በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አብሮ መመገብ የቤተሰባችሁን አንድነት ሊያጠናክረው ይችላል?

አብሮ መመገብ የቤተሰባችሁን አንድነት ሊያጠናክረው ይችላል?

 አብሮ መመገብ የቤተሰባችሁን አንድነት ሊያጠናክረው ይችላል?

“ሕይወት ራሱ በደስታ፣ በፍቅርና በመጽናናት ብቻ ሳይሆን በሐዘንና በለቅሶም ጭምር የተሞላ ነው። የሆነ ሆኖ ብንደሰትም ቢከፋንም መመገባችን አይቀርም። የተደሰቱም ሆኑ ያዘኑ ሰዎች ጥሩ ምግብ በመመገብ ሊደሰቱ ይችላሉ።”—አሜሪካዊቷ ጸሐፊ ሎሬ ኮልዊን

ዓመታት በፊት በምዕራባውያን አገሮች ውስጥ ብዙ ቤተሰቦች ከፍ አድርገው የሚመለከቱት አንድ ልማድ ነበራቸው። መላው ቤተሰብ ቢያንስ በቀን አንድ ጊዜ አብሮ ለመብላት በማዕድ ዙሪያ ይሰበሰብ ነበር። ሥርዓቱን የሚረብሽ ምንም ነገር ማድረግ አይፈቀድም። ቴሌቪዥን የሚመለከት፣ በጆሮ ማዳመጫ ሙዚቃ የሚያዳምጥ ወይም ለጓደኞቹ የጽሑፍ መልእክት የሚልክ ሰው አልነበረም። በማዕድ ሰዓት የነበረው ሰላማዊ ሁኔታ በዚያ የተገኙ ሁሉ ጣፋጭ ምግብ እየተመገቡ ጥበብን ለመቅሰም፣ የቤተሰብ ትስስራቸውን ለማጠናከርና በዕለቱ ያጋጠሟቸውን ነገሮች እያነሱ ለመሳቅ አጋጣሚ ይፈጥርላቸው ነበር።

በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ቤተሰብ ተሰባስቦ አንድ ላይ መመገቡ ዘመኑ ያለፈበት ባሕል ሊመስላቸው ይችላል። በብዙ ቤቶች ውስጥ አንድ ላይ መመገብ አልፎ አልፎ ብቻ የሚደረግ ነገር እንጂ የቤተሰቡ ደንብ አይደለም። ቤተሰቦች አንድ ላይ መመገብ አስቸጋሪ የሆነባቸው ለምንድን ነው? ይህን ልማድ ጠብቀን ማቆየታችን ተገቢ ነው? ይህ ልማድ ለእያንዳንዱ የቤተሰብ አባልስ ምን ጥቅም ያስገኛል?

ከቤተሰብ ጋር አብሮ መመገብ—እየጠፋ ያለ ባሕል

ሮበርት ፑትናም ቦውሊንግ አሎን በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “ቤተሰብ አብሮ [እራት] የመመገቡ ልማድ በአንድ ትውልድ ውስጥ በግልጽ እየቀነሰ መምጣቱ . . . ማኅበራዊ ትስስራችን ምን ያህል በፍጥነት እየተለወጠ እንደመጣ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ ነው” በማለት ገልጸዋል። ለዚህ ለውጥ ምክንያት የሆኑት ነገሮች ምንድን ናቸው? በመጀመሪያ፣ የኑሮ ውድነት ባሎችም ሆኑ ሚስቶች ረጅም ሰዓት እንዲሠሩ አስገድዷቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ አስተማማኝ የኢኮኖሚ አቅም የሌላቸው ነጠላ ወላጆች ደግሞ ከፍተኛ የጊዜ እጥረት አለባቸው። ሁለተኛ፣ ሩጫ የበዛበት የኑሮ ሁኔታ ሰዎች በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦችን በችኮላ እንዲበሉ ያስገድዳቸዋል። ትልልቅ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ልጆችም ጭምር እንደ ስፖርትና ከትምህርት ሰዓት ውጪ የሚከናወኑ ሌሎች እንቅስቃሴዎችን የመሰሉ ብዙ ጉዳዮች አሉባቸው።

በተጨማሪም በእራት ሰዓት ያለውን ጩኸትና ጫጫታ ለመሸሽ ሲሉ ትንንሽ ልጆቻቸው ከመተኛታቸው በፊት ቤት መግባት የማይፈልጉ አባቶች አሉ። በጊዜ ቤታቸው የሚገቡ ሌሎች ወላጆች ደግሞ ልጆቻቸውን ራት አብልተው ካስተኙ በኋላ ባልና ሚስቱ ብቻቸውን ጸጥታ በሰፈነበት ሁኔታ መብላት ይመርጣሉ።

እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ቤተሰቦች በተለያየ ሰዓት ምግባቸውን እንዲበሉ ያደርጋቸዋል። በምግብ ሰዓት ሊኖር የሚገባው ጭውውት በማቀዝቀዣ ላይ በሚለጠፍ ማስታወሻ እየተተካ ነው። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ቤት ሲደርስ ከዚያ በፊት ተዘጋጅቶ የተቀመጠ ምግብ አሙቆ ቴሌቪዥን እያየ፣ ኮምፒውተር እየተጠቀመ ወይም ጌም እየተጫወተ ይመገባል። በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ እንዲህ ያሉ አዝማሚያዎች የሚለወጡ አይመስሉ ይሆናል። ታዲያ እንዲህ ያለውን አዝማሚያ ለማስቀረት ይህን ያህል መጨነቅ ይኖርብናል?

አብሮ መመገብ የሚያስገኘው ጥቅም

ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መብላቱ ወላጆች የልጆቻቸውን ስሜታዊ ደኅንነት ለመከታተል የሚያስችል ልዩ አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል። ሚሪያም ዌይንስቴይን ዘ ሰርፕራይዚንግ ፓወር ኦቭ ፋሚሊ ሚልስ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ የእራት ሰዓት “ልጆች ምንጊዜም ከወላጆቻቸው ጋር የሚሆኑበት ብሎም ዘና ባለ ሁኔታ የእነሱን ትኩረት የሚያገኙበት ጊዜ ነው” በማለት ገልጸዋል። አክለውም “ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ እራት መብላቱ ለችግሮች ሁሉ መፍትሔ ያስገኛል ማለት ባይሆንም ጥቂት ጥረት ብቻ የሚጠይቁ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚረዳ የተረጋገጠ ነው” ብለዋል።

በስፔን የሚኖር ኤድዋርዶ የሚባል በመካከለኛ ዕድሜ ላይ  የሚገኝ አንድ አባት ከላይ በተገለጸው ሐሳብ ይስማማል። ኤድዋርዶ እንዲህ ብሏል፦ “ልጅ እያለሁ በየዕለቱ 11 ሆነን ማዕድ ፊት እንቀርብ ነበር። አባቴ ብዙ ጥረት ቢጠይቅበትም ከቤተሰቡ ጋር ምሳ ለመመገብ ሲል ወደ ቤት ይመጣ ነበር። በሁሉም አቅጣጫ ሲታይ ያ ሰዓት ልዩ ወቅት ነበር። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል በሕይወቱ ውስጥ ስለሚያጋጥመው ነገር ወዲያው እንሰማለን። ብዙውን ጊዜ በዚህ ሰዓት ሳቅና ጨዋታ አይጠፋም ነበር። እነዚያ አስደሳች ትዝታዎች እኔም የአባቴን ምሳሌ መከተል እንዳለብኝ አሳምነውኛል።”

በተጨማሪም ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መብላቱ ልጆች ይበልጥ ሚዛናዊና ጤናማ ሕይወት እንዲመሩ ይረዳቸዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የዕፅ ሱሰኝነትን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ብሔራዊ ማዕከል እንዳሳወቀው በሳምንት ውስጥ ወደ አምስት ጊዜ ያህል ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚመገቡ ወጣቶች ከጭንቀት፣ ከመሰላቸት ወይም ተነሳሽነት ከማጣት ጋር በተያያዘ እምብዛም ችግር የማያጋጥማቸው ሲሆን የትምህርት ቤት ውጤታቸውም የተሻለ ነው።

ኤድዋርዶ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መመገቡ ልጆች የተረጋጋ መንፈስ እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል ብዬ አምናለሁ። ሴት ልጆቼ ለእኛ የሚነግሩን ነገር ሲያጋጥማቸው መቼ አግኝተን እንነግራቸዋለን ብለው አይጨነቁም። በቤተሰብ አንድ ላይ መመገባችን በየቀኑ ለዚህ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ከዚህም በላይ አባት እንደመሆኔ መጠን እነዚህ ወቅቶች ልጆቼ የሚያጋጥማቸውን ችግር በየቀኑ እንድሰማ ይረዱኛል።”

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ቤተሰቦች አንድ ላይ መመገባቸው መጥፎ የአመጋገብ ልማድ እንዳያዳብሩ ይረዳቸዋል። በስፔን የሚገኘው የናቫሬ ዩኒቨርሲቲ ሪፖርት እንዳደረገው ለብቻ መመገብ ለመጥፎ የአመጋገብ ችግር የመጋለጥ አጋጣሚን ይጨምራል። እውነት ነው፣ ማንኛውንም ሰው እንዲህ ያለ የአመጋገብ ችግር ሊያጋጥመው ይችላል፤ ሆኖም አንድ ሰው ከሌሎች ጋር አዘውትሮ የመመገብ ልማድ ከሌለው ለዚህ ችግር የመጋለጡ አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። የሁለት ሴቶች ልጆች እናት የሆነችው ኤስሜራልዳ “አብሮ የመብላት ልማድ መኖሩ ልጆች የሚያስብላቸው ሰው እንዳለ እንዲሰማቸው ያደርጋል። ከቤተሰብ ጋር አብሮ መብላት ልጆች ሞቅ ባለና ፍቅር በሰፈነበት ቤተሰብ ውስጥ መኖር የሚያስገኘውን ስሜታዊ መረጋጋት ያጎናጽፋቸዋል” ብላለች።

በተጨማሪም ቤተሰብ አብሮ መብላቱ ወላጆች የልጆቻቸውን መንፈሳዊነት ለመከታተል አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። አምላክ ከዛሬ 3,500 ዓመታት በፊት እስራኤላውያንን፣ በልጆቻቸው ልብ ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን ለመቅረጽ አብረዋቸው ጊዜ እንዲያሳልፉ አበረታቷቸው ነበር። (ዘዳግም 6:6, 7) የሁለት ልጆች አባት የሆነው አንከል “ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ በሚበላበት ጊዜ አብረው ስለሚጸልዩና በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ ስለሚወያዩ ይህ ወቅት ጥሩ መንፈሳዊ ሁኔታ እንዲሰፍን ያደርጋል” በማለት ተናግሯል። በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መመገብ ካሉት ጥቅሞች አንጻር አንዳንድ ቤተሰቦች ዘወትር አብሮ መመገብን የቤተሰቡ ልማድ ለማድረግ የትኞቹን እርምጃዎች ወስደዋል?

ጊዜ መድቡ

ኤስሜራልዳ “መደራጀትና ፈቃደኝነት አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። መጨረሻ ቤት የሚደርሰውን የቤተሰብ አባል የሚያካትት ፕሮግራም ለማውጣት የተቻላችሁን ሁሉ ጥረት አድርጉ” በማለት ተናግራለች። የሁለት ልጆች እናት የሆነችው ማሪቤል “ምንም ይምጣ ምን በየዕለቱ እራታችንን አብረን ለመብላት ጥረት እናደርጋለን” ብላለች። አንዳንድ ቤተሰቦች ቅዳሜና እሁድ የሚያገኙትን ትርፍ ጊዜ ተጠቅመው በሳምንቱ መሀል ለሚመገቡት እራት የሚያስፈልጉ አንዳንድ ነገሮችን አስቀድመው ያዘገጃጃሉ፤ ወይም ምግቡን ሠርተው ያስቀምጣሉ።

ከቤተሰብ ጋር አንድ ላይ የመመገቡ ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር እንደሆነ አድርጋችሁ መመልከታችሁም ሊረዳችሁ ይችላል። ኤድዋርዶ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ከቤተሰቤ ጋር እራት ለመመገብ የሥራ ሰዓቴን ማስተካከል የነበረብኝ ቢሆንም ይህን በማድረጌ አይቆጨኝም። አሁን ስለ ቤተሰቤ ሁኔታ በደንብ እንደማውቅ ይሰማኛል። ሥራ ላይ እያለሁ ለረጅም ሰዓት ትኩረቴን ሥራ ላይ ማድረግ አለብኝ፤ ቤት ስመጣ ግን በምግብ ሰዓት ለቤተሰቤ ተመሳሳይ ትኩረት አለመስጠቴ አሳቢነት አለማሳየት እንደሆነ ይሰማኛል።”

ትኩረት ስለሚከፋፍሉ ነገሮችስ ምን ማለት ይቻላል? የ16 ዓመት ወጣት የሆነው ዴቪድ እንዲህ ብሏል፦ “ቤተሰባችን ምግብ የሚበላው ቴሌቪዥን በሌለበት ክፍል ውስጥ ነው። ይህን አጋጣሚ ተጠቅመን ለእማማና ለአባባ ስለውሏችን የምንነግራቸው ሲሆን እነሱም ብዙውን ጊዜ ጥሩ ምክር ይሰጡናል።” ዴቪድ አክሎ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “በአሁኑ ጊዜ በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች ከወላጆቻቸው ጋር ብዙም አያወሩም። ሁሉም የቤተሰብ አባል ቤት በሚገኝበት ጊዜም እንኳ እያንዳንዱ ሰው በየፊናው ቴሌቪዥኑን እየተመለከተ ብቻውን ይበላል። ምን እያመለጣቸው እንዳለ የሚገነዘቡ አይመስለኝም።” ሳንድራ የተባለች የ17 ዓመት ወጣት ዴቪድ ከተናገረው ሐሳብ ጋር በመስማማት እንዲህ ብላለች፦ “የክፍሌ ልጆች ‘እናቴ በማቀዝቀዣው ውስጥ ምን አስቀምጣልኝ ይሆን?’ እያሉ ሲናገሩ ስሰማ አዝናለሁ። እኔ፣ ቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ የሚመገበው ሆድ ለመሙላት ብቻ እንዳልሆነ ይሰማኛል።  እንዲህ ያለው አጋጣሚ ለመሳቅ፣ ለመጫወትና እርስ በርስ ያለንን ፍቅር ለማሳየት ጊዜ ይሰጠናል።”

ዘ ሰርፕራይዚንግ ፓወር ኦቭ ፋሚሊ ሚልስ የተሰኘው ጽሑፍ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆኖ መመገብ “ሁላችንም በየዕለቱ የሚያጋጥመንን ውጥረት ለመከላከል” ሊረዳን እንደሚችል ይገልጻል። እናንተስ በቤተሰብ አንድ ላይ ተሰባስባችሁ መመገባችሁ እርስ በርስ ይበልጥ እንድትቀራረቡ የሚያስችል አጋጣሚ ይፈጥርላችሁ ይሆን? ሕይወታችሁ ውጥረት የተሞላበት ከሆነ ከቤተሰባችሁ ጋር አንድ ላይ መመገባችሁ እንድትረጋጉና ከምትወዷቸው የቤተሰባችሁ አባላት ጋር እንድትጨዋወቱ አጋጣሚ ሊከፍትላችሁ ይችላል። በዚህ ረገድ የምታደርጉት ጥረት የሚክሳችሁ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ከቤተሰባችሁ ጋር ማዕድ ፊት ስትቀርቡ የሚከተሉትን ነገሮች ልትማሩ ትችላላችሁ

መጨዋወት። ልጆች እንዴት ማውራትና በአክብሮት ማዳመጥ እንዳለባቸው ይማራሉ። ከቤተሰብ ጋር የሚያደርጉት ጭውውት የሚያውቋቸውን ቃላት ብዛት የሚያሳድግ ከመሆኑም በላይ ሐሳባቸውን እንዴት መግለጽ እንደሚችሉ ያስተምራቸዋል።

በመደበኛው የምግብ ሰዓት ለጤና የሚጠቅሙ ምግቦችን ተመገቡ።

መልካም ምግባር አሳዩ። ተካፍላችሁ በመብላትና ከምግቡ የተሻለው ክፍል እንዲሰጣችሁ ባለመጠየቅ ለጋስነትን ተማሩ። በተጨማሪም በምትበሉበት ጊዜ ለሌሎች የቤተሰቡ አባላት አሳቢነት ማሳየትን ተማሩ።

ተባብራችሁ ሥሩ። ልጆች ምግብ በማቀራረብና ምግብ ከተበላ በኋላ ዕቃ በማነሳሳት እንዲሁም የተበላበትን ዕቃ በማጠብ ወይም ቤተሰቡን በማስተናገድ ሊተባበሩ ይችላሉ። እያደጉ ሲሄዱ ምግብ በመሥራትም ሊረዱ ይችላሉ።