በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ምግባችሁ እንዳይበከል ተጠንቀቁ!

ምግባችሁ እንዳይበከል ተጠንቀቁ!

ምግባችሁ እንዳይበከል ተጠንቀቁ!

“በጀርመን የኢ-ኮላይ [ባክቴሪያ] ስጋት ትምህርት ቤት እንዲዘጋ ምክንያት ሆነ።”​—ሮይተርስ የዜና አገልግሎት፣ ጀርመን

“በአምስት ግዛቶች የሳልሞኔላ ወረርሽኝ የተከሰተው በበቆልት ምክንያት ነው ተባለ።”​—ዩ ኤስ ኤ ቱዴይ

“በሬዲዮአክቲቭ ጨረር የተመረዘ ሣር የበሉ 6 ላሞች ሥጋ በ9 ክልሎች ተከፋፈለ።”​—ዘ ማይኒቺ ዴይሊ ኒውስ፣ ጃፓን

ከላይ የቀረቡት ዜናዎች በሙሉ የወጡት ባለፈው ዓመት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ ነው። ባደጉ አገሮች ከሚኖረው ሕዝብ መካከል 30 በመቶ የሚሆነው በየዓመቱ በምግብ ወለድ በሽታዎች እንደሚሠቃይ ተመራማሪዎች ይገምታሉ።

እንዲህ ዓይነቶቹ ዘገባዎች ምን ስሜት ይፈጥሩብሃል? በሆንግ ኮንግ የሚኖር ሖዪ የተባለ አንድ አባት “በጣም ያስጨንቀኛል፤ እንዲያውም ያናድደኛል” በማለት ይናገራል። “ሁለት ልጆች ስላሉኝ ምግባቸው የሚዘጋጅበት ቦታና የሚሠራበት መንገድ ያሳስበኛል።”

በድሃ አገሮች ደግሞ ምግብ ወለድና ውኃ ወለድ በሽታዎች በየዓመቱ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የሚቀጥፉ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ ሕፃናት ናቸው። በናይጄሪያ የምትኖረው ቦላ “በአካባቢያችን ባሉት የገበያ ቦታዎች ውስጥ የምግብ ሸቀጦች ለዝናብ፣ ለንፋስና ለአቧራ የተጋለጡ ከመሆናቸውም ሌላ ዝንቦች ይወሯቸዋል” በማለት ትናገራለች። “በምግብ ምክንያት ስለሚመጡ በሽታዎች ሳነብ ወይም ስሰማ በጣም ስለምፈራ ቤተሰቤን ከዚህ ዓይነቱ በሽታ ለመጠበቅ እጥራለሁ።”

ቤተሰባችሁ የሚመገበው ምግብ የተበከለ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ትችላላችሁ? የካናዳ ምግብ ምርመራ ባለሥልጣን እንዲህ ይላል፦ “የምግብ መሸጫ መደብሮች ውስጥ የተበከለ ምግብ ከተገኘ ዜናው በአንድ ጊዜ ይሰራጫል። ደግሞም እንዲህ መሆኑ ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ ምግብ ወለድ በሽታ ሊያስከትል የሚችል የምግብ መበከል በራሳችን ወጥ ቤቶች ውስጥ በምናደርገው ወይም ሳናደርግ በምንቀረው ነገር ምክንያትም ሊከሰት ይችላል።”

ታዲያ ቤተሰባችሁን ከምግብ ወለድ በሽታዎች ለመጠበቅ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ምግባችሁ እንዳይበከል ልታደርጉ የምትችሏቸውን አራት ነገሮች ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በቀላሉ ሊጠቁ የሚችሉት እነማን ናቸው?

በምግብ ወለድ በሽታ በቀላሉ ከሚጠቁት ሰዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፦

● ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት

● ነፍሰ ጡሮች

● ከ70 ዓመት በላይ የሆኑ አረጋውያን

● በሽታ የመከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች

አንተም ሆንክ አብረውህ የሚመገቡ ሰዎች ከላይ ከተጠቀሱት መካከል የምትመደቡ ከሆነ ስለምታዘጋጀው፣ ስለምታቀርበውና ስለምትበላው ምግብ የተለየ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብሃል።

[የሥዕል ምንጭ]

ምንጭ፦ የኒው ሳውዝ ዌልስ የምግብ ባለሥልጣን፣ አውስትራሊያ