በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን ከመመልከት መራቅ የምችለው እንዴት ነው?

ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን ከመመልከት መራቅ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ . . .

ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን ከመመልከት መራቅ የምችለው እንዴት ነው?

“አንድ ልጅ በትምህርት ቤት ውስጥ በሚገኘው ቁም ሣጥኑ በር ላይ በውስጥ በኩል እራቁቷን የሆነች አንዲት ሴት ሥዕል ለጥፏል። የእሱ ቁም ሣጥን ከእኔ ብዙም ሩቅ አልነበረም።”—ሮበርት *

“በትምህርት ቤት ለማቀርበው ሪፖርት በኢንተርኔት አማካኝነት ምርምር እያደረግሁ ሳለ ወሲባዊ ሥዕሎችን እንዳይ የሚጋብዝ ድረ ገጽ አጋጠመኝ።”—አኔት

ወላጆችህ በአንተ ዕድሜ ሳሉ ሰዎች ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን ማየት ቢፈልጉ በቀላሉ ማግኘት አይችሉም ነበር። ዛሬ ግን እንዲህ ያለው ነገር አንተን ፈልጎ የሚመጣ ይመስላል። ከላይ እንደተጠቀሰው እንደ ሮበርት ሁሉ ዓይንህ አብሮህ በሚማር ልጅ ወሲባዊ ሥዕል ላይ ያርፍ ይሆናል። ወይም ደግሞ ልክ እንደ አኔት ኢንተርኔት ስትጠቀም ድንገት ሊያጋጥምህ ይችላል። አንዲት የ19 ዓመት ልጅ እንዲህ ብላለች:- “አንዳንድ ጊዜ በኢንተርኔት አማካኝነት የተለያዩ ድረ ገጾች እየቃኘሁ ወይም እየተገበያየሁ ሌላው ቀርቶ የባንክ ሒሳቤን እየተመለከትኩ ሳለ ወሲባዊ ሥዕሎችን የያዘ ድረ ገጽ ድንገት ብቅ ይላል!” *

እንዲህ ያለው ነገር የተለመደ ነው። አንድ ጥናት እንዳመለከተው ከ8 እስከ 16 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 90 በመቶ የሚሆኑት ኢንተርኔት እየተጠቀሙ እያለ ድንገት ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን የያዙ ድረ ገጾች እንዳጋጠሟቸው ተናግረዋል፤ ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው ሁኔታ የሚያጋጥማቸው የቤት ሥራቸውን በመሥራት ላይ ሳሉ ነው! ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን የያዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድረ ገጾች ስላሉ ዛሬ እነዚህን ነገሮች ማግኘት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ቀላል ሆኗል። ሌላው ቀርቶ በሞባይል ስልኮች አማካኝነት እንኳ ማግኘት ይቻላል። የ16 ዓመቷ ዴኒዝ “እንዲህ ያለው ነገር በትምህርት ቤታችን በጣም የተለመደ ነው፤ ሰኞ ሰኞ ወሬው ሁሉ ‘ቅዳሜና እሁድ ሞባይልህ ላይ የትኞቹን ሥዕሎች ጫንክ?’ የሚል ነው” ብላለች።

ብዙ ሰዎች ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን እንደሚመለከቱ ስታውቅ ‘ይህ ነገር በእርግጥ ጎጂ ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። መልሱ አዎን የሚል ነው። ለዚህ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም እስቲ ሦስቱን ብቻ እንመልከት:-

ወሲባዊ ሥዕሎች የአዘጋጆቹንም ሆነ የሚመለከቱትን ሰዎች ክብር ዝቅ ያደርጋል።—1 ተሰሎንቄ 4:3-5

ሰዎች ወሲባዊ ሥዕሎች ለማየት የሚያድርባቸው ፍላጎት በኖኅ ዘመን የነበሩት ክፉ መናፍስት ከተፈጥሮ ውጪ የሆነ የጾታ ግንኙነት እንዲፈጽሙ ካነሳሳቸው ስሜት ጋር ይመሳሰላል።—ዘፍጥረት 6:2፤ ይሁዳ 6, 7

ወሲባዊ ሥዕሎችን መመልከት ብዙውን ጊዜ የጾታ ብልግና ወደ መፈጸም ይመራል።—ያዕቆብ 1:14, 15

ወሲባዊ ሥዕሎች በመመልከት ሱስ የተጠመዱ ሰዎች ከባድ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። እስቲ ሁለት ግለሰቦች የሰጡትን አስተያየት ተመልከት:-

“ወሲባዊ ሥዕሎችን መመልከት የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ስለነበር ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ ከፍተኛ ትግል ማድረግ ጠይቆብኝ ነበር። ይህን ልማድ ካሸነፍኩ በርካታ ዓመታት ያለፉ ቢሆኑም ሥዕሎቹ ፈጽሞ ከአእምሮዬ ሊጠፉ አልቻሉም። ሥዕሎቹ ከአእምሮህ ላይ ስለማይፋቁ ሕሊናህ መቼም ቢሆን ንጹሕ የሚሆን አይመስልህም። ወሲባዊ ሥዕሎችን መመልከት ለራስህ ያለህን አክብሮት እንድታጣ ብሎም ሁልጊዜ እንደቆሸሽክና ዋጋ እንደሌለህ እንዲሰማህ ያደርጋል። ማንም የማያውቅልህን ይህን ሸክም ተሸክመህ ትኖራለህ።”—ኤሪካ

“ወሲባዊ ሥዕሎችን መመልከት ለ10 ዓመታት ሱስ ሆኖብኝ ነበር። ከዚህ ሱስ ከተላቀቅኩ 14 ዓመታት ሆኖኛል። ይሁንና አሁንም እንዲህ ዓይነት ነገሮችን ላለማየት በየቀኑ ትግል ማድረግ ጠይቆብኛል። እነዚህን ሥዕሎች ለማየት ያለኝ ፍላጎት በጣም ቢቀንስም ሙሉ በሙሉ አልጠፋም። አሁንም እይ እይ የሚለኝ ጊዜ አለ። ሥዕሎቹ አሁን ድረስ ከአእምሮዬ አልጠፉም። ምናለ እንዲህ ያለ ነገር ማየት ባልጀመርኩ ኖሮ። መጀመሪያ ላይ ምንም ጉዳት ያለው አልመሰለኝም ነበር። አሁን ግን ጉዳቱ ገብቶኛል። ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን መመልከት ጎጂና መጥፎ ከመሆኑም በላይ የአዘጋጆቹንም ሆነ የሚመለከቱትን ሰዎች ክብር ዝቅ የሚያደርግ ነው። ይህን ድርጊት የሚደግፉ ሰዎች ምንም ይበሉ ምን ወሲባዊ ሥዕሎች ይህ ነው የሚባል ጥቅም የላቸውም።”—ጄፍ

ሁኔታውን መገምገም

በድንገት የሚያጋጥምህን ጨምሮ ማንኛውንም ዓይነት ወሲባዊ ሥዕልና ፊልም ፈጽሞ ላለመመልከት ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ? በቅድሚያ ሁኔታውን ገምግም።

ወሲባዊ ሥዕሎችን በድንገት የምታገኝበት አጋጣሚ ምን ያህል ነው?

ጭራሽ አላጋጠመኝም አልፎ አልፎ

በየሳምንቱ በየቀኑ

አብዛኛውን ጊዜ የሚያጋጥምህ የት ነው?

በኢንተርኔት በትምህርት ቤት

በቴሌቪዥን በሌላ አጋጣሚ

በአብዛኛው የሚያጋጥምህ በምን መንገድ ነው?

እስቲ የሚከተሉትን ምሳሌዎች ተመልከት:-

አንዳንድ የክፍልህ ልጆች በኢ-ሜይል ወይም በሞባይል ወሲባዊ ሥዕሎችን የመላክ ልማድ አላቸው? ይህን ማወቅህ የተላከልህን ነገር ሳትከፍተው እንድታጠፋው ሊገፋፋህ ይችላል።

ኢንተርኔት እየተጠቀምክ ሳለ መረጃ ለመፈለግ የተወሰኑ ቃላትን ስታስገባ ሌላ ድረ ገጽ እንድትከፍት የሚጋብዝ መልእክት ወይም ሥዕል ብቅ ይላል? ይህ ሊያጋጥም እንደሚችል ማወቅህ በቃላት አጠቃቀምህ ላይ ይበልጥ ጥንቃቄ እንድታደርግ ይረዳሃል።

ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን ወደ መመልከት ያመሩህን ሌሎች አጋጣሚዎች ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․․

ከላይ ከቀረቡት ነጥቦች አንጻር ወሲባዊ ሥዕሎች ድንገት የሚመጡበትን አጋጣሚ ለመቀነስ ምን ማድረግ ትችላለህ? (ሐሳብህን ከዚህ በታች ጻፍ።)

․․․․․․

ወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች ድንገት ቢያጋጥሙህ ምን ታደርጋለህ?

ወዲያውኑ ዞር እላለሁ

ከመጓጓቴ የተነሳ ትንሽ አየት አደርጋለሁ

ማየቴን እቀጥላለሁ፤ እንዲያውም ሌላ ለማግኘት እሞክራለሁ

ምልክት ያደረግከው በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ምርጫ ላይ ከሆነ ሁኔታውን ለማሻሻል ምን ግብ ማውጣት ትችላለህ?

․․․․․․

ከዚህ ልማድ መላቀቅ

ሳይታወቃቸው ለወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች የተጋለጡ አንዳንድ ሰዎች እነዚህን ነገሮች ይበልጥ የማየት ጉጉት ስለሚያድርባቸው ከጊዜ በኋላ ልማድ ይሆንባቸዋል። ከዚህ ልማድ መላቀቅ ደግሞ እንዲህ ቀላል አይደለም። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጄፍ እንዲህ ብሏል:- “መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ከመጀመሬ በፊት ያልወሰድኩት የአደንዛዥ ዕፅ ዓይነት የለም ማለት ይቻላል። ሱስ ከሆኑብኝ ነገሮች ሁሉ ለመላቀቅ በጣም የከበደኝ ግን ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን የማየት ልማዴ ነበር።”

ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን የመመልከት ልማድ ካለህ ተስፋ አትቁረጥ። ከዚህ በታች በተጠቀሱት ሐሳቦች ላይ ማሰብህ ሊረዳህ ይችላል።

ወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች ዓላማቸው ምን እንደሆነ ተረዳ። እነዚህ ሥዕሎችና ፊልሞች ይሖዋ ክቡር አድርጎ የፈጠራቸውን ነገሮች ለማራከስ ሰይጣን የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች መሆናቸው ግልጽ ነው። እነዚህን ነገሮች ከዚህ አንጻር መመልከትህ ‘ክፋትን እንድትጠላ’ ይረዳሃል።—መዝሙር 97:10

የሚያስከትላቸውን መዘዞች አስብ። ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን መመልከት ለትዳር መፍረስ ምክንያት ይሆናል። የሴቶችንም ሆነ የወንዶችን ክብር ይነካል። የሚመለከተውንም ሰው ክብር ይቀንሳል። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል” ማለቱ የተገባ ነው። (ምሳሌ 22:3) ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን የመመልከት ልማድ ቢኖርህ ሊያጋጥምህ የሚችለውን አደጋ ወይም መዘዝ ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․․

ለራስህ ቃል ግባ። ታማኝ የነበረው ኢዮብ “ወደ ኰረዳዪቱ ላለመመልከት፣ ከዐይኔ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ” ሲል ተናግሯል። (ኢዮብ 31:1) እንደሚከተለው እያልክ ለራስህ ‘ቃል’ መግባት ትችላለህ:-

□ አንድ ክፍል ውስጥ ብቻዬን ስሆን ኢንተርኔት አልጠቀምም።

□ የብልግና ሥዕሎችን እንድመለከት የሚጋብዙ መልእክቶች ወይም ድረ ገጾች ከመጡ ወዲያውኑ አጠፋቸዋለሁ።

□ ችግሩ ካገረሸብኝ ጉዳዩን ለአንድ የጎለመሰ ጓደኛዬ አጫውተዋለሁ።

ከዚህ ልማድ ጋር በምታደርገው ትግል አሸናፊ ለመሆን ልትገባው የምትችል ሌላ ቃል ኪዳን አለ? ካለ ሁለት ሦስቱን ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․․

ጉዳዩን አስመልክተህ ጸልይ። መዝሙራዊው “ከንቱ ነገር ከማየት ዐይኖቼን መልስ” በማለት ወደ ይሖዋ ጸልዮአል። (መዝሙር 119:37) ለኃጢአተኛው ሥጋችን ማራኪ የሆነን ነገር መቋቋም አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል እሙን ነው። ይሁንና ይሖዋ አምላክ ይህን ችግር እንድታሸንፍ ስለሚፈልግ ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ እንድትችል “እጅግ ታላቅ ኀይል” ይሰጥሃል!—2 ቆሮንቶስ 4:7

ለሌላ ሰው አማክር። እንደዚህ ማድረግ ያሳፍርሃል? ምናልባት ያሳፍርህ ይሆናል! ይሁን እንጂ ሁኔታውን ለሌላ ሰው ማማከርህ ምን ያህል እፎይታ እንደሚያስገኝልህ አስብ። የምታማክረው ሰው ‘ለክፉ ቀን እንደተወለደ ወንድም’ ሊሆንልህ ይችላል። (ምሳሌ 17:17) ልታማክረው የምትችል ታማኝ ሰው መምረጥህ ብዙውን ጊዜ ይህን ልማድ ለማሸነፍ የሚረዳህ ወሳኝ እርምጃ ነው።

ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን የመመልከት ልማድ ካለህ ስለ ሁኔታው ቀርበህ ለማናገር የማይከብድህን አንድ የጎለመሰ ሰው ስም ከዚህ በታች ጻፍ።

․․․․․․

ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ በምታደርገው ትግል አሸናፊ መሆን እንደምትችል እርግጠኛ ሁን። እንዲያውም ይህ ሁኔታ አጋጥሞህ ሳትመለከት በቀረህ ቁጥር ከፍተኛ ድል እንዳገኘህ ሊሰማህ ይገባል። ይህን ድል ለይሖዋ ንገረው፤ ለሰጠህም ጥንካሬ አመስግነው። እንደ መቅሰፍት የተዛመቱትን ወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች ከመመልከት በራቅህ ቁጥር የይሖዋን ልብ ደስ እንደምታሰኝ አስታውስ!—ምሳሌ 27:11

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask . . .” በሚል ዓምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተለውጠዋል።

^ አን.5 ወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች ተብሎ የተተረጎመው ፖርኖግራፊ የተባለው የእንግሊዝኛ ቃል የተመልካቹን፣ የአንባቢውን ወይም የአድማጩን ስሜት ለመቀስቀስ ተብለው የሚዘጋጁ የጾታ ግንኙነትን በግልጽ የሚያሳዩ ሥዕሎችን፣ ፊልሞችንና በጽሑፍ የተዘጋጁ ነገሮችን ያመለክታል። በድምፅ የሚተላለፉ ነገሮችንም ሊጨምር ይችላል።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

▪ ወሲባዊ ሥዕሎችና ፊልሞች ክብር ያለውን ነገር የሚያራክሱት እንዴት ነው?

▪ ወሲባዊ ሥዕሎችንና ፊልሞችን ላለመመልከት የሚረዱህ ምን ተግባራዊ እርምጃዎች አሉ?

▪ እንዲህ ያለ ችግር ያለባቸው ወንድሞች ወይም እህቶች ካሉህ እንዴት ልትረዳቸው ትችላለህ?

[በገጽ 12, 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳንድ የክፍልህ ልጆች ወሲባዊ ሥዕሎችን በሞባይል የመላክ ልማድ አላቸው?