በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እዚህ ምድር ላይ የምንኖርበት ምክንያት

እዚህ ምድር ላይ የምንኖርበት ምክንያት

እዚህ ምድር ላይ የምንኖርበት ምክንያት

ፈጣሪያችን የሆነው ይሖዋ አምላክ ያለ ዓላማ የሚሠራው ምንም ነገር እንደሌለ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ለምሳሌ ያህል፣ በምድር ላይ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችለውን እሱ ያዘጋጀውን የውኃ ዑደት ተመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ዝግጅት በግጥም መልክ፣ ሆኖም በትክክል እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “ወንዞች ሁሉ ወደ ባሕር ይፈሳሉ፤ ባሕሩ ግን ፈጽሞ አይሞላም፤ ወንዞች ወደ መጡበት ስፍራ፣ ወደዚያ እንደ ገና ይመለሳሉ።”—መክብብ 1:7

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ የሰጠውን ተስፋ አስተማማኝነት ከላይ ከተገለጸው ዑደት ጋር አወዳድሮታል። በአሁኑ ጊዜ እንደምናውቀው የፀሐይ ሙቀት ከውቅያኖሶች፣ ከባሕሮችና ከሐይቆች ላይ ውኃ እንዲተን ያደርጋል፤ ከዚያም ውኃው በዝናብ መልክ ወደ ምድር ተመልሶ ይመጣል። ይሖዋ ይህን ዑደት እንደ ማስረጃ ከጠቀሰ በኋላ እንዲህ ሲል ገልጿል፦ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል።”—ኢሳይያስ 55:10, 11

ሕይወት በምድር ላይ እንዲኖር ለማስቻል ደመናዎች ንጹሕ ውኃ ወደ ምድር ያዘንባሉ። በተመሳሳይም ‘ከአምላክ አፍ የሚወጣው ቃል’ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማርካት ያስችለናል። ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣው ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” በማለት ገልጿል።—ማቴዎስ 4:4

ከአምላክ የሚገኘውን መንፈሳዊ ምግብ መቋደስ ሕይወታችንን ከዓላማው ጋር እንድናስማማ ያስችለናል። ሆኖም ሕይወታችንን ከአምላክ ዓላማ ጋር ማስማማት እንድንችል በመጀመሪያ ዓላማው ምን እንደሆነ መረዳት ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ምድርን የፈጠራት ለምንድን ነው? ስለ ምድር ያለው ዓላማስ እኛን የሚነካን እንዴት ነው? እስቲ እንመልከት።

አምላክ ለምድር ያለው ዓላማ

አምላክ የሰው ዘሮች ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንዲያገኙ ስለሚፈልግ የመጀመሪያዎቹን ወንድና ሴት ማለትም አዳምንና ሔዋንን ኤደን ተብሎ በሚጠራ ገነት የሆነ የአትክልት ቦታ ውስጥ አስቀምጧቸው ነበር። ከዚያም “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ በመባረክ ልጆች እንዲወልዱ መመሪያ ሰጣቸው።—ዘፍጥረት 1:26-28፤ 2:8, 9, 15

ከዚህ መመሪያ በመነሳት ምን ብለን መደምደም እንችላለን? አምላክ የሰው ልጆች መላዋን ምድር እንዲያለሙና ገነት አድርገው እንዲኖሩባት ፈልጎ እንደነበረ ግልጽ አይደለም? የአምላክ ቃል “ሰማየ ሰማያት የእግዚአብሔር ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ይላል።—መዝሙር 115:16

ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ አምላክ ለእነሱ የነበረው ዓላማ ሲፈጸም ማየት ከፈለጉ ግን ይሖዋን በመታዘዝ አክብሮት ሊያሳዩት ይገባል። ታዲያ አዳም ይህን አሟልቶ ተገኝቷል? አላሟላም፤ የአምላክን ትእዛዝ በመጣስ ኃጢአት ሠርቷል። ይህስ ምን አስከተለ? ዛሬ ያለነውን ሁላችንንም ጨምሮ የአዳም ዘሮች በአጠቃላይ ኃጢአትና ሞት ወርሰናል፤ መጽሐፍ ቅዱስ “ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል” በማለት ይህን ያረጋግጣል።—ሮሜ 5:12

በዚህም ምክንያት ሰዎች ሁሉ ለሞት ተዳረጉ፤ እንዲሁም ምድር በእጽዋት ለምታ ከዳር እስከ ዳር ገነት ሳትሆን ቀረች። ታዲያ አምላክ ለምድር የነበረው ዓላማ ተለውጦ ይሆን?

አልተለወጠም፤ ምክንያቱም አምላክ “ከአፌ የሚወጣው ቃሌ፣ በከንቱ ወደ እኔ አይመለስም፤ ነገር ግን የምሻውን ያከናውናል፤ የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል” ብሎ መናገሩን አስታውስ። በተጨማሪም አምላክ “ደስ የሚያሰኘኝንም ሁሉ አደርጋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። (ኢሳይያስ 45:18፤ 46:10፤ 55:11) ደግሞም አምላክን ደስ የሚያሰኘው ነገርም ሆነ የእሱ ዓላማ፣ መጀመሪያ በነበረው ዓላማ መሠረት ይህች ምድር ከዳር እስከ ዳር ገነት ሆና እሱን ለዘላለም በደስታ እያገለገሉ በሚኖሩ ሰዎች እንድትሞላ ነበር።—መዝሙር 37:29፤ ኢሳይያስ 35:5, 6፤ 65:21-24፤ ራእይ 21:3, 4

የአምላክ ዓላማ የሚፈጸመው እንዴት ነው?

ይሖዋ ሰዎችን ከወረሱት ኃጢአትም ሆነ የኃጢአት ውጤት ከሆኑት አለፍጽምናና ሞት ነፃ ለማውጣት ዝግጅት ሲያደርግ ተወዳዳሪ የሌለው ጥበቡንና ፍቅሩን አሳይቷል። ይህንንም ያደረገው ሌሎች ሰዎች ሁሉ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ከወረሱት ኃጢአት ነፃ የሆነ ልጅ እንዲወለድ በማድረግ ነው። ይህ ዝግጅት ቤዛ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን የሚገባቸው ሆነው የተገኙ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ የሚያደርግ ነው። (ማቴዎስ 20:28፤ ኤፌሶን 1:7፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6) ቤዛው የተዘጋጀው እንዴት ነበር?

ገብርኤል የሚባለው የይሖዋ መልአክ ማርያም ለምትባል አንዲት ድንግል ሴት በተአምር ልጅ እንደምትወልድ አበሰራት፤ ‘ከወንድ ጋር ግንኙነት ፈጽማ ባታውቅም’ ልጁን የምትወልደው እንዴት እንደሆነም ጭምር ገለጸላት። አምላክ በሰማይ የተከበረ ማዕረግ የነበረውን የበኩር ልጁን ሕይወት ወስዶ በማርያም ማሕፀን ውስጥ ወዳለ እንቁላል በማዛወር ተአምር ፈጸመ። በመሆኑም ማርያም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ አማካኝነት ወንድ ልጅ ጸነሰች።—ሉቃስ 1:26-35

ኢየሱስ ከዘጠኝ ወር ገደማ በኋላ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጋር ሊመሳሰል የሚችል ፍጹም ሰው ሆኖ ተወለደ። ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞት ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወቱን ሊሰጥ ችሏል። እንዲህ በማድረግ ኢየሱስ “የኋለኛው አዳም” የሆነ ከመሆኑም ሌላ ለአምላክ ታማኝ የሆኑ ሰዎች በሙሉ ከኃጢአትና ከሞት የሚዋጁበትን መሠረት ጥሏል።—1 ቆሮንቶስ 15:45, 47

በእርግጥም አምላክ ላሳየን ለዚህ ታላቅ ፍቅር አጸፋውን ለመመለስ መነሳሳት ይኖርብናል! መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአል።” (ዮሐንስ 3:16) አሁን የሚነሳው ጥያቄ ‘ለአምላክ ፍቅር ምላሽ የምንሰጠው እንዴት ነው?’ የሚል ይሆናል። ለስጦታው የአመስጋኝነት ስሜት ማሳየት አይገባም? የአመስጋኝነት መንፈስ ያሳዩ አንዳንድ ሰዎችን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

ትርጉም ያለው ሕይወት መኖር

በፊተኛው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው ደኒዝ የአምላክን ሕግና መመሪያዎች በመጠበቅ እሱን ማክበሯ ለሕይወቷ ዓላማና ትርጉም እንደሰጠው ተገንዝባለች። እንዲህ ትላለች፦ “አምላክ ለሰው ልጆች የረዥም ጊዜ ዓላማ ያለው ከመሆኑም ሌላ የሚያመልኩት ሰዎች በአሁኑ ጊዜ እንዲያከናውኑት የሚፈልገው ሥራ እንዳለ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምሬያለሁ። ከዓላማው ጋር ተስማምቼ በመኖር የሰጠኝን ነፃ ምርጫ እሱን ለማመስገን ከማዋል የበለጠ አርኪ ሕይወት ይኖራል ብዬ አላስብም።”

እኛም የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ በመማር ከዚያም ፈቃዱን በመፈጸም ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንችላለን። እርግጥ ነው፣ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ሰብዓዊ ፍጽምና እንድናገኝ ከሚያስችለው ከቤዛዊ መሥዋዕቱ የተሟላ ጥቅም የምናገኘው ገና ወደፊት ነው። እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ በእያንዳንዳችን ውስጥ ያስቀመጠውን ለመንፈሳዊ ነገር ያለንን ጥማት ለማርካት መነሳታችን አጣዳፊ ጉዳይ ነው።

በዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጀመሪያ ክፍል ላይ የተጠቀሰው ዴቭ የነበረው መንፈሳዊ ጥማት ረክቶለታል። የሕይወትን ትርጉም በተመለከተ ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ አግኝቷል። “ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ” ይላል ዴቭ፣ “የአምላክን ዓላማ ከመማሬ በፊት የነበረው ሕይወቴ የእርባና ቢስ ጥረቶች መፈራረቂያ ሆኖ እንደነበረ ተገንዝቤያለሁ። በወቅቱ አልወቀው እንጂ በውስጤ ይሰማኝ ለነበረው ባዶነት ምክንያቱ ለካስ መንፈሳዊ ፍላጎቴ አለመርካቱ ነበር። አሁን ያ የባዶነት ስሜት ፈጽሞ አይሰማኝም። አሁን እዚህች ምድር ላይ የምኖረው ለምን እንደሆነና በሕይወቴ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ተረድቻለሁ።”

አዎን፣ ፍጹም ካልሆኑ ሰዎች አስተሳሰብ በተለየ መልኩ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው አምላክ ስለ ሕይወት ትርጉም ያለው አመለካከት እጅግ የሚያረካ ነው። እዚህች ምድር ላይ ልንኖር የቻልነው ይሖዋ እኛን በዓላማ ስለፈጠረን ነው፤ ዓላማውም ስሙን እንድናወድስ፣ ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረንና በዚህ መንገድም መንፈሳዊ ፍላጎታችንን እንድናረካ ነው። ዛሬም ሆነ ለዘላለም “[ይሖዋ፣ NW] አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን ነው” የሚለው በመንፈስ መሪነት የተነገረ ቃል ሲፈጸም በማየት መደሰት እንችላለን!—መዝሙር 144:15

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

በሰዎች ላይ የሚደርሰው መከራ

የሚደርስብን መከራ እዚህ ምድር ላይ የምንኖርበትን ምክንያት ለመረዳት እጅግ አዳጋች ከሚያደርገው ተፈታታኝ ሁኔታ አንዱ ነው። ቪክቶር ፍራንከል እንደሚከተለው በማለት ተናግረዋል፦ “ሕይወት ትርጉም አለው ከተባለ፣ በሰዎች ላይ የሚደርሰው መከራም ትርጉም ሊኖረው ይገባል። እንደ ዕድልና ሞት ሁሉ መከራም ሊወገድ የማይችል የሕይወት ክፍል ነው።”

መጽሐፍ ቅዱስ የመከራና የሞት መንስዔ ምን እንደሆነ ይገልጻል። ለእነዚህ ነገሮች አምላክ ተጠያቂ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መከራና ሞት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከፈጣሪያቸው ተነጥለው የራሳቸውን ሕይወት ለመምራት ያደረጉት መጥፎ ውሳኔ ያስከተላቸው መዘዞች ናቸው። የእነሱ ዘሮችም በሙሉ ይህን የኃጢአት ዝንባሌ የወረሱ ሲሆን በሰው ዘር ላይ ለሚደርሰው መከራ ዋናው መንስዔም ይኸው ነው።

ምንም እንኳን እዚህች ምድር ላይ የምንኖረው ለምን እንደሆነ ማወቁ በሕይወት ውስጥ ለሚያጋጥሙን ችግሮች በሙሉ መፍትሔ ባይሆንም ችግሮቹን እንድንቋቋም ይረዳናል። በተጨማሪም አምላክ መከራና ሞትን ለዘላለም የሚያስወግድበት ጊዜ ወደፊት እንደሚመጣ ተስፋ ተሰጥቶናል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ሥዕላዊ መግለጫ]

መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሰጠውን ተስፋ አስተማማኝነት አስደናቂ ከሆነው የውኃ ዑደት ጋር ያመሳስለዋል

[ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ዝናብ

የውኃ ተን

የውኃ ተን

ሐይቆችና ወንዞች

ውቅያኖሶች

[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከጊዜ በኋላ ምድር ደስተኛና ጤናማ የሆኑ ሰዎች የሚኖሩባት ገነት እንደምትሆን እርግጠኞች ልንሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

‘በተሰጠኝ ነፃ ምርጫ ተጠቅሜ አምላክን ለማገልገል ከመምረጥ የበለጠ አርኪ ሕይወት ይኖራል ብዬ አላስብም።’—ደኒዝ