በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

ለሥራ ሚዛናዊ አመለካከት መያዝ

ባድ የኢኮኖሚ ድቀት ባለበት በዚህ ዘመን ሰዎችን በዋነኝነት የሚያሳስባቸው ቤተሰብን ለማስተዳደር የሚበቃ ገቢ የሚያስገኝ አስተማማኝ ሥራ ማግኘት ነው። በተለይ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከሥራ እየተቀነሱ ባሉበት በዚህ ጊዜ እንዲህ ያለ ሥራ ማግኘት ቀላል አይደለም። በድንገት ከሥራ ተፈናቅለህ ከሆነ ሌላ ሥራ ለማግኘት ጥረት ማድረግ ፈተና ሊሆንብህ ይችላል።—በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኙትን ሣጥኖች ተመልከት።

ይሁንና ሕይወት ማለት ሥራ ብቻ አይደለም። በአውስትራሊያ የሚኖረው ግሌን የተባለ የቤተሰብ ራስ እንዲህ ብሏል፦ “እውነቱን እንነጋገር ከተባለ፣ ማንም ሰው ሊሞት በሚያጣጥርበት ጊዜ ‘ምነው ሥራዬ ላይ የበለጠ ጊዜ ባሳለፍኩ ኖሮ’ ብሎ አይቆጭም።” እርግጥ ነው፣ ሕይወታችን የሚያረካና ትርጉም ያለው እንዲሆን ለሥራ የሚሆን ጊዜ መመደብ ያስፈልገናል። ይሁንና ለሌሎች ነገሮችም ይኸውም ለቤተሰብ፣ ለመዝናኛና ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ጊዜ መመደብ አስፈላጊ ነው። ታዲያ በሕይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑትን እነዚህን ነገሮች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማከናወን የምትችለው እንዴት ነው?

ለሥራ የሚሆን ጊዜ፣ ለራስ የሚሆን ጊዜ

መጽሐፍ ቅዱስ በርትተን በመሥራት ለቤተሰባችን የሚያስፈልገውን ነገር እንድናሟላ ይነገረናል። (ኤፌሶን 4:28) ያም ቢሆን ‘እንድንበላ፣ እንድንጠጣና በምንደክምበት ሁሉ እርካታን እንድናገኝም’ ያበረታታናል። (መክብብ 3:13) በእርግጥም በቂ እረፍት ሳታገኝ ወይም ዘና ሳትል ለረጅም ሰዓታት መሥራት በሕይወት ውስጥ የሚገኙትን ብዙ አስደሳች ነገሮች እንዳታጣጥም ሊያደርግህ ይችላል። በተጨማሪም ከባድ የጤና ችግር ሊያስከትልብህ ይችላል።

ከመጠን በላይ የመሥራት ልማድ ጤናማ ላልሆነ ውፍረት፣ ለአልኮል ሱሰኝነት፣ ለልብ ሕመም፣ በሥራ ቦታ ለሚደርስ አደጋ፣ ለመድኃኒት ሱሰኝነት፣ ለኃይለኛ ድካም፣ ለመንፈስ ጭንቀትና በውጥረት ምክንያት ለሚመጡ ብዙ ችግሮች ሊያጋልጥ ይችላል። ከመጠን በላይ መሥራት ለሞትም ሊዳርግ ይችላል። አንድ ዘገባ እንዳመለከተው በጃፓን በየዓመቱ 10,000 የሚያህሉ ሰዎች በሥራ ብዛት ምክንያት እንደሚሞቱ የሚገመት ሲሆን ይህ አኃዝ በዚያች አገር በመኪና አደጋ ምክንያት በየዓመቱ ከሚሞቱት ሰዎች ቁጥር ጋር እኩል ነው። ካሮሺ ወይም “ከመጠን በላይ በመሥራት የሚከሰት ሞት” ተብሎ የሚጠራው ይህ ችግር በጃፓን ብቻ የተወሰነ አይደለም።

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ጥበብ ያዘለ ምክር ልብ በል፦ “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል።” (መክብብ 4:6) አዎን፣ ሚዛናዊ መሆን በጣም አስፈላጊ ነው። ሥራህ ሕይወትህን እንዲቆጣጠረው አትፍቀድ። እረፍት ለማድረግና የድካምህን ፍሬ ለማጣጣም የሚያስፈልግህን ጊዜ በመመደብ አእምሯዊ፣ አካላዊና ስሜታዊ ጤንነትህን ጠብቅ።

ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የሆነው አንድሩ “የምንሠራው ለመኖር ነው እንጂ የምንኖረው ለመሥራት አይደለም” ብሏል። በተጨማሪም ሥራን ከእረፍትና ከመዝናኛ ጋር ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማከናወንህ የቤተሰብህን ፍላጎት ለማሟላት ይረዳሃል። ይሁን እንጂ በተለይ የተለያዩ ወጪዎች ካሉብህ ይህን ማድረግ ቀላል አይሆንም።

ሥራንና የቤተሰብ ሕይወትን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ መምራት

በዛሬው ጊዜ በርካታ ቤተሰቦች ፕሮግራማቸው በጣም የተጣበበ ሲሆን አብረው የሚያሳልፉት ጊዜም በጣም ትንሽ ነው። በእንግሊዝ የምትኖር አንዲት ሴት “ሥራዬ ኃይሌን ስለሚያሟጥጠው ለልጆቼ የሚተርፈኝ ኃይል በጣም ትንሽ ነው” ስትል በምሬት ተናግራለች። በዩናይትድ ስቴትስ ጥናት ከተደረገባቸው 5 በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች መካከል አንዱ በዋነኝነት የሚያሳስበው ነገር “ከወላጆቹ ጋር በቂ ጊዜ ማሳለፍ አለመቻሉ” እንደሆነ ገልጿል። በዚያች አገር የተደረገ ሌላ ጥናት እንደሚጠቁመው ደግሞ ሁለቱም የሚሠሩ ባልና ሚስት፣ በቀን ውስጥ እርስ በርስ የሚነጋገሩት በአማካይ ለ12 ደቂቃ ብቻ ነው።

በርካታ ግለሰቦች በሥራ ቦታ የሚያጋጥማቸው ውጥረት እየጨመረ መሄዱ ስላታከታቸው ቅድሚያ ሊሰጧቸው የሚገቡ ነገሮችን መለስ ብለው ከመረመሩ በኋላ ለውጥ ማድረግ ጀምረዋል። ሁለት ትናንሽ ልጆች ያሉት ቲሞቲ የተባለ አባወራ እንደሚከተለው ይላል፦ “እኔ ትርፍ ሰዓት የምሠራ ሲሆን ባለቤቴ ደግሞ ቅዳሜና እሁድ ትሠራ ነበር። አንገናኝም ነበር ማለት ይቻላል። በመጨረሻ ሕይወታችንን ከገመገምን በኋላ የሥራ ሁኔታችንን ለወጥን። አሁን በጣም ደስተኞች ነን።” የአንድ ንግድ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ የነበረው ብራያን እንዲህ ብሏል፦ “ሁለተኛው ልጃችን ሊወለድ መሆኑን ሳውቅ ለቤተሰባችን የሚስማማ ሥራ መፈለግ ጀመርኩ። የበለጠ ጊዜ ለማግኘት ስል ቀድሞ በዓመት ከሚከፈለኝ በአሥር ሺህ የአሜሪካ ዶላር የሚያንስ ደመወዝ የሚከፈልበት ሥራ ያዝኩ፤ ያም ቢሆን ይህን በማድረጌ አልቆጭም!” መሊና ደግሞ የመጀመሪያ ልጇን ስትወልድ በውጭ መሥራት አቆመች። “በአንድ ሰው ገቢ መተዳደርን እንደገና መልመድ አስቸግሮን ነበር” በማለት ታስታውሳለች። “ይሁን እንጂ እኔና ባለቤቴ ልጃችን ኤሚሊ በሕፃናት ማቆያ ቦታ ከምትውል ይልቅ እኔ አብሬያት ቤት ብሆን እንደሚሻል ተስማማን” ብላለች።

ይሁን እንጂ በርካታ ቤተሰቦች የወር ወጪያቸውን ለመሸፈን ብቻ እንኳ ብርቱ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልጋቸው መዘንጋት የለብንም። አንዳንድ ባለትዳሮች መሠረታዊ የሆኑ ወጪዎቻቸውን ለመሸፈን ሲሉ አንዳቸው ሁለት ሥራ መሥራት ሲኖርባቸው ሌሎች ባልና ሚስቶች ደግሞ ልጆቻቸውን አያቶቻቸው ዘንድ ወይም በሕፃናት ማቆያ ቦታዎች ትተው ሁለቱም ሥራ ይውላሉ።

አንተም የቤተሰብ ኃላፊነትህንና ሥራህን ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመወጣት የሚያስችሉህ ተጨማሪ ዘዴዎች ታገኝ ይሆናል። ዋናው ቁም ነገር፣ ለሥራ ከመጠን ያለፈ ትኩረት በመስጠት ከቤተሰብ ሕይወት የሚገኘውን ደስታ አለማጣትህ ነው።

ሥራን፣ መዝናኛንና ለቤተሰብህ የሚያስፈልጉትን ነገሮች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ማከናወንህ ብዙ ጥቅም እንደሚያስገኝልህ እርግጠኛ ሁን። በመጨረሻው ርዕሳችን ላይ ቀላልና ሚዛናዊ የሆነ ኑሮ ለመምራት ይበልጥ አስፈላጊ ስለሆነ አንድ ነገር እንመለከታለን።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ሥራህ ሕይወትህን እንዲቆጣጠረው አትፍቀድ

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል።”—መክብብ 4:6

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ለሥራ ከመጠን ያለፈ ትኩረት በመስጠት ከቤተሰብ ሕይወት የሚገኘውን ደስታ አትጣ

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ገንዘብ ወይስ እረፍት?

አንዳንድ የሃያኛው መቶ ዘመን ምሑራን የቴክኖሎጂ ማደግና መስፋፋት ሰዎችን አሰልቺ ከሆነ ሥራ አላቅቆ “ታይቶ ወደማይታወቅ የእረፍት ዘመን” እንደሚያስገባቸው ያምኑ ነበር።

ፕሮፌሰር ጁልያን ሃክስሊ፣ ወደፊት ማንም ሰው በሳምንት ከሁለት ቀን በላይ መሥራት እንደማያስፈልገው በ1930ዎቹ መጀመሪያ ላይ ተንብየው ነበር። በንግድ ሥራ የተሠማሩት ዎልተር ጊፈርድ፣ ቴክኖሎጂ “እያንዳንዱ ሰው የፈለገውን ማድረግ የሚችልበትን አጋጣሚ ይከፍትለታል። . . . የመኖርን ጥበብ የሚያዳብርበትን [እንዲሁም] አእምሮውንና መንፈሱን የሚያረኩ እንቅስቃሴዎችን ለማከናወን የሚያስችለውን ጊዜ” እንደሚሰጠው ተናግረው ነበር።

ሰዎች ቁሳዊ ነገሮችን ለማካበት ያላቸው ምኞትስ? ሄንሪ ፌርቻይልድ የተባሉ ሶሺዮሎጂስት “በአማካይ ከአራት ሰዓት በማይበልጥ የሥራ ቀን ውስጥ [ፋብሪካዎች] የት እናድርሰው ብለን እስክንቸገር ድረስ በጣም ብዙ ምርት ያመርታሉ” ሲሉ ፎክረው ነበር።

እነዚህ ትንቢቶች ምን ያህል ትክክል ናቸው? በእርግጥም በ20ኛውና በ21ኛው መቶ ዘመን በጣም ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ እድገት ታይቷል። ይህ ደግሞ የሥራ ጫናውን በእጅጉ መቀነስ ነበረበት። ይሁን እንጂ እውነታው ምን ያሳያል? ጆን ደ ግራፍ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “[ሰዎች] ምርታማ መሆናቸው ያስገኘውን ውጤት ተጨማሪ ገንዘብንና ቁሳቁሶችን ለማግበስበስ ተጠቀሙበት እንጂ አንዳቸውም ቢሆኑ ተጨማሪ ነፃ ጊዜ ለማግኘት አላዋሉትም። በቀላል አነጋገር፣ በማኅበረሰብ ደረጃ ከጊዜ ይልቅ ገንዘብን መርጠናል።”