በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

 ከዓለም አካባቢ

“የክርስቲያኖች አምላክ በአሜሪካውያን ሕይወት ውስጥ አሁንም ሕያው ነው፤ ይሁን እንጂ በቅርብ ከምናስታውሰው ከማንኛውም ዘመን ይልቅ ዛሬ በፖለቲካችንና በባሕላችን ውስጥ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አነስተኛ ነው።”—ኒውስዊክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“የኢኮኖሚ ውድቀትና አለመረጋጋት አዳዲስ የተጎጂ ቡድኖችን ፈጥሯል፦ ከእነዚህ መካከል ለመፋታት የገንዘብ አቅማቸው የማይፈቅድላቸው ባለትዳሮች ይገኙበታል። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ብዙ ሰዎች፣ ተቻችለው መኖር በማይችሉበት ጊዜም ጭምር ሳይፋቱ መኖር ብዙ ወጪ የማይጠይቅ እንደሆነ እየተገነዘቡ ነው።”—ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል፣ ዩናይትድ ስቴትስ

በጀርመን ውስጥ አስተያየት ከተጠየቁ 3 እናቶች መካከል አንዷ ፋሽንን፣ ጓደኝነትንና ነገሮችን ይበልጥ ቀለል አድርጎ ማየትን ወይም ለራስ ከፍ ያለ ግምት መስጠትን በተመለከተ ከሴት ልጇ ትምህርት ታገኛለች።—በርሊነር ሞርገንፖስት፣ ጀርመን

ፀረ እንግዳ አካላት አሁንም በደማቸው ውስጥ አሉ

“በታሪክ ውስጥ በጣም ገዳይ የሆነው ኢንፍሉዌንዛ ከጠፋ ዘጠኝ አሥርተ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም በ1918 የተነሳውን የዚህን ኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ለመከላከል የሚረዳ ፀረ እንግዳ አካል (Antibody) አሁንም ከበሽታው በተረፉ ሰዎች ደም ውስጥ አለ፤ ይህ ደግሞ ሰዎች በሽታ የመከላከል አቅማቸው ጊዜ የማይሽረው መሆኑን ያሳያል” በማለት ኢንተርናሽናል ሄራልድ ትሪቢዩን ዘግቧል። የሳይንስ ሊቃውንት ከኅዳር በሽታ በተረፉ አረጋውያን ደም ላይ ባደረጉት ምርምር “የድሮውን ኢንፍሉዌንዛ ርዝራዦች ቢያገኙ ለመዋጥ ዝግጁ ሆነው የሚጠባበቁ አንቲቦዲዎችን” አግኝተዋል። ተመራማሪዎች እነዚህን አንቲቦዲዎች በመጠቀም ገዳዩን ኢንፍሉዌንዛ በመርፌ ተወግተው በበሽታው የተያዙ አይጦችን መፈወስ የቻለ ክትባት ሠርተዋል። ሰውነታችን ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ ሁኔታውን አስታውሶ በሽታ መከላከል መቻሉ ተመራማሪዎቹን አስገርሟል። አንድ ተመራማሪ “አምላክ ዕድሜ ልክ የሚሠሩ አንቲቦዲዎችን በመስጠት ባርኮናል!” በማለት በአድናቆት ተናግረዋል። ይህም “የማይገድልህ አደጋ አጠንክሮህ ያልፋል” የሚለውን አባባል እውነተኝነት ያረጋግጣል።

ለአምላክ የሚቀርቡ ጥያቄዎች

“አንተ ጥሩ ከሆንክ መከራ የኖረው ለምንድን ነው?” ስዊድን ውስጥ የኮሌጅ ተማሪዎች አምላክን የመጠየቅ አጋጣሚ ቢያገኙ ኖሮ መጠየቅ ከሚፈልጉት ጥያቄዎች መካከል ይህ ጥያቄ እንደሚገኝበት ዳገን የተሰኘው የስዊድን ዕለታዊ ጋዜጣ ይናገራል። አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው ተማሪዎቹ ካነሷቸው የተለመዱ ጥያቄዎች ውስጥ “የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው?” እና “ስንሞት ምን እንሆናለን?” የሚሉት ይገኙበታል። ስዊድን ሃይማኖት የለሽ አገር በመሆኗ ትታወቃለች። ያም ሆኖ ግን “አሁንም እነዚህን ጥያቄዎች የሚያነሱ ሰዎች አሉ” በማለት ጥናቱን የመራው አንድ የክርስቲያን ተማሪዎች ድርጅት ተወካይ ተናግሯል። “ወጣቶች እንዲህ ያሉ ጥያቄዎች ያሳስቧቸዋል።”

የአካል ጉዳተኝነት በትዳር ውስጥ ደስታን ይጨምራል

“በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የአካል ጉዳት ከደረሰባቸው በኋላ በጋብቻቸው ይበልጥ ደስተኛ መሆን እንደጀመሩ ገልጸዋል” በማለት ተመራማሪዎች ይናገራሉ። የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችን እንደ ልብ ማከናወን አለመቻል ውጥረት እንደሚፈጥር የታወቀ ነው፤ ሆኖም የትዳር ጓደኛሞች አንድ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። በተለይም በዕድሜ የገፉ ወንዶች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር አስደሳች ጊዜ ለማሳለፍ የሚያስችላቸው ተጨማሪ ጊዜ እንዳገኙ ይናገራሉ። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ የእርጅና ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ካረን ሮቤርቶ እንዲህ ብለዋል፦ “ወንዶች ቀደም ሲል በትዳራቸው ውስጥ ያከናውኑት ከነበረው ለየት ያለ ወይም ይበልጥ ትኩረት የሚጠይቅ የመንከባከብ ሥራ ወይም ኃላፊነት መቀበላቸው ሚስቶቻቸውን እንዲደግፉና አብረዋቸው ተጨማሪ ጊዜ እንዲያሳልፉ አጋጣሚ ሰጥቷቸዋል፤ ይህ ደግሞ ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይበልጥ እንዲያደንቁ አድርጓቸዋል።”