በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

የፍርድ ቀን ምንድን ነው?

የፍርድ ቀን ምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “በዓለም ሁሉ ላይ . . . ለመፍረድ ዓላማ ያለው ሲሆን ይህንንም ለማድረግ ቀን ወስኗል” ይላል። (የሐዋርያት ሥራ 17:31) ብዙ ሰዎች በምንም መልኩ ቢሆን ለፍርድ መቅረብ የሚለውን ሐሳብ መስማት አይፈልጉም። አንተስ የሚሰማህ እንደዚህ ነው?

ከሆነ የፍርድ ቀን የሞቱትን ሰዎች ጨምሮ ለመላው የሰው ዘር ታላላቅ በረከቶችን የሚያመጣ ፍቅራዊ ዝግጅት እንደሆነ ስታውቅ ደስ ሊልህ ይችላል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ይሁንና የፍርድ ቀን ያስፈለገው ለምንድን ነው? ደግሞስ በዚያ “ቀን” የሚከናወነው ነገር ምንድን ነው?

የፍርድ ቀን ያስፈለገው ለምንድን ነው?

አምላክ ሰዎችን በምድር ላይ እንዲኖሩ ሲያደርግ ዓላማው ወደፊት በሌላ ስፍራ ለሚኖራቸው ሕይወት በምድር ላይ እንዲፈተኑ አልነበረም። ሰዎችን የፈጠራቸው በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት በአካልም ሆነ በአእምሮ ፍጹማን የነበሩ ቢሆንም በአምላክ ላይ ዓመፁ። በዚህም ምክንያት ከፊታቸው የተዘረጋላቸውን ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ከማጣታቸውም በላይ በዘሮቻቸው ሁሉ ላይ ኃጢአትንና ሞትን አመጡ።—ዘፍጥረት 2:15-17፤ ሮም 5:12

የፍርድ ቀን ለሺህ ዓመት የሚቆይ ጊዜ ሲሆን በዚህ ጊዜ ውስጥ ሰዎች፣ አዳምና ሔዋን ያጡትን ነገር መልሰው የማግኘት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። * ከላይ በተጠቀሰው በሐዋርያት ሥራ 17:31 ላይ የፍርድ ቀን ‘በዓለም ላይ’ የሚኖሩ ሰዎችን እንደሚመለከት መገለጹን ልብ በል። መልካም ፍርድ የሚፈረድላቸው ሰዎች የሚኖሩት በምድር ላይ ሲሆን ፍጹም በሆኑ ሁኔታዎች ሥር ዘላለማዊ ሕይወትን ያጣጥማሉ። (ራእይ 21:3, 4) በመሆኑም የፍርድ ቀን አምላክ ለሰዎችና ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ ከግብ ለማድረስ ይረዳል።

አምላክ የሾመው ዳኛ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ‘በሕያዋንና በሙታን ላይ እንደሚፈርድ’ ይናገራል። (2 ጢሞቴዎስ 4:1) ለፍርድ የሚቀርቡት “ሕያዋን” እነማን ናቸው? ሙታን እንደገና ‘በዓለም ላይ’ ለመኖር ወደ ሕይወት የሚመለሱት እንዴት ነው?

ኢየሱስ “በሕያዋን” ላይ ይፈርዳል

አምላክ ክፉዎችንና ብልሹ የሆነውን ሰብዓዊ ማኅበረሰብ ክፍሎች በሙሉ ወደሚያጠፋበት አስቀድሞ በትንቢት ወደተነገረው የዚህ ሥርዓት ፍፃሜ እየተቃረብን ነው። ለፍርድ የሚቀርቡት “ሕያዋን” ከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት የሚተርፉት ሰዎች ናቸው።—ራእይ 7:9-14፤ 19:11-16

አንድ ሺህ ዓመት በሚቆየው በዚያ የፍርድ ጊዜ ውስጥ ክርስቶስ ኢየሱስ፣ በሰማይ ለመኖር ትንሣኤ ካገኙ 144,000 ወንዶችና ሴቶች ጋር በመሆን በምድር ላይ ይገዛል። ክርስቶስና 144,000ዎቹ፣ ነገሥታትና ካህናት ሆነው በማገልገል የሰው ልጆችን የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ካስገኛቸው በረከቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይረዷቸዋል፤ እንዲሁም ታማኝ የሆኑ ሰዎች ቀስ በቀስ ወደ አካላዊና አእምሯዊ ፍጽምና እንዲደርሱ ያደርጋሉ።—ራእይ 5:10፤ 14:1-4፤ 20:4-6

በፍርድ ቀን ሰይጣንና አጋንንቱ በሰዎች ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ ይታገዳሉ። (ራእይ 20:1-3) ይሁን እንጂ በፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ ሰይጣን የእያንዳንዱን ሰው ታማኝነት እንዲፈትን ይፈቀድለታል። ለአምላክ ታማኝ ሆነው የሚቀጥሉ ሁሉ አዳምና ሔዋን ያላለፉትን ፈተና ያልፋሉ። እነሱም እንደገና በምትቋቋመው ገነት ውስጥ በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት ብቁ እንደሆኑ ይፈረድላቸዋል። በአንጻሩ ግን በአምላክ ላይ ለማመፅ የሚመርጡ ሁሉ እንደ ሰይጣንና አጋንንቱ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይጠፋሉ።—ራእይ 20:7-9

“በሙታን” ላይ መፍረድ

መጽሐፍ ቅዱስ በፍርድ ቀን ሙታን ‘እንደሚነሱ’ ይናገራል። (ማቴዎስ 12:41) ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት ትንሣኤ፣ ክፉ ነገር የሠሩ ደግሞ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉ።” (ዮሐንስ 5:28, 29) ይህ ጥቅስ የሚናገረው ሰዎቹ ሲሞቱ ከሥጋቸው ተለይተው ስለወጡ ነፍሳት አይደለም። ሙታን ምንም ስለማያውቁ ከሞት በኋላ መኖሯን የምትቀጥል ነፍስ የላቸውም። (መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 11:11-14, 23, 24) ኢየሱስ በሞት ያንቀላፉትን ሰዎች እንደገና ወደ ሕልውና በማምጣት በምድር ላይ እንዲኖሩ ያደርጋል።

ትንሣኤ ያገኙ ሰዎች ፍርድ የሚሰጣቸው ከመሞታቸው በፊት በሠሩት ነገር መሠረት ነው? አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ “የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል” በማለት ያስተምራል። (ሮም 6:7) ስለዚህ ከዚህ ሥርዓት ፍጻሜ በሕይወት እንደሚተርፉት ሰዎች ሁሉ በምድር ላይ ለመኖር ትንሣኤ የሚያገኙት ሰዎችም ፍርድ የሚሰጣቸው በፍርድ ቀን ውስጥ ‘በሚሠሩት ሥራ መሠረት’ ይሆናል። (ራእይ 20:12, 13) ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች በፍርድ ቀን ውስጥ በሚያደርጉት ነገር መሠረት ትንሣኤያቸው የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ አሊያም ጥፋት የሚያስከትል ይሆናል። ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል አብዛኞቹ ስለ ይሖዋ አምላክና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ስላወጣቸው ብቃቶች ለማወቅ ይህ የመጀመሪያ ጊዜያቸው ይሆናል። እነሱም ከአምላክ ፈቃድ ጋር ተስማምተው በመኖር በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት ለማግኘት አጋጣሚ ያገኛሉ።

የፍርድ ቀን ሊፈራ አይገባም

የፍርድ ቀን ከአምላክ ትምህርት የሚገኝበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በሕይወት የሚኖሩ ሁሉ የሚማሩትን ነገር ተግባራዊ ማድረግና በዚህም የሚገኘውን በረከት ማጣጣም የሚችሉበት ጊዜ ይሆናል። በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ከሞት ተነስተው ስትገናኙና አብረሃቸው ቀስ በቀስ ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና ስትደርስ የሚሰማህን ደስታ እስቲ አስበው!

በሞት የተለዩህ የምትወዳቸው ሰዎች ከሞት ተነስተው ስትገናኙ የሚሰማህን ደስታ እስቲ አስበው

በፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ አምላክ የሰብዓዊ ፍጥረታትን ታማኝነት ሰይጣን እንዲፈትን ይፈቅዳል። ይሁን እንጂ ይህ የሚያስጨንቅ ወይም የሚያስፈራ ነገር አይደለም። በፍርድ ቀን መጨረሻ ላይ በሕይወት የሚኖሩ ሁሉ ለዚህ የመጨረሻ ፈተና ለመቅረብ ሙሉ ብቃት ያላቸው ይሆናሉ። እንግዲያው የፍርድ ቀን፣ በኤደን ገነት በአምላክ ላይ የተነሳው የመጀመሪያው ዓመፅ ያስከተለውን ውጤት ለማስተካከል አምላክ ያወጣው ዓላማ ፍጻሜ አንዱ ክፍል ነው።

^ አን.7 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቀን” የሚለው ቃል የተለያየ ርዝማኔ ያለውን ጊዜ ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ዘፍጥረት 2:4ን በ1954 ትርጉም ተመልከት።