በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በቅርቡ ሁሉም ሰው ጤናማ ምግብ ያገኛል!

በቅርቡ ሁሉም ሰው ጤናማ ምግብ ያገኛል!

በቅርቡ ሁሉም ሰው ጤናማ ምግብ ያገኛል!

ምግብህ እንዳይበከል ለማድረግ ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች አሉ። ይሁን እንጂ በዚህ ረገድ ብዙዎቹ ነገሮች ከአንተ ቁጥጥር ውጭ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ እያንዳንዱን የምግብ ሸቀጥ ከመግዛትህም ሆነ ከማዘጋጀትህ በፊት ራስህ መመርመር አትችልም። ሩቅ በሆነ አካባቢ ተመርቶ የመጣ ምግብ መግዛት ሊኖርብህ ይችላል። በተጨማሪም በአየር፣ በውኃ፣ ወይም በአፈር ውስጥ ባሉ አደገኛ ኬሚካሎች የተበከለ ምግብ ልትገዛ ትችላለህ።

የዓለም የጤና ድርጅት ባለሥልጣናት “ምግብ ወለድ በሽታን መከላከል​—ድንበር የማይገድበው ፈተና” (እንግሊዝኛ) በሚል ርዕስ በወጣ አንድ ዘገባ ላይ እንደገለጹት ምግብ እንዳይበከል ከማድረግ ጋር ተያያዥነት ያላቸው አንዳንዶቹ ችግሮች “የየአገራቱ መንግሥታት በተናጠል ሊፈቷቸው የሚችሉ አይደሉም፤ ከዚህ ይልቅ ዓለም አቀፋዊ ትብብር ይጠይቃሉ።” በእርግጥም ምግብ ወለድ በሽታ ዓለም አቀፍ ችግር ነው!

በመሆኑም በቅርቡ ሁሉም ሰው ለጤና ተስማሚ ምግብ እንደሚያገኝ በእርግጠኝነት መናገራችን በአንዳንዶች አእምሮ ውስጥ ጥያቄ እንደሚፈጥር መገመት አያዳግትም። እርግጠኞች ልንሆን የቻልነው ‘የምድር ሁሉ ጌታ’ የሆነው ይሖዋ የሰው ልጅ ከምግብ ጋር በተያያዘ ለገጠሙት ችግሮች መፍትሔ እንደሚያመጣ ቃል ስለገባ ነው። (ኢያሱ 3:13) አንዳንድ ሰዎች የተበከለ ምግብ መኖሩ በራሱ አምላክ እምነት ሊጣልበት እንደማይችል የሚያረጋግጥ እንደሆነ ይናገሩ ይሆናል። ሆኖም እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አንድ ምግብ አሳላፊ በጥንቃቄ ጉድለት ጥሩው ምግብ እንዲበላሽ ቢያደርግ ምግቡን ያዘጋጀውን ሰው ተወቃሽ ማድረግ ተገቢ ይሆናል? እንደማይሆን የተረጋገጠ ነው።

በተመሳሳይም ግሩም የሆነው የምድር የምግብ አቅርቦት በመበላሸቱ ተጠያቂ የሚሆኑት ሰዎች እንጂ ፈጣሪ አይደለም። የተበከለ ምግብ መብዛቱ የሰው ልጆች ያመጡት ችግር ነው። በአንጻሩ አምላክ “ምድርን እያጠፉ ያሉትን [እንደሚያጠፋ]” ቃል ገብቷል።​—ራእይ 11:18

አምላክ የምግባችን ጥራትና ንጽሕና እንደሚያሳስበው በግልጽ ማየት ይቻላል። ምድርን የሠራትና “ለዐይን የሚያስደስት” ብቻ ሳይሆን “ለመብልም መልካም” የሆኑ ዛፎችን የፈጠረው እሱ ነው። (ዘፍጥረት 2:9) በኃጢአት ምክንያት የሰው ልጆች መታመም ከጀመሩ በኋላም እንኳ ይሖዋ፣ ሕዝቡ ምግባቸውንና ሰውነታቸውን ከብክለት እንዲጠብቁ የሚረዷቸው ግልጽ መመሪያዎች ሰጥቷል።​—“የጤና መርሆች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

አምላክ ምን ዓይነት ምግብ እንድናገኝ ይፈልጋል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከምድር ምግብን ታወጣ ዘንድ፣ ለእንስሳት ሣርን፣ ለሰው ልጆች ሥራ ዕፀዋትን ታበቅላለህ፤ የሰውን ልብ ደስ የሚያሰኝ ወይን፣ ፊቱን የሚያወዛ ዘይት፣ ልቡን የሚያበረታ እህል በዚህ ይገኛል።” (መዝሙር 104:14, 15) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ሕያውና ተንቀሳቃሽ ፍጡር ሁሉ ምግብ” ሊሆነን እንደሚችል ይናገራል።​—ዘፍጥረት 9:3

መጪውን ጊዜ በተመለከተ የአምላክ ቃል እንደሚከተለው በማለት ቃል ገብቶልናል፦ “በምድርም ለዘራኸው ዘር ዝናብን ይሰጥሃል፤ ከመሬትም የሚገኘው ፍሬ ምርጥና የተትረፈረፈ ይሆናል። በዚያን ቀን ከብቶችህ በትልቅ ሜዳ ላይ ይሰማራሉ።” (ኢሳይያስ 30:23) አዎን፣ በዛሬው ጊዜ ያሉት አስፈሪ የዜና ዘገባዎች “ጤናማ ምግብ ለሁሉም!” በሚል ማስታወቂያ የሚተኩበት ጊዜ ቅርብ ነው።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ፈጣሪ፣ ጤናማ የሆነ የተትረፈረፈ ምግብ የሚኖርበት ጊዜ እንደሚያመጣ የሚገልጽ ብሩሕ ተስፋ ሰጥቶናል

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

“የጤና መርሆች”

ከ3,500 ዓመታት ገደማ በፊት ለእስራኤል ብሔር የሙሴ ሕግ ተሰጥቶት ነበር። ሕጉ እስራኤላውያንን ከብዙ ምግብ ወለድ በሽታዎች ጠብቋቸዋል። እስቲ የሚከተሉትን ሕጎች እንመልከት፦

● ከሞተ እንስሳ ጋር በመነካካታቸው የረከሱ ማብሰያዎችን ወይም መመገቢያዎችን አትጠቀሙ፦ “የሚሠራበት ዕቃ ሁሉ እርሱ በውኃ ውስጥ ይደረግ፣ እስከ ማታም ርኩስ ነው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል።”​—ዘሌዋውያን 11:31-34 የ1954 ትርጉም

● ሳይታረድ የሞተ እንስሳ አትብሉ፦ “የሞተውን ሁሉ አትብላ።”​—ዘዳግም 14:21

● የተረፈ ምግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይበላ፦ “የተረፈውም ሁሉ በማግስቱ ይበላ። እስከ ሦስት ቀን የቆየ ማንኛውም የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቃጠል።”​—ዘሌዋውያን 7:16-18

ሬንድል ሾርት የተባሉ ሐኪም የሙሴ ሕግ፣ በእስራኤል ዙሪያ ያሉት ሕዝቦች ካሏቸው ሕግጋት ጋር ሲነጻጸር “ጥልቅ ጥበብና ምክንያታዊነት የተንጸባረቀባቸው የጤና መርሆች” የያዘ መሆኑ እንዳስደነቃቸው ገልጸዋል።