝነትን፣ ለሌሎች አሳቢ መሆንንና ቻይነትን ያጠቃልላል። ወንድም ሺሊ “ምክንያታዊ የሆኑ ሰዎች ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ሚዛናዊ ናቸው። ወደ አንደኛው ጽንፍ አያዘነብሉም” በማለት ተናግሯል። አንድ ሚስዮናዊ ምክንያታዊ እንዲሆን ምን ሊረዳው ይችላል? ልክን ማወቅ፣ ሌሎች ሲናገሩ ማዳመጥና ከእነርሱ መማር እንዲሁም አምላካዊ መሠረታዊ ሥርዓት እስካልተጣሰ ድረስ የሌሎችን አመለካከት ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን ሊረዳው ይችላል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 9:​19-23

በወጣው ፕሮግራም መሠረት “መመገብ እንዳለባችሁ አትርሱ!” የሚለውን የሚያጓጓ ርዕስ ቀጥሎ ያቀረበው ሌላው የአስተዳደር አካል አባል ሳሙኤል ኸርድ ነበር። ቅዱስ አገልግሎት ለማቅረብ የሚያስችለውን ብቃት እንደያዙ ለመቀጠል በመንፈሳዊ ጥሩ አድርጎ መመገብ የሚያስገኘውን ጥቅም አጉልቶ ተናግሯል። ወንድም ኸርድ እንዲህ አለ:- “በቅርቡ የስብከትና የማስተማር ሥራችሁን ስትጀምሩ ከፍ ወዳለ መንፈሳዊ እንቅስቃሴ ትገባላችሁ። በመሆኑም ኃይላችሁን ለማደስ በመንፈሳዊ የምትመገቡትን መጠን መጨመር ያስፈልጋችኋል።” መንፈሳዊ ምግብ ዘወትር መመገብ አንድ ሚስዮናዊ መንፈሳዊ ጭንቀት እንዳያጋጥመውና ናፍቆት እንዳያጠቃው ሊረዳው ይችላል። አንድ ሰው እንዲህ ሲያደርግ እርካታ እንዲያገኝና ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርብ በተመደበበት የሙጥኝ ብሎ እንዲቆይ ይረዳዋል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​13

የጊልያድ አስተማሪ የሆነው ሎውረንስ ቦወን ተመራቂዎቹን “ወደ መጀመሪያው ተመለሱ” ሲል አበረታታቸው። ምን ማለቱ ነበር? አድማጮቹ ምሳሌ 1:​7ን አውጥተው “የጥበብ [“የእውቀት፣” NW ] መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው” የሚለውን እንዲያነቡ ጋበዘ። ተናጋሪው እንዲህ ሲል አብራራ:- “መሠረታዊ እውነት የሆነውን የይሖዋ ሕልውና ሽምጥጥ አድርጎ የሚክድ የትኛውም እውቀት ከትክክለኛ እውቀት ሊፈረጅ ወይም እንደ ትክክለኛ ማስተዋል ሊታይ ፈጽሞ አይችልም።” ወንድም ቦወን የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ዝርዝር መግለጫ ብዙ ቁርጥራጮችን በማገጣጠም ከሚሠራ አንድ ቅርጽ ጋር አመሳስሎታል። ቁርጥራጮቹ ሲገጣጠሙ አንድ ቅርጽ ወይም ምስል ይወጣቸዋል። እያንዳንዱ ቁርጥራጭ ቦታ ቦታውን በያዘ ቁጥር ምስሉ እያደገና ምንነቱ የበለጠ ግልጽ እየሆነ ይመጣል። ይህ ደግሞ አንድ ሰው ለምስሉ ያለውን አድናቆት እንዲጨምር ያደርገዋል። ይህ ሁሉም ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዲያቀርቡ ሊረዳ ይችላል።

የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጂስትራር የሆነው ዋላስ ሊቨረንስ በተከታታይ ከተሰጡት ንግግሮች መካከል የመጨረሻውን አቀረበ። የንግግሩ ርዕስ “ምስጋናን ለአምላክ መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ” የሚል ነበር። ትኩረት ያደረገው ኢየሱስ አሥሩን የሥጋ ደዌ በሽተኞች እንደፈወሰ በሚገልጸው ዘገባ ላይ ነው። (ሉቃስ 17:​11-19) አንዱ ብቻ አምላክን ለማወደስና ኢየሱስን ለማመስገን ተመለሰ። ወንድም ሊቨረንስ እንዲህ ሲል ተናገረ:- “የተቀሩት ዘጠኙም በመፈወሳቸው እንደተደሰቱ ምንም ጥርጥር የለውም። ፈውሱ ለራሳቸው የነበራቸውን ስሜት ያደሰላቸው ቢሆንም እነርሱ የፈለጉት ካህኑ ንፁሕ ናችሁ እንዲላቸው ብቻ ይመስላል።” አንድ ሰው እውነትን በመማር የሚያገኘው መንፈሳዊ ፈውስ የሚያሳድርበት የአመስጋኝነት መንፈስ አምላክን ስለ ጥሩነቱ እንዲያመሰግን ሊገፋፋው ይገባል። የጊልያድ 108ኛ ክፍል ተማሪዎች በአገልግሎታቸውና በሚከፍሉት መሥዋዕትነት ለአምላክ ያላቸውን ምስጋና ለመግለጽ በሥራዎቹና በጥሩነቱ ሁሉ ላይ እንዲያሰላስሉ ማበረታቻ ተሰጣቸው።​—⁠መዝሙር 50:​14, 23፤ 116:​12, 17

እንዴት መሥራት እንደሚቻል የሚገልጹ ተሞክሮዎችና ቃለ መጠይቆች

የሥነ ሥርዓቱን ቀጣይ ክፍል የመራው ሌላው የጊልያድ አስተማሪ ማርክ ኑሜር ነበር። ተማሪዎቹ በስልጠናው ወቅት በመስክ አገልግሎት ሲሰማሩ ያጋጠሟቸውን ተሞክሮዎች አቀረበ። ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ቤቱ ከመጠራታቸው በፊት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በአማካይ 12 ዓመታት አሳልፈዋል። በትምህርት ላይ እያሉ የተለያየ አስተዳደግ ያላቸውን በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመሩ። ይህ ደግሞ “ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር” እንደ ሌሎች መሆንን እንደሚያውቁ የሚያሳይ ነው።​—⁠1 ቆሮንቶስ 9:​22

ከተማሪዎቹ ተሞክሮዎች በኋላ ቻርልስ ሞሎሃን እና ዊልያም ሳሙኤልሰን በጊልያድ ከተማሩ የቤቴል ቤተሰብ አባላትና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጋር ቃለ ምልልስ አደረጉ። ቃለ ምልልስ ከተደረገላቸው ወንድሞች መካከል አንዱ የሆነው ሮበርት ፔቪ በጊልያድ 51ኛ ክፍል ከተመረቀ በኋላ በፊሊፒንስ አገልግሏል። ተማሪዎቹን እንዲህ በማለት አሳሰባቸው:- “አንድ ችግር ሲነሳ ሁሉም የየራሱን የመፍትሔ ሐሳብ ሊሰነዝር ይችላል። ምንጊዜም ቢሆን ከእናንተ ይልቅ የተሻለ ሐሳብ የማፍለቅ ችሎታ ያለው ሰው ይኖራል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስን በመመርመር አምላክ ስለጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ጥረት ማድረግን የመሰለ ነገር የለም። ምንጊዜም ትክክለኛው መፍትሔ የሚገኘው በዚያ መንገድ ነው።”

አስደሳች በሆነው በዚህ መንፈሳዊ ፕሮግራም ማጠቃለያ ላይ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጆን ባር “በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ቅዱስ አገልግሎት አቅርቡ” በሚል ርዕስ ንግግር አቀረበ። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ እንዲያመልኩ ለመርዳት በመስክ አገልግሎት መካፈል አንዱ የቅዱስ አገልግሎት መግለጫ መሆኑን ጥሩ አድርጎ አብራርቷል። ወንድም ባር በ⁠ማቴዎስ 4:​10 ላይ የሚገኙትን የኢየሱስ ቃላት ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ አለ:- “ይሖዋን ብቻ የምናመልክ ከሆነ ከመጎምጀት፣ ከባለ ጠግነት ምኞትና ራስን ከፍ ከፍ ማድረግን ከመሳሰሉ ስውር የጣዖት አምልኮ ዓይነቶች መራቅ ይገባናል። ሚስዮናውያኖቻችን ከ1940ዎቹ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ ስውር የጣዖት አምልኮዎችን በማስወገድ ረገድ ጥሩ ስም ያተረፉ መሆኑ ምንኛ አስደስቶናል! እናንተ የጊልያድ 108ኛ ክፍል ተመራቂዎችም የእነርሱን ጥሩ ምሳሌ ትኮርጃላችሁ ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን ቅዱስ አገልግሎት ለእርሱ ለማቅረብ ዝግጅታችሁን አጠናቅቃችኋል።”

ይህ ገንቢ ለሆነው ሥነ ሥርዓት አስደሳች መደምደሚያ ነበር። ቀጥሎ ከዓለም ዙሪያ የመልካም ምኞታቸውን መግለጽ ከሚፈልጉ ሰዎች የተላኩ ሰላምታዎች ተነበቡ፤ ዲፕሎማ የመስጠት ሥነ ሥርዓት ተከናወነ፤ እንዲሁም ተማሪዎች ያገኙትን ስልጠና እንደሚያደንቁ የሚገልጽ ደብዳቤ ተነበበ። ተመራቂዎቹ በአገልግሎት ምድባቸውና በይሖዋ አገልግሎት ጸንቶ የመቆየት ባሕርይ እንዲያሳዩ ተበረታተዋል። ከ25 አገሮች የመጡ እንግዶችን ጨምሮ በዚያ የተገኙ ሁሉ መዝሙር ከዘመሩ በኋላ ሥነ ሥርዓቱ በጸሎት ተዘጋ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a መጋቢት 11, 2000 የተደረገው የምረቃ ፕሮግራም የተላለፈው ኒው ዮርክ ፓተርሰን ከሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የትምህርት ማዕከል ነው።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ

ሚስዮናውያኑ የተውጣጡባቸው አገሮች:- 10

የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 17

የተማሪዎቹ ብዛት:- 46

አማካይ ዕድሜ:- 34

በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 16

በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 108ኛ ክፍል ተመራቂዎች

ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው።

(1) አማዶሪ ኢ፣ ኩክ ኦ፣ በርን ኤም፣ ሊ ኤ፣ (2) ኒውሰም ዲ፣ ፔዴርትሶልሊ ኤ፣ ቢግራ ኤች፣ ካቶ ቲ፣ ጌትዉድ ዲ፣ (3) ኢድ ዲ፣ ኢድ ጄ፣ ዌልስ ኤስ፣ ጄሚሰን ጄ፣ ጎንዛሌዝ ኤም፣ ጎንዛሌዝ ጄ፣ (4) ካቶ ቲ፣ ሎን ዲ፣ ኒክሎስ ዋይ፣ ፕሪስ ኤስ፣ ፎስተር ፒ፣ ኢባራ ጄ፣ (5) አማዶሪ ኤም፣ ማኒንግ ኤም፣ ጄምስ ኤም፣ ቦስትሩም ኤ፣ ጌትዉድ ቢ፣ ኒውሰም ዲ፣ (6) ፎስተር ቢ፣ ጄሚሰን አር፣ ሃይፊንገር ኤ፣ ኮፈል ሲ፣ ኮፈል ቲ፣ በርን ጂ፣ (7) ሃይፊንገር ኬ፣ ማኒንግ ሲ፣ ኩክ ጄ፣ ቦስትሩም ጄ፣ ሎን ኢ፣ ፔዴርትሶልሊ ኤ፣ (8) ጄምስ ኤ፣ ዌልስ ኤል፣ ፕሪስ ዲ፣ ኒክሎስ ኢ፣ ሊ ኤም፣ ኢባራ ፒ፣ ቢግራ ዋይ።